” በ2ኛው ዙር የጎል ማስቆጠር ድክመታችንን ቀርፈን እንመጣለን” አሸናፊ በቀለ

አዳማ ከተማ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አንደኛው ዙርን 4ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ አጠናቋል፡፡ ባለፉት አመታት ከነበረው ተፎካካሪነት አንጻር ደረጃው መንሸራተት ቢያሳይም ከመሪዎቹ ያለው ርቀት ጥቂት ነው፡፡ ዳዊት ጸሀዬ በአዳማ ከተማ አንደኛ ዙር እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ከቡድኑ አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ጋር ያደረገውን ቆይታ እንደሚከተለው አሰናድተነዋል፡፡

የአዳማ ከተማን በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያው ዙር እንቅስቃሴን እንዴት ተመለከትከው?

“አዳማ በመጀመሪያው ዙር እንደተመለከታችሁት ጠንካራ ተፎካካሪ እና ጥሩ ቡድን ነበር፡፡ የመጀመሪያውን ዙር በ26 ነጥብ በ4ኛ ደረጃ ማጠናቀቅም ችሏል ፤ በዚህም በህዝቡ ዘንድ በሰፊው ተቀባይነትን ማግኘት ችሏል፡፡”

በውድድር ዘመኑ በሜዳችሁ አበበ ቢቂላ ስታድየም ካደረጋችኀቸው 8 ጨዋታዎች ምንም ሽንፈት ሳታስተናግዱ በ6ቱ አሸንፋችሁ በ2 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይታችኃል፡፡ ይህንን የሜዳችሁን ጥንካሬ እንዴት ትገልፀዋለህ?

“ማንኛውም ቡድን በሜዳው ውጤታማ ለመሆን ጥረት ያደርጋል፡፡ እኛም ከዚህ ቀደም በርካታ ነጥቦችን የምንሰበስበው ከሜዳ ውጪ ነበር፡፡ በዘንድሮው አመት ግን ከበፊቱ በተሻለ በርካታ ነጥቦችን በመጀመሪያው ዙር በሜዳችን መሰብሰብ ችለናል፡፡ በዚህ ረገድ ዘንድሮ ከሌሎች አመት ተሽለናል ብዬ አስባለሁ፡፡”

በአንተ እይታ በመጀመሪያው ዙር በቡድንህ ላይ ያስተዋልካቸው ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች ምንድን ናቸው?

“ጠንካራ ጎናችን ብዬ የማስበው የቡድኔ ተጫዋቾች በጋራ መከላከል እና ማጥቃት መቻላችን ነው፡፡ እኛ ቡድን ውስጥ እንደ ቡድን እንጂ የግለሰብ የተናጠል እንቅስቃሴ ጎልቶ አይወጣም፡፡ ከዛም በተጨማሪ ሊጉ ላይ ከሚጫወቱ ቡድኖች በተለየ ከጨዋታው መጀመር አንስቶ እስከ መጨረሻው ደቂቃ ድረስ ታግሎ የሚጫወት ቡድን ነው መገንባት የቻልነው፡፡ በደካማ ጎንነት የማነሳው ነገር ቢኖር ጎል ጋር በተደጋጋሚ እንደመድረሳችን በአጨራረስ ችግር ምክንያት በሚፈለገው ደረጃ ግቦችን እያስቆጠርን አንገኝም፡፡ ይህ በሁለተኛው ዙር በዋንኛነት መታረም ያለበት ክፍተት ነው ብዬ አስባለሁ፡፡”

በመጀመሪያ ዙር የታዩትን ክፍተቶችን ለመድፈን እና በሁለተኛው ዙር የተሻለ ሆኖ ለመቅረብ ምን እየሰራችሁ ትገኛላችሁ? ለውጦችስ ይኖራሉ?

“ማንኛውም ቡድን በውጤታማነቱ ለመዝለቅ ከፈለገ ክፍተቶቹን ማረም ግዴታው ነው ፤ ስለዚህም እኛ በመጀመሪያው ዙር እድሎችን ወደ ግብ በመቀየር ላይ ይታዩብን የነበሩ ችግሮችን ለመቅረፍ ጠንካራ ስራዎችን ሰርተን እንመጣለን ፤ በተጫዋቾች ዝውውር ላይ በሊጉ ላይ እየታየ እንደሚገኘው አብዛኛዎቹ ክለቦች ኢትዮጵያውያን አያስፈልጉም ብለው ፊታቸውን ወደ ውጪ አዙረዋል፡፡ ነገርግን እኛ ከሌሎቹ በተለየ ባሉን ልጆች እንቀጥላለን፡፡”

አዳማ ከተማን የተመለከቱ አስተያየት ሰጪዎች ቡድኑ ከያዘው ስብስብ ጥልቀት እና ጥራት አንጻር ውጤቱ ከዚህም በላይ መሆን ነበረበት ፤ ይህ እንዳይሆን ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ የአሰልጣኙ የጨዋታ አቀራረብ በተለይ ከሜዳ ውጪ ያለው የመከላከል አቀራረብ ነው ሲሉ ይደመጣሉ. .

“ማንኛውም ሰው አስተያየት የመስጠት መብት እንዳለው አምናለሁ ፤ እኛ ደግም እነዚህ ወገኖች የሚሰጡትን አስተያየቶች አንቃወምም፡፡ ማንኛውም የስፖርቱ ቤተሰብ እንደሚያውቀው አዳማ ከተማ ውስጥ የሚገኙት አብዛኛዎቹ ተጫዋቾች ከነበሩባቸው ክለቦች የተቀነሱ ተጫዋቾች መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ሳይቀነሱ ወደ ቡድኑ የመጡት ልጆች ቁጥራቸው አምስት አይሞሉም ፤ ስለዚህ በተቀነሱ ልጆች በተገነባ ቡድን ይህን ያህል ውጤት ማምጣት በራሱ ለኔ ትልቅ ስኬት ነው ፤ ስለዚህ ማንኛውም ሰው የፈለገውን ሊል ይችላል፡፡ ነገር ግን ማውራት እና መስራት ፈፅሞ የተለያዩ ነገሮች ስለሆኑ ለኛ ይሄ ብዙም ግድ አይሰጠንም፡፡”

አዳማ ከነማ በያዘው በዚህ የቡድን ስብስብ እስከምን ድረስ መጓዝ ይችላል?

“ማንኛውም ቡድን የሚፈልገው ዋንጫን ነው ፤ ለመውረድ ነው የምጫወተው የሚል ቡድን የለም፡፡ ስለዚህ የኛም ፍላጎት እንደማንኛውም ቡድን ጥሩ ቡድን ይዞ እስከ መጨረሻው መጓዝ ነው፡፡ ነገርግን በምኞት ሳይሆን አመቱ መጨረሻ ላይ በሰራነው ልክ የሚገባንን ውጤት እናገኛለን ብዬ አስባለሁ፡፡

ሰሞኑን በተለያዩ የመገናኛ አውታሮች ስምህ ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ጋር በስፋት እየተያያዘ ይገኛል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ያለህ አስተያየት ምንድን ነው?

“እኔም እንደማንኛውም ኢትዮጲያዊ ሲወራ ሰምቻለሁ፡፡ ነገር ግን እኔ በእርግጠኝነት የማውቀው ነገር ቢኖር የስራ ማመልከቻ ማስገባቴን ብቻ ነው ፤ እንጂ እንደሚባለው ከኔ ጋር የተነጋገረም ሆነ ግንኙነት የፈጠረ አካል የለም፡፡”

ያጋሩ

Leave a Reply