ኡመድ ኡኩሪ ዛማሌክ ላይ የሊግ ግብ አስቆጥሯል

የግብፅ ፕሪምየር ሊግ ከአንድ ወር እረፍት በኃላ በሳምንቱ አጋማሽ በተደረጉ ጨዋታዎች ሲጀመር ኤል ኤንታግ ኤል ሃርቢ ባልተጠበቀ መልኩ ዛማሌክን ከሜዳው ውጪ 2-1 አሸንፏል፡፡

ባሳለፍነው ሳምንት የምንግዜም ባላንጣውን አል አሃሊን አቡዳቢ ላይ በመለያ ምት አሸንፎ የግብፅ ሱፐር ካፕን ላሸነፈው ዛማሌክ ያልተጠበቀ ሽንፈት ነው፡፡

በፔትሮስፖርት ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ኤል ኤንታግ በኡመድ ኡኩሪ ግብ በ22ኛው ደቂቃ መምራት ሲችል ታሪክ ጠሃ አብደልሃሚድ በ35ኛው ደቂቃ የኤል ኤንታግን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ አድርጓል፡፡ ዛማሌኮች በጥር ወር ከሰሞሃ ክለቡን በተቀላቀለው አንጋፋው አጥቂ ሆሳም ፓውሎ የ44ኛው ደቂቃ ግብ ልየነትቱን ወደ አንድ ማጥበብ ችለው ነበር፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ ግብ ሳይሰተናገድበት ከግብፅ ዋንጫ በኤል መስሪ ተሸንፎ ከውድድር ለወጣው ኤል ኤንታግ ኤል ሃርቢ ጣፋጭ ድል ሆኖለታል፡፡ በሻውኪ ጋርብ የሚመራው ኤል ሃርቢ በደረጃ ሰንጠረዡ በ20 ነጥብ 12ኛ ሆኗል፡፡

በጨዋታው ድንቅ እንቅስቃሴ ያሳየው ኡመድ የጨዋታው ኮከብ ተብሎ በግብፁ የእግርኳስ ቁጥራዊ መረጃን በሚያቀርበው አቅራም ድህረ-ገፅ ተመጧል፡፡ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ኡመድ ለሶከር ኢትዮጵያ ባሳየው እቅስቃሴ ደስተኛ መሆኑን ተናግሯል፡፡ “ባሳየሁት እንቅስቃሴ እና ግብ በማስቆጠሬ ተደስቻለው፡፡ የጨዋታው ኮከብ ተብዬ መመረጤ ይበልጥ ደስታዬን ከፍ አድርጎታል” ብሏል የቀድሞ የመከላከያ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ የፊት መስመር ተሰላፊ፡፡

የግብፅ ፐሪምየር ሊግን አሁን አል አሃሊ በ46 ነጥብ ይመራል፡፡ የካይሮው ሃያል ትላንት ከተከታዮቹ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ማስፋት የሚችልበትን እድል አግኝቶ ኤስማኤሊ ጋር ያለግብ አቻ በመለያየቱ ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡ ከታንታ ጋር ያለግብ አቻ የተለያየው ምስር ኤል ማቃሳ በ41 ነጥብ ሁለተኛ ሲሆን ዛማሌክ በ34 ነጥብ ሶስተኛ ነው፡፡

 

የኡመድን ግብ ለመመልከት ይህንን ሊንክ ይከተሉ

https://youtu.be/E7C7PIhK4qE
 

Leave a Reply