መሳይ ጳውሎስ በሁለተኛው ዙር ከሀዋሳ ከተማ ጋር ስኬትን ያልማል

በዘንድሮው የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በበርካታ ጨዋታዎችን ላይ የተሰለፉ ተጫዋቾች ዝርዝርን ብናስተውል አመዛኞቹ ተጫዋቾች በሊጉ ረጅም አመት የመጫወት ልምድ ያላቸው ናቸው፡፡ እንደ ሀዋሳ ከተማው መሳይ ጳውሎስ በቋሚነት እየተጫወቱ የሚገኙ ወጣት ተጫዋቾች ግን እጅግ ጥቂት ናቸው፡፡

ሀዋሳ ከተማ ዘንድሮ በሊጉ መጥፎ አመት እያሳለፈ ቢገኝም ከሌሎች ክለቦች በተሻለ አዳዲስ ፊቶችን በማሳየት ላይ ይገኛል፡፡ መሳይ ጳውሎስም ከነዚህ መካከል ጎልቶ በመውጣት ቋሚ አሰላለፍ ውስጥ ሰብሮ መግባት ችሏል፡፡

በሀዋሳ ተወልዶ ያደገው መሳይ በሰውነቱ ደቃቃነት ምክንያት በአካባቢ ጨዋታዎች ላይ ብዙዎች ትኩረት ቢነፍጉትም በ2007 የሀዋሳ ከተማ ታዳጊ ቡድኑን ከመቀላቀል አላገደውም፡፡ መሳይ ነገሮች በፍጥነት የተቀየሩበትን መንገድ እንዲህ ይገልፃል፡፡

” እግርኳስን መጫወት የጀመርኩት በልጅነቴ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ በጨርቅ በሚሰራ ኳስ ነው፡፡ አሁን በሀዋሳ ከተማ ዋናው ቡድን አብሮኝ ከሚገኘው ነጋሽ ታደሰ ጋር አንድ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ባቋቋመው የእግርኳስ ፕሮጀክት ውስጥም እንጫወት ነበር፡፡  በልጅነቴ ኳስ ተጫዋቾች እንደምሆን አስብ ነበር፡፡ እንዲህ በፍጥነት ግን በትልቅ ክለብ ውስጥ ገብቼ እጫወታለው ብዬ አስቤ አላውቅም፡፡ ” ይላል፡፡

መሳይ ታዳጊ ቡድኑን በተቀላቀለበት አመት ያሳየው ፈጣን እድገት የአሰልጣኝ ውበቱ አባተን ትኩረት አግኝቶ በ2008 የውድድር ዘመን ዋናውን የሀዋሳ ከተማ ቡድን መቀላቀል ችሏል፡፡ ” ወደ ሀዋሳ ከተማ የታዳጊ ቡድን የታቀፍኩት በክፍለ ከተማ ውድድር ላይ አንድ ጨዋታ ብቻ አድርጌ ነበር፡፡  ብዙም ሳልቆይ ወደ ዋናው ቡድን አደግኩ፡፡ ይህ ለኔ ትልቅ ፈተና ነበር፡፡  ነገር ግን በፍጥነት አእምሮዬን አሳመንኩት፡፡ አልፈራሁም ፤ እንደውም ራሴን ይበልጥ አበረታታሁት ” ሲል ፈጣን እድገቱን ይገልፃል፡፡

በእርግጥም መሳይ በዋናው ቡድን የመጀመሪያ ጨዋታውን በሀዋሳ ሴንትራል ዋንጫ ካደረገ በኋላ እድገቱን አላቋረጠም፡፡ በዘንድሮው የውድድር ዘመን መክፈቻ ሀዋሳ ከተማ በአአ ከተማ ከተሸነፈ በኋላ ባሉት ጨዋታዎች ከቡድኑ ቋሚ አሰላለፍ ወጥቶ አያውቅም፡፡

” በፕሪምየር ሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታዬን ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር በተደረገው ጨዋታ ተቀይሬ በመግባት ነበር ያደረግኩት፡፡ ወደ ሜዳ ስገባ ውስጤ በደስታ ተሞልቶ ነበር፡፡ ደስ የሚል ስሜት ነበር የተሰማኝ፡፡ ምክንያቱም ትልልቅ ውድድሮችን ተካፍዬ አላቅም፡፡ የሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታዬን ሁሌም ትልቅ ቦታ እሰጠዋለው፡፡ ተቀይሬ በገባሁበት ወቅት ከግርማ በቀለ ጋር በመሠለፌም ትልቅ የሆነ ነገርን ከሱ አግቻለው”

መሳይ ከሳምንት ሳምንት በሀዋሳ ቋሚ አሰላለፍ ውስጥ በመገኘቱ ከወዲሁ ከሊጉ ትልልቅ አጥቂዎች ጋር ለመጋፈጥ አስችሎታል፡፡ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር 1-1 አቻ በተለያዩበት ጨዋታ ከአዳነ ግርማ እና ሳላዲን ሰኢድ በተቃራኒ ተሰልፎ ሙገሳ ያስቸረው ብቃት ማሳየቱ ከአዳነ ግርማ ጭምር አድናቆት አትርፎለታል፡፡
” አዳነ እና ሳላዲን ትልልቅ ተጫዋቾች ከመሆናቸው አንፃር እንዲህ አይነት ብቃት አሳያለሁ ብዬ አልጠበቅኩም ነበር፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ታላቅ ክለብ ነው ፤ በዚህ አይነት ጨዋታ ላይ መሳተፍ እና ከአዳነ ጋር መፋጠጥ ደስ የሚል ስሜት አለው፡፡ በወቅቱ ደጋፊዎች የሰጡኝ ብርታት ስንቅ ሆኖኛል፡፡ አዳነ ጨዋታው ሲጠናቀቅ የሰጠኝ የማበረታቻ ሀሳቦች ደስ ይላል ፤ ምክሩም ጥሩ ነበር፡፡ ” ሲል በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ያስታውሳል፡፡

ሀዋሳ ከተማ በሊጉ የመጀመርያ ዙር የመጨረሻ ጨዋታዎች ያስመዘገበውን ውጤት ተከትሎ ከወራጅ ቀጠናው መውጣት ቢችልም አሁንም በመውረድ ስጋት ውስጥ ከሚገኙና በሁለተኛው ዙር ትልቅ ፈተና ከሚጠብቃቸው ክለቦች አንዱ ነው፡፡ መሳይ ጳውሎስም የሀዋሳን የመውረድ ስጋት የመቅረፍ አላማውን ገልጿል፡፡

” አሁን የማስበው ክለቤን አሁን ካለበት ደረጃ ለማውጣት መጣር ነው፡፡ በደጋፊዎች በኩል ይወርዳል የሚለው ስጋት እንዲጠፋ እፈልጋለው፡፡ ይህ እግርኳስ ጨዋታ ነው ፤ የሚመጣው ነገር አይታወቅም፡፡ ነገር ግን ይህ ክለብ ምንም አይሆንም፡፡ እኔ በበኩሌ ራሴን መስዋዕት ለማድረግ ተዘጋጅቻለሁ፡፡ ”

ሙሉጌታ ምህረት ፣ ሽመልስ በቀለ እና አዳነ ግርማ የመሳሰሉ ኮከቦችን ለብሄራዊ ቡድን ባፈራው ኮረም ሰፈር እየተጫወተ ያደገው መሳይ ከወደፊቱ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተስፋዎች አንዱ ነው፡፡ በሀዋሳ ያሳየውን ፈጣን እድገት ከደገመ በአጭር ጊዜ የዋልያዎቹን ማልያ ለብሶ እንመለከተው ይሆናል፡፡ ቁጥቡ መሳይ ግን ” ከዋናው ብሄራዊ ቡድን በታች ባሉ ቡድኖች መመረጥ ” የቅርብ ጊዜ አላማው ነው፡፡

Leave a Reply