የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 1ኛ ዙር የክለቦች ዳሰሳ – ደደቢት

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመርያ ዙር መጠናቀቅን ተከትሎ ሶከር ኢትዮጵያ እያንዳንዱን ቡድን በተናጠል በመዳሰስ ላይ ትገኛለች፡፡ ዮናታን ሙሉጌታ እና ሚልኪያስ አበራ በዚህ ፅሁፍ አንደኛውን ዙር በ2ኛ ደረጃ ያጠናቀቀው ደደቢትን የ1ኛ ዙር አቋም እንዲህ ባለ መልኩ ዳሰውታል፡፡


የመጀመሪያ ዙር የደደቢት ጉዞ

ደደቢት በባለፈው አመት ጉድለቶቹ ላይ ያተኮሩ የተጨዋች ግዢ በማድረግ በቀድሞው የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ዮሀንስ ሰሀሌ እየተመራ ነበር ውድድሩን የጀመረው። አሰልጣኙ በሶስተኛው ሳምንት መልካ ቆሌ ላይ ከወልድያ ጋር ያለግብ አቻ ተለያይተው ከመሰናበታቸው በፊትም በሊጉ መጀመሪያ ኢትዮጵያ ቡናን አሸንፈው በቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ ተሸንፈው ነበር።

ከአሰልጣኝ ዮሀንስ ሳህሌ በኋላ ቡድኑን የተረከቡት በአመቱ መጀመሪያ ላይ ክለቡን በቴክኒክ ዳይሪክተርነት እያገለገሉ የነበሩት አንጋፋው አሰልጣኝ አስራት ሀይሌ ነበሩ። ቡድኑ በአዲሱ አሰልጣኙ ስር በመቀጠል ከህዳር ወር እስከ ታህሳስ ወር መጨረሻ ካደረጋቸው 5 ጨዋታዎች አራቱን በማሸነፍ እንዲሁም አንዱን አቻ በመውጣት ከ15 ነጥቦች 13ቱን ማሳካት ቻለ። በዚህ ውጤት ምክንያትም ወደሊጉ መሪነት የመጣበትን አጋጣሚ እንዳገኘ ይታወሳል። በነዚህ አምስት ጨዋታዎች ደደቢት የተቆጠረበት አንድ ግብ ብቻ መሆኑም ለጠንካራ ጉዞው ሌላ ማሳያ ነው።

ይህ ጠንካራ አቋሙም እስከመጀመሪያው ዙር ማብቂያ ድረስ የሚቆም አይመስልም ነበር። ሆኖም ግን ቡድኑ ቀጣይ ድል ለማስመዝገብ እስከ 12ኛው ሳምንት መጠበቅ ነበረበት ። ከ9ኛው እስከ 11ኛው ሳምንት ድረስ ያደረጋቸውን ጨዋታዎችን በአቻ ውጤት ነበር የጨረሰው። 12ኛው ሳምንት ላይ ወደ ጎንደር ተጉዞ ፋሲል ከተማን አሸንፎ ከተመለሰ በኋላም አዲስ አበባ ላይ ከሊጉ ሌላ ተፎካካሪ አዳማ ከተማ ጋር ያለግብ አቻ ተለያይቶ በመቀጠል ይርጋለም ላይ በሲዳማ ቡና የአመቱን ሁለተኛ ሽንፈት ቀምሷል። ክለቡ መጀመሪያውን ዙር አበበ ቢቂላ ስታድየም ላይ ባጠናቀቀበት ጨዋታ ግን ወላይታ ድቻን 3-0 በሆነ ውጤት በመርታት እና ወደ ድል በመመለስ በዋንጫው ፉክክሩ ውስጥ ሆኖ አጠናቋል።


የቡድኑ ውጤት ከአምናው ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነፃፀር

ደደቢት በሁለቱም የውድድር አመታት የመጀመሪያ ዙር 7 ጨዋታዎችን አሸንፎ ሁለት ጨዋታዎችን ተሸንፏል። አምና በ25 ዘንድሮ በ27 ነጥብ በሁለተኝነት ደረጃ ነው ያጠናቀቀው። ከፍተኛ ለውጥ የተስተዋለው ቡድኑ ባስቆጠራቸው እና ግብ ባስተናገዳቸው አጋጣሚዎች ነው። ደደቢት አምና በመጀመሪያው ዙር ብዙ ጎል በማስቆጠር ከቀዳሚዎቹ ክለቦች አንዱ ነበር። በየጨዋታውም በአማካይ 1.76 ጎል ማስቆጠር ይችል የነበረ ሲሆን ይህ ቁጥር በዘንድሮው ውድድር ወደ 1.06 ዝቅ ብሏል። በተቃራኒው ቡድኑ በጨዋታ የሚቆጠርበት የግብ መጠን ከ 1.15 ወደ 0.46 ወርዷል። በዘንድሮው ውድድር ዝቅተኛ የግብ መጠን (7) ካስተናገዱ ሶስት ክለቦች መሀከል አንዱ የሆነው ደደቢት በ10 ጨዋታዎች ላይ ግብ ሳይቆጠርበት መውጣት ችሏል። አምና ግን ቡድኑ በተመሳሳይ ጊዜ ካደረጋቸው 13 ጨዋታዎች በ ሶስቱ ብቻ ነበር ግብ ሳይቆጠርበት የቀረው።

የመጀመሪያው ዙር የቡድኑ አቀራረብ

በአመቱ መጀመሪያ ላይ ደደቢት በአመዛኙ የ 4-4-2 የተጨዋቾች አደራደርን ይከተል ነበር። ከፊት ካሉት ሁለት አጥቂዎችም ዳዊት ፍቃዱ የሚያደርገው እንቅስቃሴ የቡድኑን ቅርፅ ወደ 4-4-1-1 የሚወስድበትም አጋጣሚ ነበር። ቡድኑ በተወሰኑ አጋጣሚዎችም የ 3-5-2 አጨዋወትን ሲተገብር ተመልክተናል። ውድድሩ በገፋ ቁጥር በተለይም በመጨረሻዎቹ ጨዋታዎች ላይ የአስራት መገርሳ እና የኮትዲቮዋሩ አማካይ ካድር ኩሊባሊ የመሀል ሜዳ ጥምረት የቡድኑን አወቃቀር ወደ 4-2-3-1 ያዘነበለ እንዲሆን ሲያደርገው ተስተውሏል። የደደቢት ዋና የማጥቃት አማራጮች ከሁለቱ መስመሮች የሚነሳ ሲሆን እያጠበቡ በሚጫወቱት የመስመር አማካዮቹ በኩል የጎል እድሎችን ለመፍጠር ይሞክራል። የሚፈጠሩት አብዛኞቹ እድሎችም የጌታነህ ከበደን እንቅስቃሴ ማዕከል ያደረጉ ናቸው።

ጠንካራ ጎን

በተለይ አሰልጣኝ አስራት ሀይሌ ቡድኑን ከተረከቡ በኋላ በአካል ብቃቱ ረገድ የደደቢት ተጨዋቾች ጠንክረው ታይተዋል። ይህም ቡድኑ በቀላሉ ጎል እንዳይቆጠርበት ካደረጉ ምክንያቶች መካከል አንዱ ነው።

ደደቢት ያለው የመከላከል ብቃት ዋናው ጥንካሬው ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ይህ ጥንካሬውም በርከት ያሉ ነጥቦችን እንዲሰበስብ እገዛ አድርጎለታል።  በተከላካይ መስመሩ ላይ ጉዳት እና ቅጣት ባስተናገደባቸው አጋጣሚዎች ሳይቀር በመሀል ተከላካይነት የሚያጣምራቸው ተጨዋቾች የጋራ እና የተናጠል ብቃት እንዲሁም እምብዛም በማጥቃቱ ላይ እየተሳተፉ ያልሆኑት የመስመር ተከላካዮቹ ሚናም ለመከላከል ጥንካሬው ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው። እዚህ ላይ እንደ ካድር ኩሊባሊ አይነት ያለ በተከላካይ እና በተከላካይ አማካይነት ሚና መጫወት የሚችል ተጨዋች መኖሩ ጥቅሙ የጎላ ነበር። በተከላካይ አማካይነት ሚና ተጫዋቹ ከአስራት መገርሳ ጋር ሲጣመር ተጋጣሚዎች በሜዳው ቁመት የሚሰነዝሩት ጥቃት ለደደቢት ያን ያህል ስጋት ሲፈጥር አይታይም። የመስመር አማካዮቹ የማጥቃት ተሳትፎም የቡድኑ ሌላ ጥረ ጎኑ ነው። በአንድ ለአንድ ግኑኝነቶች በተጋጣሚዎቻቸው ላይ የሚወስዱት ብልጫ እና የአጥቂውን መስመር በግል ጥረታቸው የሚያግዙበት መንገድ ለማጥቃት ስርዐቱ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው።

ሌላው የደደቢት ጥንካሬ ጌታነህ ከበደ ነው። ምንም እንኳን ቡድኑ የሚያስቆጥረው የጎል ብዛት በአማካይ ሲታይም ሆነ ከአምናው ጋር ሲነፃፀር ቀንሶ ቢታይም የጌታነህ ከበደ የሚያገኛቸውን እድሎች በአግባቡ የመጠቀም ብቃት ደደቢት ጨዋታዎችን አሸንፎ እንዲወጣ ትልቅ እገዛ አድርገዋል።


ደካማ ጎን

የደደቢት የማጥቃት አጨዋወት በድክመት የሚነሳ ነው። በተለይ ቡድኑ በሜዳው ቁመት በተከላካይ አማካዮች እና በፊት አጥቂዎች  እንዲሁም በሜዳው ስፋት በመስመር አማካዮች መሀል የሚንቀሳቀስ የመጨረሻ የግብ እድሎችን የሚፈጥር እንዲሁም በዙሪያው ያሉ የአማካይ እና የፊት መስመር ተሰላፊዎችን የሚያገናኝ ተጨዋች እጥረት አለበት። የሳምሶን ጥላሁን ጉዳቶች እና በቀደመው አቋሙ ላይ አለመገኘት እንዲሁም በዚህ በአስር ቁጥር ሚና ላይ በአማራጭነት የሚሰለፈው ሽመክት ጉግሳ በተፈጥሮ የመስመር ተጨዋች መሆኑ ቦታው የሚፈልገውን አገልግሎት በሚገባ መወጣት አለመቻሉ ይህን የቡድኑን ደካማ ጎን አጉልቶ የሚያሳይ ነው።

የደደቢት የማጥቃት አጨዋወት ላይ ሌላ የሚነሳው ጉዳይ የመስመር ተከላካዮቹ ደካማ ተሳትፎ ነው። የመስመር አማካዮቹ የማጥቃት ሀላፊነት ከፍ ያለ መሆኑና ሽመክት ጉግሳም ሆነ ኤፍሬም አሻሞ አጥብበው ወደመጫወቱ ማዘንበላቸው ከመስመር ተከላካዮቹ ፊት ለፊት ሰፊ ክፍተት ሲፈጠር ቢታይም በ 3-5-2 ቅርፅ የመስመር ተመላላሽዎች በሌሎቹ ቡድኑ በተከተላቸው አጨዋወቶች ደግሞ የመስመር ተከላካይ ቦታ ላይ ተሰልፈው የሚጫወቱ ተጨዋቾች በማጥቃቱ ላይ አብዝተው ሲሳተፉ አይስተዋሉም። ቡድኑ ብዙ የግብ እድሎችን ከሁሉም አቅጣጫዎች ለአጥቂዎቹ በብዛት እንዳይፈጥርም ነጥብ ዋነኛ ምክንያት ነው።

ሌላው የሰማያዊዎቹ ደካማ ጎን ከዚሁ የማጥቃት አማራጮች እጥረት ጋር ተያይዞ የቡድኑ የጎል ማስቆጠር ህልውና በጌታነህ ከበደ ላይ ብቻ መመስረቱ ነው። ጌታነህ ከበደ እና ዳዊት ፍቃዱ ዳግም በደደቢት መጣመራቸው ቡድኑ በዘንድሮው ውድድር ብዙ ጎሎችን እንዲያገኝ ያስችለዋል ተብሎ ቢጠበቅም የደዊት ፍቃዱ ከግብ አስቆጣሪነት መራቅ ግምቱን ፉርሽ አርጎታል። በእርግጥ ዳዊት እስካሁን ጎል ማስቆጠር ባይችልም በጌታነህ ጎሎች ላይ ቀጥተኛ ተሳታፊ የሆነባቸው አጋጣሚዎች በርካታ ናቸው። ሆኖም ግን  ደደቢት ከአጥቂ መስመር ተሰላፊዎቹ ውጪም በሌሎች ተጨዋቾች ጎል የማስቆጠር ከፍተኛ ችግር አለበት። ይህም ጥሩ የመሀል ተከላካዮች ካሏቸው እና የጌታነህን እንቅስቃሴ መግታት ከቻሉ ቡድኖች ጋር ሲገናኝ እንዲቸገር  አድርጎታል ።

በሁለተኛው ዙር ምን ይጠበቃል?

ደደቢት ኤሪክ ኦፖኩ እና ክዌኩ አንዶህ የተባሉ ጋናዊ የመሀል ተከላካይ እና የቀኝ መስመር አማካይ እንዲሁም የኢኳቶሪያል ጊኒ  ዜጋ የሆነውን አጥቂ ሮበን ኦባማ ኑሲ ማስፈረም ችሏል። ቡድኑ ካለው ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት እና ስል የአጥቂ መስመር አንፃር ሲታይ ደደቢት አዳዲስ ፈራሚዎቹን ከነባሮቹ ጋር በማጣመር ጥሩ ጉዞ ሊያደርግ እንደሚችል መገመት ይቻላል። ሆኖም ግን ቡድኑ የአማካይ መስመሩ ላይ ከፍተኛ መሻሻል ማድረግ ይጠበቅበታል።

የቡድኑ የመጀመሪያ ዙር ኮከብ ተጨዋች – ጌታነህ ከበደ

በሀገሪቱ ከሚገኙ ወጥ አቋም ካላቸው አጥቂዎች መሀከል ጌታነህ ግንባር ቀደሙ ነው። ዘንድሮ ተጨዋቹ ከደቡብ አፍሪካ መልስ የቀድሞ ክለቡን በመቀላቀል የቡድኑ ቁልፍ ተጨዋች ሆኖ ነበር የመጀመሪያውን ዙር ያጠናቀቀው። ብዙ የማግባት አጋጣሚዎችን የመፍጠር ችግር ባለበት ቡድን ውስጥ ሆኖም እንኳን የቦታ አያያዙ እና የአጨራረስ ብቃቱ ለደደቢት ትልቅ ጠቀሜታን እያስገኘለት ይገኛል ። ጌታነህ ደደቢት በሊጉ ካስቆጠራቸው ጎሎች መሀከል 68% የሚሆነውን ጎል ከመረብ ያገናኘ ሲሆንም በሌሎቹ ግቦችም ላይ የጎላ ተፅዕኖ ነበረው።

ተስፋ ሰጪ ተጨዋች – አቤል እንዳለ

አቤል እንዳለ በዚህ አመት ከተስፋ ቡድኑ ዋናውን የደደቢት ቡድን የተቀላቀለ ተጨዋች ነው። የመሀል ሜዳ አማካይ ቦታ ላይ የሚጫወተው አቤል የመሰለፍ ዕድል ባገኘባቸው ጨዋታዎች ከጎኑ ከሚሰለፉት ሌሎች አማካዮች ጋር የሚኖረው ጥምረት እና ከተከላካይ መስመሩ ፊት ሆኖ በመጫወት ደካማውን የደደቢትን የማጥቃት ሂደት ለማገዝ የሚያደርገው ጥረት ቡድኑ በሁለተኛው ዙር ለሚኖረው ጉዞ ተስፋን ከሚሰጡ ተጨዋቾች መሀከል ዋነኛው ያደርገዋል።

Leave a Reply