የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 1ኛ ዙር የክለቦች ዳሰሳ – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመርያ ዙር መጠናቀቅን ተከትሎ ሶከር ኢትዮጵያ ክለቦችን በተናጠል በመዳሰስ ላይ ትገኛለች፡፡ አንደኛውን ዙር በ15ኛ ደረጃ ያጠናቀቀው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የውድድር ዘመን አጋማሽ ጉዞ በዮናታን ሙሉጌታ እና ሚልኪያስ አበራ እንዲህ ተዳሷል፡፡

የመጀመሪያ ዙር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጉዞ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመጀመሪያው ዙር ወጥ ያልሆነ አቋም ነበር ያሳየው። ቡድኑ የውድድር አመቱ ሲጀመር ያደረጋቸውን ሁለት ጨዋታዎች ከሜዳው ውጪ ወልድያ እና ጅማ ላይ አድርጎ በአዲስ አዳጊዎቹ ክለቦች ሽንፈትን ቀምሷል። በመቀጠል በ8ኛው ሳምንት በደደቢት እስከተረታበት ጊዜ ድረስ ከህዳር መጨረሻ እስከ ታህሳስ አጋማሽ ድረስ ከተደረጉ አራት ጨዋትዎች ሁለት አሸንፎ ሁለት አቻ በመውጣት በውድድሩ አጋማሽ በንፅፅር መልካም የሚባለውን ጊዜ ማሳለፍ ችሎ ነበር ። በመቀጠል እስከ ሊጉ የመጀመሪያ ዙር ማብቂያ ድረስ ያደረጋቸው ስምንት ጨዋታዎች ቡድኑን ወደ ወራጅ ቀጠናው የገፉት ነበሩ። 11ኛው ሳምንት ላይ የወቅቱ የሊጉ መሪ የነበረውን አዳማ ከተማን 2-0 ከረታበት ጨዋታ ውጪ በሁለተኛ ሳምንት ላይ ሳይደረግ በቀሪነት ተይዞ የነበረውን የሀዋሳ ከተማ ጨዋታ ጨምሮ 5 ሽንፈቶችን አስተናግዷል። በእነዚህ ጊዜያት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከወላይታ ድቻ እና ከመከላከያ ጋር ነጥብ ከመጋራቱ ውጪ ተጨማሪ ጨዋታዎችን ማሸነፍ አለመቻሉ እና በተለይ በመጨረሻዎቹ ጨዋታዎች ላይ በርከት ያሉ ጎሎችን ማስተናገዱን ተከትሎ የመጀመሪያውን ዙር በ15ኛ ደረጃ ላይ ሆኖ እንዲያጠናቅቅ ተገዷል።

የቡድኑ ውጤት ከአምናው ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነፃፀር

አምና በተመሳሳይ ጊዜ በስምንት ጨዋታዎች ላይ ነጥብ ተጋርቶ መውጣት ችሎ የነበረው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዘንድሮ ስምንት ሽንፈቶችን አስተናግዷል። በ 15 ጨዋታዎች የሰበሰበው 13 ነጥብም በ2008 የውድድሩ አጋማሽ በ13 ጨዋታዎች ካሳካቸው 17 ነጥቦች ያነሰ ነበር። በደረጃም ብናየው ዘንድሮ በወራጅ ቀጠና ውስጥ የጨረሰው ንግድ ባንክ አምና በሰንጠረዡ ወገብ ላይ 7ኛ ደረጃ ላይ ሆኖ ማጠናቀቅ ችሎ ነበር። በሌላ በኩል ቡድኑ በጨዋታ በአማካይ የሚያስቆጥረው የግብ መጠን ከአምናው ጋር ሲነፃፀር ከ 0.76 ወደ 1 እድገት ቢያሳይም በተቃራኒው የሚቆጠርበት የግብ መጠን ደግሞ በኣማካይ ከ 0.7 ወደ 1.6 ከፍ ብሏል ።

የመጀመሪያው ዙር የቡድኑ አቀራረብ

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንደ አምናው ሁሉ ዘንድሮም በ 4-1-4-1 የተጨዋቾች አደራደር ነበር አብዛኛውን ጨዋታ ያደረገው። ቡድኑ በዋነኝነት ከፊት ግዙፉን ናይጄሪያዊ አጥቂ ፒተር ንዋድኬን እንዲሁም ጋናዊውን ጂብሪል አህመድን ከተከላካዮች ፊት ባለው ቦታ ላይ ይጠቀማል። በሁለቱ መሀልም አራት አማካዮችን የሚያሰልፍ ሲሆን ሁለቱ ከግራ እና ከቀኝ መስመር ሲነሱ የተቀሩት ሁለቱ ደግሞ ከጂብሪል ፊት የሚኖረውን ቦታ ሸፍነው የሚጫወቱ ናቸው። ከነዚህ ሁለት የአጥቂ አማካዮች መሀከል አንዱ (በተለይ ታድዮስ) ወደ ጂብሪል ቀርቦ በሚጫወትባቸው አጋጣሚዎች የቡድኑን ቅትፅ ወደ 4-2-3-1 የሚያቀርበው ሲሆን የመስመር አማካዮቹም ከፒተር ጎን በሚገኙት ቦታዎች ላይ አመዝነው ሲጫወቱ ደግሞ የቡድኑን ቅርፅ ወደ 4-3-3 የሚያደላ ያስመስሉታል። ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የግብ ዕድሎችን የሚፈጥረው በአጥቂው ፒተር ንዋድኬ እንቅስቃሴ ላይ በመመስረት ነው። ብዙዎቹ ጥቃቶችም የሚነሱት ከመስመር አማካዮቹ ቢንያም በላይ እና ፍቅረየሱስ ተ/ብርሀን ነው። የመሀል አማካዮቹ ዮናስ ገረመው እና ታዲዮስ ወልዴም የቡድኑ ሌሎች የማጥቃት አማራጮች ናቸው ።

ጠንካራ ጎን

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ካሳለፈው ደካማ የውድድር አጋማሽ አንፃር ቡድኑ ውስጥ ጠንካራ ጎኖችን ማግኘት ከባድ ነው። ነገር ግን የቡድኑ ዋና ተሰላፊዎችን ጉዳት ተከትሎ ከተስፋ ቡድን ያደጉት ተጨዋቾች የተሰጣቸውን የመጫወት ዕድል እንደ አንድ መልካም ጎን ማንሳት ይገባል። ምንም እንኳን በቋሚነት የቡድኑን ውጤታማነት ይዘው መቀጠል ቢቸገሩም እነዚህ ተጨዋቾች በቀጣይ ጊዜያት ክለቡ ለሚኖረው ጉዞ ተስፋ ሊጣልባቸው ይችላል።

ደካማ ጎን

ለአመታት በክለቡ ዘንድ ዋና ድክመት የነበረው ደካማ ተፎካካሪነት ዘንድሮም ሳይቀረፍ ቀጥሏል። ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንደ ክለብ ያለው አቅም እና ሜዳ ላይ እንደ ቡድን የሚያሳየውም እንቅስቃሴ ሆነ የሚያስመዘግበው ውጤት እጅግ የተራራቁ ናቸው። በሊጉ የላይኛው የሰንጠረዡ ክፍል ላይ ካሉ ቡድኖች ጋር እንኳን ሲገናኝ ያሳይ የነበረው ጥንካሬ ዘንድሮ ከቡድኑ ጋር የለም።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዘንድሮው ስብስብ ልምድ ከሌላቸው እና ከአዳጊዎቹ ወጣቶች ውጪ በብዛት የእግር ኳስ ዘመናቸው መጨረሻ ላይ በሚገኙ ተጨዋቾች የተሞላ ነው። ከዚህ በተጨማሪም የቡድኑ ቁልፍ ተጨዋቾች በጉዳት እና በተለያዩ ምክንያቶች በጨዋታዎች ላይ ያልተገኙባቸው አጋጣሚዎች የተበራከቱ ነበሩ። ይህም በመሆኑ ህልውናው በአመዛኙ በመጀመሪያዎቹ ምርጥ 11ዎች ላይ የተጣለው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተጨዋቾች ከመሀል በሚጎድሉበት ጊዜ የነሱን ቦታ በሚገባ የሚሸፍኑ ልምድ ያላቸው እና በእድሜ ያልገፉ ተጨዋቾችን መያዝ ባለመቻሉ የጣላቸው ነጥቦች በርካታ ናቸው። በነዚህ ጊዜያት ሀላፊነት የተጫነባቸው ወጣት ተጨዋቾችም ለቡድኑ የረዥም ጊዜ ተተኪ የመሆን እና ቀስ በቀስ ልምድ እያካበቱ እንደተጨዋች የማደግ እንጂ በድንገት የክለቡን ዋና ተጨዋቾች ቦታ የመሸፈን ደረጃ ላይ ባለመድረሳቸው የአቅማቸውን ቢሞክሩም ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ወደተሻለ ውጤት ማምጣት ከብዷቸው ታይቷል፡፡

ቡድኑ በሜዳ ላይ በሚያሳየው አቋም በሁሉም የቡድኑ ክፍሎች ላይ ድክመት ይታይበታል። ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያስተናገደው የጎል መጠን (24) ከሁሉም የሊጉ ክለቦች በላይ ብዙ ግብ የተቆጠረበት ክለብ ያደርገዋል። ይህም በስፋት ከተናጠል የተከላከይ መስመር ተስላፊዎች በሚሰሩት ስህተት እና እርስ በእርስ ከነበራቸው ደካማ ጥምረት ምክንያት የተፈጠረ ነው። በተለይ ክለቡ 11 ግቦችን ባስተናገደባቸው የመጨራሻ ሶስት ጨዋታዎች ላይ እነዚህ ችግሮቹ ጎልተው ወጥተዋል። ከዚህ ሌላም በጉዳት ምክንያት ብዙ ጨዋታዎች ያመለጡትን የተከላካይ አማካዩ የጂብሪል አህመድ ቦታ በአግባቡ አለመሸፈኑ ሌላው ምክንያት ነው። ይህን ቦታ ሊሸፍን የሚችለው ታድዮስ ወልዴም ወደፊት ገፍቶ እንዲጫወት በተሰጠው ሚና ምክንያት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከአማካይ መስመሩ ሊያገኝ የሚገባውን በቂ የመከላከል ሽፋን አሳጥቶታል።

በብዙ ጨዋታዎች ላይ ለብቻው ተነጥሎ የሚታየው የአጥቂ ክፍልም በቂ ግቦችን እያመረተ አይገኝም። ይህም የቡድኑን የማጥቃት አጨዋወትን ጥያቄ ውስጥ ይከተዋል። የውህደት ችግር የሚስተዋልበት እና ከመስመር ተከላካዮች በቂ የማጥቃት እገዛ የማይደረግለት የአማካይ ክፍልም የግብ እድሎችን ለመፍጠር ሲቸገር ይስተዋላል። የቡድኑ ዋነኛ ባለተሰጥኦ ተጨዋች ቢኒያም በላይ የመስመር ተጨዋችነት ሚናም ተጨዋቹ በነፃነት ያለውን ቴክኒካዊ ችሎታ በመጠቀም የማጥቃት አጨዋወቱን ይበልጥ እንዳያግዝ አድርጎታል። በጥቅሉ የአማካይ መስመሩ በተደራጀ እና በጠራ የማጥቃት አጨዋወት የግብ እድሎችን እየፈጠረ እና ግብም እያስቆጠረ አይገኝም። የፊት መስመር ተሰላፊው ፒተር ንዋድኬም በአየር ላይ ኳሶች ባለው የተክለሰውነት ግዝፈት በመጠቀም ግቦችን እንዲያስቆጥር ከማድረግ ይልቅ ተጨዋቹ ከማጥቃት ወረዳው እየራቀ ወደ መስመር እና የመሀል አማካይምች ቀርቦ እንዲጫወት መደረጉ ሌላው የቡድኑ የማጥቃት ዕቅዱ ድክመት ነው።

በሁለተኛው ዙር ምን ይጠበቃል?

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከጥቂት ቀናት በፊት ዋና አሰልጣኙን ፀጋዬ ኪ/ማርያምን ማሰናበቱ የሚታወስ ነው። ይህ ፅሁፍ እስከቀረበበት ቀን እና ሰዐትም ክለቡ የአዲስ አሰልጣኝ ቅጥርን ይፋ አላደረገም። ቡድኑ የቀድሞውን የኢትዮጵያ ቡና እና አዳማ ከተማ አጥቂ ናይጄሪያዊውን አቢኮይ ሻኪሩን ከማስፈረሙ ውጪም ሌላ ተጨዋች ባለመግዛቱ ሁለተኛውን ዙር በተመሳሳይ የተጨዋቾች ስብስብ እንደሚቀጥል ይገመታል። ይህም በመሆኑ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሁለተኛው ዙር የተጎዱ ተጨዋቾቹን በቶሎ መመለስ እና ከወጣት ተጨዋቾቹም የመጨረሻውን አገልግሎት ማግኘት ካልቻለ አዲስ ከሚመጣው አሰልጣኝ ጋር የሚኖረውን የሽግግር ጊዜ አልፎ ከሌሎች ላለመውረድ ከሚጫወቱ ክለቦች ጋር  በሊጉ ለመቆየት የሚያደርገው ትንቅንቅ ቀላል የሚሆንለት አይመስልም።

የቡድኑ የመጀመሪያ ዙር ኮከብ ተጨዋች –  ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን

የቀድሞው የሐረር ሲቲ እና የኢትዮ ኤሌክትሪክ የመስመር አማካይ ዘንድሮ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተደጋጋሚ ጉዳት ሳቢያ ሙሉ አገልግሎት መስጠት ካልቻሉ የቡድኑ ቁልፍ ተጨዋቾች መሀል አንዱ ነው። ያም ሆኖ ፍቅረየሱስ በተሰለፈባቸው ጨዋታዎች ላይ በቡድኑ ውስጥ ያለው ተሳትፎ ከፍተኛ ነው። ለአጠቃላይ የቡድኑ የማጥቃት አጨዋወትም ከቀኝ መስመር በመነሳት የሚያደርገው እንቅስቃሴ ለንግድ ባንክ የፊት መስመር የተሻለ ጥንካሬ ሲያላብሰው ይስተዋላል። ፍቅረየሱስ በውድድሩ አጋማሽ ለመጫወት በበቃባቸው ጨዋታዎች ሶስት ግቦችን ሲያስቆጥር በሌሎቹ የቡድኑ ግቦችም ላይ ተሳትፎ አድርጓል።

ተስፋ ሰጪ ተጨዋች – ሳሙኤል ዮሀንስ

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ውስጥ ይታይ በነበረውን ተደጋጋሚ ጉዳት ሳቢያ የመጫወት  ዕድል ካገኙ ተጨዋቾች መሀከል ሳሙኤል ዮሀንስ አንዱ ነው ። አምና ከንግድ ባንክ ተስፋ ቡድን ዋናውን ቡድን መቀላቀል የቻለው ሳሙኤል ዘንድሮ መሰለፍ በቻለባቸው ጨዋታዎች በአማካይ መስመሩ ላይ ያሳየው አቋም በመጪዎቹ ጊዜዎች ቡድኑ ያለበትን ክፍተት ለመቅረፍ ተስፋ የሚጥልበት አይነት ነው

Leave a Reply