የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 1ኛ ዙር የክለቦች ዳሰሳ – ጅማ አባ ቡና

ሶከር ኢትዮጵያ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመርያ ዙር መጠናቀቅን ተከትሎ ክለቦችን በተናጠል መዳሰሷን ቀጥላለች፡፡ ዮናታን ሙሉጌታ እና ሚልኪያስ አበራም በዚህ ፅሁፍ አንደኛውን ዙር በ14ኛ ደረጃ ያጠናቀቀው ጅማ አባ ቡናን የ1ኛ ዙር አቋም እንዲህ ባለ መልኩ ዳሰውታል፡፡


የመጀመሪያ ዙር የጅማ አባ ቡና ጉዞ

የጅማ አባ ቡና የአመቱ አጀማመር መልካም የሚባል ነበር። አምና በከፍተኛ ሊጉ የነበረበትን ምድብ ለ በአንደኝነት ያጠናቀቀው ይህ ክለብ በሊጉ ጅማሬ ባደረጋቸው ሶስት ጨዋታዎች በአንድ ድል እና በሁለት አቻዎች 5 ነጥቦችን ማሳካት ቻለ። ክለቡ ከከፍተኛ ሊግ ከመምጣቱ አንፃር የሶስቱ ጨዋታዎቹ ውጤት ምንም ግብ ካለማስተናገዱ ጋር ተደምሮ ምናልባትም የውድድሩ ክስተት ሊሆን እንደሚችል በብዙዎች ዘንድ ግምት እንዲሰጠው ያደረገ ነበር።

ቀጣይ የሊጉ ጨዋታዎች ግን ለምዕራብ ኢትዮጵያ ተወካዩ ቡድን ጥሩ ውጤትን ይዘው አልመጡም። ቡድኑ 9ኛው ሳምንት ላይ ሲዳማ ቡናን አስተናግዶ እስኪያሸንፍ ድረስ ካደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች በአራቱ ተሸንፎ በአንዱ ብቻ ነጥብ መጋራት ነበር የቻለው።  ከነዚህ ጨዋታዎች መካከልም በሜዳው ከተሸነፈ ረዥም ጊዜያት አስቆጥሮ ለነበረው ክለብ በ7ኛው ሳምንት ጅማ ላይ በፋሲል ከተማ 3-1 በሆነ ውጤት የደረሰበት ሽንፈት ያልተጠበቀ ነበር። በሲዳማ ቡና ላይ ያገኘው ድልም ለቡድኑ መነሳሻ ይሆነዋል ተብሎ ቢገመትም ጅማ አባ ቡና ሌላ ድል ለማግኘት እስከውድድሩ የመጨረሻ ዙር ድረስ መጠበቅ ነበረበት። በመሀል ከተደረጉት አምስት ጨዋታዎችም እንደቀደመው ጊዜ ሀሉ ማግኘት የቻለው 1 ነጥብ ብቻ ነበር። ይህ አዲስ አበባ ላይ በጥሩ አቋም ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ነጥብ የተጋራበት ጨዋታም ክለቡን ወደሊጉ ካመጡት አሰልጣኝ ደረጄ በላይ ጋር ያደረገው የመጨረሻ ጨዋታ ነበር ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን በአፍሪካ ዋንጫ ቀሪ ሁለት ጨዋታዎች ላይ የመሩትና እስከ አምና ድረስ መከላከያን ያገለገሉት  አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌም ጅማ አባ ቡናን 13ኛው ሳምንት ላይ ተረከቡ። አባ ቡና በአዲሱ አሰልጣኝ ስርም ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ከተሸነፈ በኋላ 15ኛው ሳምንት ላይ ድሬደዋ ከተማን አስተናግዶ 3-0 በመርታት እና የሊጉን ሶስተኛ ድሉን በማስመዝገብ ነበር የመጀመሪያውን ዙር ያጠናቀቀው ።

የዘንድሮው ውጤት ከአምናው ጋር ሲነጻጸር

ጅማ አባ ቡና አምና የከፍተኛ ሊግ ተወዳዳሪ እንደነበር የሚታወስ ነው። የሁለቱ ሊጎች ባህሪም ሆነ አጠቃላይ ደረጃ የተለያየ መሆኑ ለቀጥታ ላማነፃፀር ቢከብድም ጅማ አባ ቡና በከፍተኛ ሊጉ በተጋጣሚዎቹ ላይ ያሳይ የነበረው ብልጫ እና የማሸነፍ ስነ ልቦናው በፕሪሚየር ሊጉ አብሮት እንዳልቀጠለ ግን መናገር ይቻላል ።

የመጀመሪያው ዙር የቡድኑ አቀራረብ

ጅማ አባ ቡና የ 4-4-2 የተጫዋቾች የሜዳ ላይ አደራደር በሰፊው ሲተገብር ይስተዋላል። ከፊት ወጣቱ አሜ መሀመድን ከ መሀመድ ናስር ጋር በስፋት ሲያጣምር የተስተዋለ ሲሆን የአማካይ ክፍሉም ከክሪዚስቶም ንታንቢ ጎን የሚሰለፍ እና ከሳጥን እስከ ሳጥን ያለውን ቦታ ሸፍኖ የሚጫወትን አንድ አማካይ ከ ሁለት የመስመር አማካዮች ጋር ያጣመረ ነው። ከሁለቱ የመስመር አማካዮች በተለይም ከግራ መስመር አማካዩ ዳዊት ተፈራ የሚነሱ ኳሶች የቡድኑ ዋነኛ የማጥቃት አማራጮች ሆነው ሲያገለግሉ ይታያል። ከሁለቱ የፊት አጥቂዎችም መሀከል አንደኛው ወደ መስመሮች በመውጣት ከመስመር አማካዮቹ ጋር የመገናኘት ሚና ይኖረዋል። ከዚህ ውጪ ቡድኑ ከጥልቅ የአማካይ ቦታ እና ከኋላው መስመር በረጅሙ የሚላኩ ኳሶችንም በመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ሲጠቀም ይስተዋላል።


ጠንካራ ጎን

ምንም እንኳን እንደከዚህ ቀደሙ ሜዳው ላይ የማይደፈር ቡድን የመሆኑን ታሪክ በፋሲል ከተማ ፣ በኢትዮጵያ ቡና እና በወልድያ የደረሱበት ሽንፈቶች ቢቀንሱትም ጀማ አባ ቡና ሜዳው ላይ ከፍተኛ ቁጥር ባለው ደጋፊው ታግዞ የሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ላይ አንፃራዊ ጥንካሬ ያሳያል ። ቡድኑ ያሳካቸው ሶስት ድሎችም የተገኙት ጅማ ላይ በተደረጉ ጨዋታዎች ነው ። በመጀመሪያው ዙር ካስቆጠራቸው 10 ግቦችም ውስጥ 7ቱ ከመረብ ያረፉት እና ከሰበሰባቸው 14 ነጥቦች ውስጥ 78% የሚሆነውን ነጥብ ማስካት የቻለው በሜዳው ባደረጋቸው ጨዋታዎች ላይ ነው። ለነዚህ ውጤቶች መገኘት ደግሞ የደጋፊው ሚና ላቅ ያለ ነው። በጨዋታ ቀናት በጠዋት በስቴድየሙ ዙሪያ መሰብሰብ የሚጀምረው የጅማ አባ ቡና ደጋፊ የአየሩን ሞቃትነት በመቋቋም እና በየጨዋታው ላይ በከፍተኛ ቁጥር በመታደም ቡድኑን የሚያበረታታበት መንገድ የሚያስደንቅ ነው። የክለቡ የፕሪምየር ሊግ ተሳትፎም በአጠቃላይ በከተማዋ ላይ የፈጠረው እግር ኳሳዊ መነቃቃት ቀላል አይደለም ። ይህም ለወደፊቱ የአካባቢው የእግር ኳስ እድገት የሚኖረው አስተዋፅኦ ስፋ ያለ ነው።

በሜዳ ላይ ከሚታየው የተጨዋቾች እንቅስቃሴ አንፃር የመስመር አማካዮቹ የመከላከል ተሳትፎ በንፅፅር መልካም የሚባል ነው። ቡድኑ ሲከላከል ከመስመር ተከላካዮቹ ፊት እና ከተከላካይ አማካዩ ጎን የሚኖረውን ክፍተት ለመሸፈን የሚያደርጉት ጥረት የተከላካይ መስመሩ ይበልጥ እንዳይጋለጥ እና ከዚህም በላይ ጎሎች እንዳያስተናግድ እገዛ አድርጎለታል።

ፊት መስመር ላይ የሚጫወተው የወጣቱ አጥቂ አሜ መሃመድ የግል ጥረትም ሳይነሳ የሚታለፍ አይደለም። ከፍተኛ ሊጉን በኮከብ ግብ አግቢነት የጨረሰው አሜ ወደ መስመሮች በመውጣት እና ኳሶችን ይዞ ወደመሀል ለመግባት የሚያደርገው ጥረት የተጋጣሚ ተከላካዮችን አቋቋም ለመረበሽ ጥሩ አስተዋፅኦ ያለው ነው።  በግማሹ የውድድር አመት አራት ግቦችን ያስቆጠረው ታታሪው የጅማ አባ ቡና አጥቂ የጨዋታ ባህሪም የተከላካይ መስመራቸውን ወደመሀል ሜዳ አስጠግተው የሚጫወቱ ተጋጠሚዎችን በመልሶ ማጥቃት ለመግጠም ምቹ አማራጭ ያደርገዋል።

ደካማ ጎን

ጅማ አባ ቡና በመጀመሪያው ዙር ከሜዳው ውጪ ካደረጋቸው ሰባት ጨዋታዎች ማሳካት የቻለው አዲስ አበባ ስታድየም ላይ አዲስ አበባ ከተማን እና ቅዱስ ጊዮርጊስን ገጥሞ አቻ በተለያየባቸው ጨዋታዎች ያገኛቸውን ሁለት ነጥቦችን ብቻ ነው። በነዚህ ሰባት ጨዋታዎችም  ግብ ማስቆጠር የቻለው በሶስት አጋጣሚዎች ብቻ ነው። ከሶስቱ አጋጣሚዎች ውስጥም በሁለቱ ቀድሞ ግብ ማስቆጠር ቢችልም እስከ ሊጉ አጋማሽ ድረስ አባ ቡና ከሜዳው ውጪ 3 ነጥብ አሳክቶ መመለስ አልቻለም። ይህም በሊጉ ካሉ በተቃራኒ ቡድን ሜዳ ላይ ነጥብ መሰብሰብ ከሚቸግራቸው ቡድኖች መሀከል አንዱ ያደርገዋል።

በክለቡ ውጤት ላይ ዋና ተዋንያን ይሆናሉ ተብለው የተጠበቁ ተጨዋቾች የተናጠል አቋም መውረድ እና በቶሎ ወደ ቀደመው አቋማቸው አለመመለስ ጅማ አባ ቡና ላስመዘገበው የመጀመሪያ ዙር ደካማ ውጤት ሌላው ምክንያት ነው።   በውድድሩ አጋማሽ ላይ በጉዳት ከተለየው ግብ ጠባቂ ጀማል ጣሰው እና ወጥ አቋም ካሳዩት ቢያድግልኝ ኤልያስ እና ክሪዚስቶም ንታንቢ ውጪ የክለቡ አዳዲስ ፈራሚዎችም በተጠበቀው መጠን በቡድኑ ላይ አሻራቸውን ማሳረፍ አልቻሉም።

የጅማ አባ ቡና የማጥቃት አጨዋወት መነሻ ነጥቦች መመሳሰል በተጋጣሚዎቹ በቀላሉ እንዲገመት ያደረገው መሆኑ በቀላሉ ግቦችን እናዳያስቆጥር ፈተና ሲሆንበትም ተስተውሏል።  ጅማ አባ ቡና በተለይ በሜዳው ቁመት ዕድሎችን ሚፈጥር  ከአጥቂዎቹ ጀርባ የሚጫወት ነፃ ሚና ያለው ባለተሰጥኦ አማካይ ተጨዋች ያስፈልገዋል። የመሰመር ተከላካዮች የማጥቃት ተሳትፎም በእጅጉ ሊሻሻል የሚገባው ሲሆን በተለይም በግራ መስመር የተከላካይ ክፍል ላይ የቦታውን ተፈጥሯዊ ተጨዋች አለመያዙ ከማጥቃት ተሳትፎው ማነስ በተጨማሪም ለተጋጣሚዎቹ   በተደጋጋሚ ጥቃት ሲዳርገው ይስተዋላል።

ቡድኑ በሜዳው በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ላይ ከሚኖረው ከፍተኛ ጫና እና ሌሎች ከሜዳ ውጪ ባሉ ጉዳዮች ምክንያት ተጨዋቾች ነፃ ሆነው በሙሉ አቅማቸውን አውጥተው  አለማበርከታቸው የክለቡ ያመጀመሪያ ዙር ሌላው ደካማ ጎኑ ነበር ። ጅማ አባ ቡና በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ  በሊጉ እየተሳተፈ እንደመሆኑ መጠን በውድድሩ ላይ በዘላቂነት ለመቆየት እዚህ ነጥብ ላይ በትኩረት ሰርቶ ለክለቡ ተጨዋቾች እና አሰልጣኞች የዕምሮ ነፃነት ችግር የሚሆኑ ጉዳዮችን በመለየት መፍትሄዎችን ማምጣት የግድ ይለዋል።

በሁለተኛው ዙር ምን ይጠበቃል?

ጅማ አባ ቡና የመጀመሪያው ዙር ሊገባደድ ሶስት ጨዋታዎች ሲቀር ነበር የአሰልጣኝ ለውጥ ያደረገው። ምንም እንኳን የመጨረሻውን ጨዋታ በሰፊ ጎል አሸንፎ ግማሹን የውድድር አመት ቢጨርስም ክለቡ ሙሉ ለሙሉ ወደሚፈልገው አቋሙ ተመልሷል ለማለት ግን ጊዜው ገና ነው። የአሰልጣኝ ለውጡን ተከትሎም አባ ቡና የሽግግር ጊዜ ላይ ነው ማለት ይቻላል ። ሁለተኛው ዙር ከመጀመሩ በፊት ሁለት ዩጋንዳዊያን ተጨዋቾች በጅማ የሙከራ ጊዜ ቢያሳልፉም ክለቡ በመፈልገው ደረጃ ላይ ባለመገኘታችው ዝውውሮቹ ሳይፈፀሙ ቀርተዋል። ከዚህ በተጨማሪም ክለቡ በውሰት ከሌሎች የሊጉ ቡድኖች ላይ ተጨዋቾች ለማምጣት እየጣረ ነው።  ቡድኑ ድክመት ባሳየባቸው ቦታዎች ላይ ተጨማሪ ተጨዋቾች የሚመጡ ከሆነ  ከነባሮቹ የቡድኑ ተሰላፊዎች እና ከአዲሱ አሰልጣኛቸው ጋር በመሆን በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በሀገሪቱ ትልቅ ውድድር ላይ እየተካፈለ የሚገኘውን ጅማ አባ ቡናን በሁለተኛው ዙር ከወራጅ ቀጠናው የማራቅ ከባድ ሀላፊነት ይጠብቃቸዋል ።

የቡድኑ የመጀመሪያ ዙር ኮከብ ተጨዋች – ክሪዚስቶም ንታንቢ

ዩጋንዳዊው የተከላካይ አማካይ የምዕራብ የኢትዮጵያውን ቡድን የተቀላቀለው በዘንድሮው የውድድር አመት ነው። ምንም እንኳን በቅድመ የውድድር ጊዜው ላይ በአዲስ አበባ ዋንጫ ቡድኑ ባደረጋቸው ጨዋታዎች ጥሩ ሳይንቀሳቀስ ቢቀርም በመጀመሪያው ዙር የሊጉ ጨዋታዎች ግን ከፍተኛ መሻሻልን ማሳየት ችሏል። ተጨዋቹ ከሊጉ እና ከቡድን ጓደኞቹ ጋር እየተላመደ በመጣ ቁጥር የአማካይ መስመሩን ከበስተኋላ ሆኖ በመምራት እና እርጋታ በተሞላበት አጨዋወቱ ወጥ የሆነ ብቃትን አሳይቶናል። ንታንቢ በአንደኛው ዙር በ15ቱም ጨዋታዎች ላይ ለ1350 ደቂቃዎች ተሰልፈው ከተጫወቱ ጥቂት ተጨዋቾች አንዱ በመሆንም በአካል ብቃቱ በኩል ያለውን ከፍ ያለ ደረጃ ማሳየት ችሏል።

Leave a Reply