የፕሪምየር ሊግ 1ኛ ዙር የክለቦች ዳሰሳ – አዳማ ከተማ

ሶከር ኢትዮጵያ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመርያ ዙር መጠናቀቅን ተከትሎ ክለቦችን በተናጠል በመዳሰስ ላይ ትገኛለች፡፡ አብርሃም ገብረማርያም እና ሚልኪያስ አበራ አንደኛውን ዙር በ4ኛ ደረጃ ያጠናቀቀው አዳማ ከተማ የውድድር ዘመን አጋማሽ ጉዞ እንዲህ ዳሰውታል፡፡

የመጀመሪያ ዙር የአዳማ ከተማ ጉዞ

አዳማ ከተማ በርካታ አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ቡድኑ ቀላቅሎ የውድድር አመቱን ጀምሯል፡፡ የመጀመርያዎቹን ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች በሜዳው አድርጎ በማሸነፍ ምርጥ አጀማመር ያደረገው አዳማ በ3ኛው ሳምንት ወደ ሶዶ ተጉዞ በወላይታ ድቻ የመጀመርያ ሽንፈቱን አስተናግዷል፡፡ በተከታታይ 2 ጨዋታዎችን በአቻ ውጤት ካጠናቀቀ በኋላ በተከታታይ ጨዋታዎች ወደ ድል ተመልሶ የሊጉን መሪነት እስከመጨበጥ ቢደርስም በመጀመርያው ዙር የመጨረሻዎቹ ጨዋታዎች በተደጋጋሚ የጣላቸው ነጥቦች በ4ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ 1ኛውን ዙር እንዲጨርስ አስገድዶታል፡፡

አዳማ ከያዘው ስብስብ አንጻር የሊጉን ዋንጫ ያነሳሉ ተብለው ከሚገመቱ ቡድኖች አንዱ ቢሆንም ከሜዳው ውጪ ለማሸነፍ እና ግቦች ለማስቆጠር ሲቸገር እንዲሁም ወጥ አቋም ማሳየት ሲቸገር ተስተውሏል፡፡

 የቡድኑ ውጤት ከአምናው ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነፃፀር

አዳማ ከተማ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ተመሳሳይ የሆነ አማካይ ነጥብ (በአማካይ በጨዋታ 1.7 ነጥብ) ቢያስመዘግብም ግብ በማስቆጠር በኩል የዘንድሮው ዝቅተኛ ሆኗል፡፡ አምና በ1ኛው ዙር በአማካይ በጨዋታ 1.4 ጎሎች ያስቆጠረው አዳማ በዚህ አመት በግማሽ አሽቆልቁሏል፡፡

ቡድኑ ከአምናው ጎል በማስቆጠር በእጥፍ ዝቅ ቢልም በተቃራኒው የመከላከል ሪከርዱን በእጥፍ አሻሽሏል፡፡ በ2008 አንደኛ ዙር በ13 ጨዋታ 14 ጎል የተቆጠረበት ቡድን ዘንድሮ በ15 ጨዋታ የተቆጠረበት 7 ብቻ ነው፡፡

የመጀመሪያው ዙር የቡድኑ አቀራረብ

የአሸናፊ በቀለ አዳማ ከተማ አመዛኙን የመጀመርያ ዙር በ4-3-3 የጨዋታ አቀራረብ ተመልክተነዋል፡፡ የአማካይ መስመሩ መደበኛ የሶስት ማዕዘን ቅርፅ የሚኖረው ሲሆን ከብሩክ ቃልቦሬ ፊት ፋሲካ አስፋው እና አዲስ ህንፃ (ጥላሁን ወልዴ) ይሰለፋሉ፡፡  አሰልጣኝ አሸናፊ በፊት መስመሩ ላይ ሚካኤል ጆርጅ ፣ ሙጂብ ቃሲም እና ዳዋ ሁቴሳን ይጠቀማል፡፡ ወደ መጨረሻዎቹ ጨዋታዎች ደግሞ ቡልቻ የሙጂብን ቦታ ሸፍኖ ሲጫወት ተመልክተነዋል፡፡ ቡድኑ 3 ተመሳሳይ ባህርይ ያላቸው አጥቂዎችን ከፊት ሲጠቀም በተደጋጋሚ ይስተዋላል፡፡

አሰልጣኝ አሸናፊ ከ4-3-3 በተጨማሪ በአንዳንድ ጨዋታዎች ላይ 3-5-2ን ሲጠቀሙ ታይተዋል፡፡ ይህ አደራደር ካላቸው የተጫዋች ስብስብ ጋር የሚጣጣም ቢሆንም ብዙም ሲጠቀሙበት አልታየም፡፡

ጠንካራ ጎን

የተከላካይ መስመሩ የቡድኑ ጠንካራ ጎን ነው፡፡ አዳማ ተጋጣሚዎቹን በጠባብ የግብ ልዩነት የሚያሸንፈው በቀላሉ ግብ የማያስተናግድ በመሆኑ ነው፡፡ ከአንድ ጎል በላይ ያስተናገደው በአንድ ጨዋታ ላይ ብቻ ሲሆን 9 ጨዋታዎች ላይ ግብ አላስተናገደም፡፡ የተስፋዬ በቀለ እና ምኞት ደበበ ጥምረት ከሊጉ የዘንድሮ ጥምረቶች ምርጥ የሚባል እና ወጥ አቋም የሚያሳይ ነው፡፡ ሁለቱም በአካል ብቃት የተሟሉ ፣ አንድ ለአንድ ግንኙነት ላይ ጠንካራ እና 50/50 ኳሶችን በበላይነት የሚወጡ ናቸው፡፡

የሜዳ አድቫንቴጅ መጠቀም የአዳማ ጠንካራ ጎን ነው፡፡ ዘንድሮ በአበበ ቢቂላ ካደረጋቸው 8 ጨዋታዎች ማግኘት ካለበት 24 ነጥብ 20 ነጥቦችን ማሳካት ችሏል፡፡ በአጠቃላይ ከሰበሰበው ነጥብ 76% ያሳካውም በሜዳው ነው፡፡

አዳማ በሚቸገርባቸውና አሳማኝ እንቅስቃሴ በማያሳይባቸው ጨዋታዎች ላይ ነጥብ ይዞ የመውጣት ልምዱ እንደጠንካራ ጎን ሊወሰድ ይገባል፡፡ ይህም ቡድኑ በ2ኛው ዙር በምርጥ አቋሙ ላይ የሚገኝ ከሆነ በርካታ ነጥብ መሰብሰብ እንደሚችል ያመለክታል፡፡

ደካማ ጎን

አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ የሚመርጡት የጨዋታ አቀራረብ እና የሚያሰልፏቸው ተጫዋቾች አለመጣጣም ቡድኑ እንዲቸገር አድርጎታል፡፡ በተለይም በአጥቂ መስመር ላይ የሚሰለፉ ተጫዋቾች ተመሳሳይ የአጨዋወት ባህርይ በመያዛቸው አንድ ቦታ ላይ ተጠጋግተው እንዲጫወቱ እና በተጋጣሚ ተከላካዮች ቁጥጥር ስር በቀላሉ እንዲወድቁ አድርጓቸዋል፡፡ እንደ አጥቂ መስመሩ ሁሉ የአማካይ ስፍራ ላይም ተመሳሳይ ባህርይ ያላቸው አማካዮችን ሲያጣምሩ ታይቷል፡፡ ይህም ቡድኑ ኳስ እንዳይቆጣጠር እና ከአጥቂ መስመሩ ጋር እንዳይግባባ አድርጎታል፡፡

ወጥ የሆነ የተጫዋቾች ምርጫ እና ሚና አሰጣጥ ላይም አሰልጣኝ አሸናፊ የወሰዱት እርምጃ እንደ ድክመት መጠቀስ ይኖርበታል፡፡ አሰልጣኙ አስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ ባይገቡም የተጫዋቾችን ሚና በተደጋጋሚ ሲቀያይሩ ተመልክተናል፡፡

የተጫዋቾች የተናጠል ብቃት መውረድም ቡድኑ የተጠበቀውን ያህል እንዳይጓዝ ካደረጉት ደካማ ጎኖች አንዱ ነው፡፡ ከመሀል ተከላካይ ስፍራ ተጫዋቾቹ በቀር በወጥ አቋም የተጫወተ ተጫዋች በቡድኑ ውስጥ ማግኘት ይቸግራል፡፡

ቡድኑ ከሜዳ ውጪ የሚያሳየው እንቅስቃሴም ሆነ የሚያስመዘግበው ውጤት መልካም አይደለም፡፡ አዳማ ከሜዳው ሙሉ ለሙሉ የመከላከል አቀራረብ ይዞ የሚገባ ሲሆን ጎል የማስቆጠር እና የማሸነፍ ፍላጎት የማይታይበት ቡድን ነው፡፡ ከ7 ጨዋታ ያስመዘገበው 6 ነጥብ ብቻ መሆኑ ለዋንጫው እንደሚፎካከር ቡድን በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡

በሁለተኛው ዙር ምን ይጠበቃል?

አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ የብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆነው የሚሾሙ ከሆነ ቡድኑ ሊቸገር ይችላል፡፡ አሸናፊ ያለፉትን 3 አመታት በራሳቸው መንገድ የገነቡትን ቡድን ከለቀቁ ቡድኑ ከተፎካካሪነት ይልቅ ወደ ሽግግር የሚያመራ ይሆናል፡፡

በሁለተኛው ዙር ከክለቡ ተጫዋቾች የአቋም መሻሻል ይጠበቃል፡፡ አሰልጣኙም የተጫዋቾቹን ምርጥ ብቃት የሚያወጣ አጨዋወት መተግበር ይጠበቅባቸዋል፡፡

ቡድኑ ከመሪው በ3 ነጥብ ብቻ ከመራቁ በተጨማሪ ልምድ ያላቸው ፣ ወጣቶች እና በጥሩ አቋም ላይ የሚገኙ ተጫዋቾች ስብጥር በስብስቡ በመያዙ በሊጉ ከፍ ያለ ደረጃ ይዞ የማጠናቀቅ አቅም አለው፡፡

የቡድኑ መጀመርያው ዙር ኮከብ ተጫዋች – ተስፋዬ በቀለ

ተስፋዬ በቀለ የቡድኑ የተከላካይ መስመር መሪ ነው፡፡ ሱሌይማን መሀመድ በጉዳት በርካታ ጨዋታዎች አለማድረጉን ተከትሎም ቡድኑን በአምበልነት እየመራ ይገኛል፡፡

ጠንካራው ተከላካይ ከምኞት ደበበ ጋር የፈጠረው ጥምረት ቡድኑ በ9 ጨዋታዎች ላይ ግብ ሳያስተናግድ እንዲወጣ አድርጓታል፡፡

ተስፋ የሚጣልበት ተጫዋች – ሱራፌል ዳኛቸው

አምና ወደ ዋናው ቡድን ያደገው ሱራፌል ዘንድሮ የተሻለ የመሰለፍ እድል እያገኘ ይገኛል፡፡ በአንዳንድ ጨዋታዎች ላይም የወደፊቱ የኢትዮጵያ እግርኳስ ኮከብ እንደሚሆን ፍንጭ የሚሰጥ ድንቅ አቋም አሳይቷል፡፡ በሁለተኛው ዙር የቋሚነት ተሰላፊነት እድል ካገኘ ቡድኑ ያለበትን የግብ እድል የመፍጠር ችግር የመቅረፍ እና ተጽእኖ መፍጠር አቅም አለው፡፡

Leave a Reply