” የወልድያ ተጨዋቾች መከላከል ላይ ያላቸው የብቃት ደረጃ ከፍ ያለ ነው ” አዳሙ መሀመድ

ወልድያ ወደ ፕሪምየር ሊጉ በተመለሰበት የውድድር ዘመን በሰንጠረዡ ወገብ አንደኛውን ዙር አጠናቋል፡፡ ቡድኑ ግብ የማስቆጠር ችግር ቢታይበትም የተከላካይ ክፍሉ በቀላሉ ግብ የማያስተናግድ እና በሚገባ የተዋሃደ ነው፡፡ ለቡድኑ የመከላከል ጥንካሬ ትልቁን አስተዋጽኦ እያበረከተ የሚገኘው ደግሞ አዳሙ መሀመድ ነው፡፡ ጋናዊው ተከላካይ ስለ ቡድኑ የመከላከል ጥንካሬ እና ተያያዥ ጉዳዮች ከሚልኪያስ አበራ ጋር ያደረገውን ቆይታ እንደሚከተለው አሰናድተነዋል፡፡


በአንደኛው ዙር የወልድያ ጉዞ ውስጥ ቁልፍ ከሚባሉ የቡድኑ ተጨዋቾች አንዱ ነህ. . .

በመጀመርያ ፈጣሪዬን አመሰግናለው። ይህ የሆነው በኔ ብቻ አይደለም ፤ ቡድን አጋሮቼን ፣ አሰልጣኝ ንጉሴን እና አጠቃላይ የአስተዳደር ሰዎችን አመሰግናለው ። በተለይ ደግሞ የወልድያ ደጋፊዎች ትልቅ ድጋፍ እየሰጡን ነው። በዚሁ ቀጥለን ሁለተኛው ዙር የበለጠ እንሰራለን ብዬ አስባለው፡፡

የቡድናችሁ ዋንኛ ጥንካሬው መከላከል ላይ ያለው የጨዋታ አቀራረብ ነው ይህን እንዴት ታየዋለህ ?

እንዳልከው ጠንካራ ጠንካራ ጎናችን እና የቡድናችን መለያ የመከላከል አጨዋወት ነው። እኔ ብቻ ሳልሆን ሁሉም የቡድኑ የተከላካይ መስመር ተጨዋቾች በዚህ ተጠቃሽ አስተዋፆ አድርገዋል፡፡ ልምምዳችንን ጠንክረን እንሰራለን ፤ በጨዋታ ላይ ፤ አካላዊ እና አምሮአዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በደንብ እንዘጋጃለን፡፡ ይህንን ጥምረትና ውህደት ይዘን በመቀጠል ሁለተኛው ዙር እንመጣለን

ይህን ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት የፈጠረ የተለየ ታክቲካዊ አቀራረብ አለ ወይስ የተጨዋቾች የግል ብቃት ላይ የተመሰረተ ጥንካሬ ነው?

በመጀመርያ እንደሚመስለኝ መከላከል አጨዋወት ላይ ተሳታፊዎች የሆኑ ተጨዋቾች መከላከል ላይ ያላቸው ብቃት ደረጃ ከፍ ያለ ነው። ልምዳቸውም ከፍተኛ ነው በታክቲክም ቢሆን ዲሲፕሊንድ ናቸው።

 በተለየ አድናቆት የምትቸራቸው የተከላካይ ተጨዋቾች በአገሪቱ እነማን ናቸው ?

አብዛኛዎቹ ጥሩ ናቸው፡፡ ደጉ ግን በጣም አደንቀዋለው፡፡ ከደጉ የምወስዳቸው ብዙ ጥሩ ነገሮች አሉ፡፡ ምክንያቱም ልምድ ያለውና አሁንም በጥሩ ብቃት እየተጫወተ ይገኛል ፤ በእግር ኳስ እድሜ ቁጥር ብቻ መሆኑን ያሳያል። አስቻለው ታመነንም እንዲሁ አደንቃለው ፤ ከ2 አመት በፊት በደደቢት አብሬው ጥሩ ጊዜ አሳልፌያለው። ሁለቱንም በደንብ የማደንቃቸው ተከላካዮች ናቸው።

የትኛው የአጥቂ ጥምረት ይበልጥኑ ይፈትንሀል ?

የጌታነህ  እና የዳዊት ፍቃዱ ጥምረት ለተከላካዮች ፈታኝ ናቸው ። ሁለቱም በጥሩ አቋማቸው ላይ ሲገኙ ለማቆም ትቸገራለህ፡፡ በተለይ የዳዊት እንቅስቃሴ ከፍተኛ ነው። ለጌታነህ ደግሞ ትንሽ እድል ከሰጠኸው በቃ ወደ ጎልነት ይቀይረዋል፡፡

ብዙ ጎል አይቆጠርባችሁም ፤ ጎሎችንም አታስቆጥሩም፡፡ ይህን ሚዛናዊ ለማድረግ ምን ታደርጋላቹ?

እርግጥ ነው ብዙ ጎሎች አይቆጠርብንም ያንን በደንብ ለማሻሻል እየሰራን ነው ። በመከላከል አጨዋወታችን ጥንካሬ እንዘልቃለን ፤ ጎሎችን ለማስቆጠር ደግሞ የበለጠ እንጥራለን። እንደሚመስለኝ በእግር ኳስ ጎሎች እንዳይቆጠርብህ ማድረግ ጥሩ ነው። በተለይ ደግሞ ጕሎች የማታስቆጥር ከሆነ፡፡

በኢትዮዽያ ረጅም ጊዜ ቆይተሃል፡፡ የኢትዮጵያውያን አኗኗር እና የህዝቡን ሁኔታ እንዴት አገኘኸው ?

ቱርክ ፣ አልባንያ እና ሌሎች ሀገሮች ተጫውቻለው፡፡ ወደ ኢትዮዽያ ከመጣሁ ስድስት አመት ሆኖኛል፡፡ የኢትዮዽያ እና የጋና አኗኗር ተመሳሳይ ነው፡፡ ህዝቡም በጣም ተግባቢ  እና መልካም ነው። በአጠቃላይ ኢትዮዽያ ሁለተኛ ሀገሬ ናት ደስተኛ ነኝ፡፡

Leave a Reply