የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 1ኛ ዙር የክለቦች ዳሰሳ – አርባምንጭ ከተማ

ሶከር ኢትዮጵያ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመርያ ዙር መጠናቀቅን ተከትሎ ክለቦችን በተናጠል በመዳሰስ ላይ ትገኛለች፡፡ አንደኛውን ዙር በ7ኛ ደረጃ ያጠናቀቀው አርባምንጭ ከተማ የውድድር ዘመን አጋማሽ ጉዞ በአብርሃም ገብረማርያም እና ሚልኪያስ አበራ እንዲህ ተዳሷል፡፡

የመጀመርያ ዙር ጉዞ
በዘንድሮው የውድድር ዘመን የአርባምንጭ ከተማን የመጀመርያ ዙር ጉዞ በ3 ከፍሎ መመልከት ይቻላል፡፡ በህዳር ወር ባደረጋቸው 4 ጨዋታዎች ጅማ አባ ቡና ላይ ብቻ ድል አስመዝግቦ መልካም ያልሆነ የሊግ ጅማሮ አድርጓል፡፡ የቡድኑ ደጋፊዎችም በክለባቸው ውጤት ማጣት ምክንያት ተቃውሟቸውን ማሰማት ጀምረው ነበር፡፡

በታህሳስ ወር የተመለከትነው አርባምንጭ ደግሞ እጅግ የተሻሻለ ቡድን መሆን ችሎ ነበር፡፡ በወሩ ምንም ጨዋታ ያልተሸነፈ ሲሆን ከሜዳ ውጪ ሳይቀር ነጥቦችን በመሰብሰብ ወደ ሰንጠረዡ አናት መጠጋት ችሏል፡፡

የጥር ወርን መከላከያን ከሜዳው ውጪ በመርታት ቢጀምርም ካለፈው ጋር ሲነጻጸር የተቀዛቀዘ ጉዞ በማድረግ አንደኛውን ዙር በደረጃ ሰንጠረዡ ወገብ ላይ አጠናቋል፡፡

 የቡድኑ ውጤት ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር
ቡድኑ ዘንድሮ ከአምናው የመጀመርያው አጋማሽ ፍጹም የተለየ ውጤት አስመዝግቧል፡፡ አምና በተመሳሳይ ወቅት 12ኛ ደረጃ ላይ የነበረ ሲሆን መሰብሰብ የቻለው 14 ነጥቦችን (በአማካይ በጨዋታ 1.1 ነጥብ) ብቻ ነበር፡፡ ዘንድሮ 22 ነጥብ (በአማካይ 1.4) በመሰብሰብ በሰንጠረዡ ወገብ ላይ ተቀምጧል፡፡

ጎል በማስቆጠር ረገድም የዘንድሮው የተሻለ ነው፡፡ አምና በ13 ጨዋታ 10 ጎሎች (በአማካይ 0.7 ጎል) ብቻ ሲያስቆጥር ዘንድሮ 17 ጎል (በአማካይ 1.13) በማስቆጠር ተሻሽሏል፡፡ ቡድኑ ከአምናው ጋር ሲነጻጸር በተመሳሳይ ደረጃ ላይ የሚገኘው የተከላካይ መስመሩ ነው፡፡ በሁለቱም አመታት በየጨዋታው በአማካይ 0.9 ጎል ያስተናግዳል፡፡

የጨዋታ አቀራረብ

አሰልጣኝ ጳውሎስ ጸጋዬ በውድድር ዘመኑ 4-4-2 የተጫዋቾች የሜዳ ላይ አደራደርን ተጠቅመዋል፡፡ የአማካይ መስመሩ በአብዛኛው ጠፍጣፋ ቅርጽ የሚይዝ ሲሆን በመጨረሻዎቹ 5 ጨዋታዎች የአማኑኤል ጎበናን አለመኖር ተከትሎ ተክቶት የተሰለፈው አለልኝ አዘነ አጨዋወት ቅርጹን ወደ 4-1-3-2 ሲቀይረው ተስተውሏል፡፡

የአጥቂ መስመሩ እንደ አማካዩ ሁሉ በሜዳው ወርድ የሚጣመሩ ሲሆን የመስመር አማካዮቹ ወደ መሃል አጥብበው ሲጫወቱ የሚፈጠረውን የስፋት ችግር አጥቂዎቹ ሲሸፍኑ በተደጋጋሚ ይስተዋላል፡፡

በሁለቱም መስመር የሚሰለፉት የመስመር ተከላካዮች ተደጋጋሚ የፊት ለፊት ሩጫ ሲያያደርጉ ሁለቱ ታታሪ አማካዮች (በተለይም ምንተስኖት አበራ) ትተውት የሚሄዱትን  ክፍተት በመሸፈን ይጠመዳሉ፡፡

ጠንካራ ጎን

የአማካይ ክፍሉ የቡድኑ ጠንካራ ጎን ነው፡፡ ታታሪነት ፣ የቴክኒክ ችሎታ እና የታክቲክ አረዳድ በ4 ተጫዋቾች የተዋቀረው የአማካይ ክፍል ላይ ይታያል፡፡ ከመስመር እየተነሱ የሚጫወቱት ወንድሜነህ ዘሪሁን እና ታደለ መንገሻ የድንቅ ክህሎት ባለቤት ሲሆኑ ተከላካይ ሰንጣቂ ኳሶቻቸው ግሩም ናቸው፡፡ በመሀለኛው የሜዳ ክፍል ጎን ለጎን የሚጣመሩት አማኑኤል ጎበና እና ምንተስኖት አበራ የቡድኑን ሚዛን የመጠበቅ ፣ እንቅስቃሴን የመምራት ፣ ክፍተት የመድፈን እና እርስ በእርስ ያላቸው መግባባት ድንቅ ነው፡፡

ተገማች ያልሆነ የጨዋታ አቀራረብ የቡድኑ ሌላው ጠንካራ ጎን ነው፡፡ የሊጉ አመዛኝ ቡድኖች ከሜዳቸው ውጪ ሲጫወቱ ይዘውት ከሚቀርቡት ጥብቅ መከላከል በተቃራኒው አርባምንጭ ከተማ በተለይ በመጀመርያው አጋማሽ ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ይዞ በመቅረብ የተጋጣሚዎቹን ግምት ሲያሳስት በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ ከሜዳው ውጪ ሁለት ድል አስመዝግቦ በ3 ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቶ እንዲወጣ ያደረገውም ይህ ከግምት ውጪ የሆነው አቀራረቡ ነው፡፡

የተከላካይ መስመሩ ደካማ ቢሆንም አጥቂዎች በመከላከል ሒደቱ ላይ የሚያደርጉት ተሳትፎ መልካም የሚባል ነው፡፡ ሁለቱ አጥቂዎች ኳስ ከኋላ እንዳይመሰረት የመጀመርያ መከላከል ከማድረጋቸው በተጨማሪ ቡድኑ በሚመራበት ወቅት እስከ መሀለኛው የሜዳ ክፍል ድረስ በመጠጋት የመከላከል እንቅስቃሴውን የማገዝ ልምዳቸው መልካም ነው፡፡

አሰልጣኝ ጳውሎስ ጸጋዬ ሁሉንም የቡድኑ ተጫዋች ለመጠቀም መሞከራቸውን እንደ ጠንካራ ጎን መውሰድ እንችላለን፡፡ የመጀመርያ ተሰላፊዎቻቸው ብዙ ጊዜ የማይቀያየሩ ቢሆኑም በተለያዩ አጋጣሚዎች ተጫዋቾች የመጫወቻ ጊዜ አግኝተዋል፡፡ ይህም አንድነት አዳነ ፣ ጸጋዬ አበራ እና አለልኝ አዘነን ከመሳሰሉ ተጫዋቾች ምርጥ ግልጋሎት እንዲያገኙ አድርጓቸዋል፡፡

 ደካማ ጎን
የተከላካይ ክፍሉ የቡድኑ ደካማ ጎን ነው፡፡ በመከላከል ቀጠናው ወጥ የሆነ የተጫዋቾች ጥምረት አለመኖሩ ቡድኑ የተረጋጋ የተከላካይ መስመር እንዳይኖረው አድርጓታል፡፡ የመሀል ተከላካዮች ወደ ግብ ጠባቂው ቀርበው የሚከላከሉ በመሆናቸው ከአማካይ ክፍሉ ጋር ሰፊ ክፍተት እንዲኖር እና መናበብ እንዳይችሉ አድርጓቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት የተከላካይ አማካዮቹ ክፍተት ለመድፈን ሰፊ ርቀት እንዲሸፍኑ አስገድዷቸዋል፡፡

የቡድኑ እንቅስቃሴ መሀል ለመሀል በሚደረግ እንቅስቃሴ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ የሜዳውን ስፋት የማይጠቀሙ ሲሆን በመስመር ለሚደረግ ጥቃት ተጋላጭ ናቸው፡፡ ቡድኑ ለመከላከልም ሆነ ለማጥቃት ተጨማሪ እቅዶች ካላዘጋጀ በሁለተኛው ዙር ሊቸገር ይችላል፡፡

በአንድ ቡድን ውስጥ ከአንድ በላይ ተጫዋች ነጻ ሚና መስጠት የሚያስከፍለውን ዋጋ አርባምንጭም ላይ ተመልክተናል፡፡ ወንድሜነህ እና ታደለ የተሰጣቸው ነጻ ሚና በቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ አዎንታዊ ተጽዕኖ ቢኖረውም ኳስ ከእግራቸው ስትወጣ ቡድኑን ለአደጋ ሲያጋልጠው ተመልክተናል፡፡ ሁለቱ ተጫዋችች በተናጠል በመከላከል እንቅስቃሴ ላይ ያላቸው ተሳትፎም ደካማ ነው፡፡

በሁለተኛው ዙር ምን እንጠብቅ?

አርባምንጭ በሁለተኛው ዙር አዳዲስ ተጫዋቾችን የማስፈረም እቀቅድ የሌለው በመሆኑ በስብስቡ ላይ ለውጥ አንመለከትም፡፡ በጉዳት እየተቸገሩ የሚገኙት ወንድወሰን ሚልኪያስ ፣ እንዳለ ከበደ ፣ አማኑኤል ጎበና እና አመለ ሚልኪያስ በሙሉ ጤንነት ላይ ከተገኙ አርባምንጭ የተሻለ ውጤት የማስመዝገብ እድል ይኖረዋል፡፡ በተለይ የወንድወሰን መመለስ የተከላካይ መስመሩን የተረጋጋ ለማድረግ ቁልፍ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡፡ እንዳለ ከበደ ሙሉ ጤነኛ ከሆነም ቡድኑ የሌለው ቀጥተኝነትን በመስጠት አማራጭ መፍጠር ይችላል፡፡

 የአንደኛው ዙር የቡድኑ ኮከብ ተጫዋች – ወንድሜነህ ዘሪሁን

ወንድሜነህ ምናልባትም የእግርኳስ ህይወቱ ምርጡ አቋም ላይ ይገኛል፡፡ ዘንድሮ አርባምንጭ ከተማን የተቀላቀለው ወንድሜነህ በፍጥነት ተጽዕኖ ፈጣሪነቱን ማሳየት ችሏል፡፡ በውድድር ዘመኑ 6 ጎል የሆኑ ኳሶች አመቻችቶ ያቀበለውና 2 ጎሎች በስሙ ያስመዘገበው ወንድሜነህ በየአመቱ የሚቸገርበትን ወጥ አቋም የማሳየት ችግር ከቀረፈ የፕሪምየር ሊጉ ኮከብ ተጫዋች ሊሆኑ ከሚችሉ ተጫዋቾች ዋንኛው ነው፡፡

ተስፋ የሚጣልበት – አንድነት አዳነ

አንድነት በተከላካዮች ጉዳት ምክንያት ያገኘውን የመሰለፍ እድል ተጠቅሞ ጥሩ እንቅስቃሴ ማሳየት ችሏል፡፡ ረጅሙ ተከላካይ በአንድ ለአንድ ግንኙነት እና ጉልበት አጠቃቀም ላይ ተስፋ የሚጣልበት ሲሆን ከኳስ ጋር ያለውን እንቅስቃሴ ማሻሻል ከቻለ የአርባምንጭ የተከላካይ መስመር መሪ የመሆን አቅም አለው፡፡

Leave a Reply