የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 1ኛ ዙር የክለቦች ዳሰሳ – ኢትዮጵያ ቡና

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመርያ ዙር መጠናቀቅን ተከትሎ ሶከር ኢትዮጵያ ክለቦችን በተናጠል በመዳሰስ ላይ ትገኛለች፡፡ አንደኛውን ዙር በ6ኛ ደረጃ ያጠናቀቀው ኢትዮጵያ ቡና የውድድር ዘመን አጋማሽ ጉዞ በአብርሃም ገብረማርያም እና ሚልኪያስ አበራ እንዲህ ተዳሷል፡፡

የመጀመርያ ዙር ጉዞ

ኢትዮጵያ ቡና በ2008 የነበረውን ድንቅ የ2ኛ ዙር ጉዞ ተከትሎ በ2009 ከደጋፊዎቹ ብዙ ቢጠበቅበትም የሊግ አጀማመሩ አስከፊ የሚባል ነበር፡፡  በደደቢት 3-0 ተሸንፎ የጀመረው ቡና ከመከላከያ አቻ ተለያይቶ በፋሲል በሜዳው ተሸንፎ ከአዳማ አቻ ተለያይቶ በህዳር ወር መጥፎ ጊዜ አሳልፏል፡፡ በታህሳስ ወር ባላንጣው ቅዱስ ጊዮርጊስን ቢያሸንፍም ካደረጋቸው 5 ጨዋታዎች ማግኘት የቻለው 8 ነጥብ ብቻ ነው፡፡ በተለይ ወደ መልካ ቆሌ አምርቶ በወልድያ 1-0 መሸነፉ ሰርቢያዊ አሰልጣኝ ኔቦሳ ቪቼቪችን ከመንበራቸው እንዲነሱ አድርጓቸዋል፡፡

የቡና የውድድር ዘመኑ ለውጥ የጀመረው በጥር ወር መጀመርያ ኔቦሳ ተሰናብተው ገዛኸኝ ከተማ እና እድሉ ደረጀ ቡድኑን በጊዜያዊነት ከተረከቡ በኋላ ነው፡፡ ቡድኑ በወሩ ባደረጋቸው 6 ጨዋታዎች 4 አሸንፎ በሁለቱ አቻ በመለያየት ከፍተኛ የውጤት መሻሻል ማሳየት ችሏል፡፡ ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ያለው የነጥብ ልዩነትም ወደ 5 አጥብቦ 1ኛውን ዙር በ6ኛ ደረጃ ላይ ማጠናቀቅ ችሏል፡፡

ቡድኑ ከአምናው ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነጻጸር

ኢትዮጵያ ቡና በ2008 የውድድር ዘመን አንደኛው ዙር እጅግ ደካማ ደረጃ ላይ ሆኖ ነበር ያጠናቀቀው፡፡ ከ13 ጨዋታዎች 15 ነጥብ ብቻ (በአማካይ በጨዋታ 1.1 ነጥብ) አሳክቶ 11ኛ ደረጃ ላይ የነበረ ሲሆን ዘንድሮ 23 ነጥብ (በአማካይ በጨዋታ 1.5  ነጥብ) ሰብስቦ 6ኛ ላይ ተቀምጧል፡፡ በግብ ማስቆጠር ረገድም የዘንድሮው 18 ጎሎች (1.2 ጎል/ጨዋታ)  ከአምናው 12 ጎል (0.9 ጎል/ጨዋታ)የተሻለ ነው፡፡ በመከላከል ሪኮርዱም አምና 14 ጎል (1 ጎል/ጨዋታ) የተቆጠረበት ቡና ዘንድሮ በጥቂቱ አሻሽሎ 13 ጎል (0.8 ጎል/ጨዋታ) ተቆጥሮበታል፡፡ በአጠቃላይ ቡድኑ በሁሉም ረገድ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የተሻለ ነው፡፡

የቡድኑ አቀራረብ

ኢትዮጵያ ቡና በአሰልጣኝ ኔቦሻ ቪቼቪችም ሆነ ገዛኸኝ ከተማ ስር ተመሳሳይ 4-3-3 የተጫዋቾች የሜዳ ላይ አደራደርን በዋነኝነት ተጠቅሟል፡፡ በአንዳንድ አጋጣሚዎች ደግሞ በ4-1-4-1 ሲጠቀሙ ተስተውሏል፡፡

በአማካይ መስመሩ ላይ ጋቶች ፓኖም ፣ አማኑኤል ዮሃንስ እና ኤልያስ ማሞ በአብዛኛው ጨዋታዎች ላይ ተጣምረዋል፡፡ ጋቶች የተከላካይ አማካይነቱን ሚና ሲወጣ አማኑኤል ከሳጥን ሳጥን ፣ ኤልያስ ደግሞ የጨዋታ አቀጣጣይነቱን ሚና ይወጣሉ፡፡

በአጥቂ መስመር እያሱ ታምሩ እና አስቻለው ግርማ በመስመር ፣ ያቡን/ሳኑሚ ደግሞ በመሀል አጥቂነት ይሰለፋሉ፡፡ ታታሪው እያሱ የመከላከል እና የማጥቃት እንቅስቃሴውን በሚዛናዊነት ሲወጣ አስቻለው ከግራ መስመር ወደ ውስጥ በማጥበብ አደጋ ይፈጥራል፡፡

የቡድኑ አጨዋወት የመስመር ተከላካዮቹ እንዲያጠቁ ነጻነት የሚሰጣቸው ቢሆንም አህመድ እና አብዱልከሪም በጉዳት በርካታ ጨዋታ ላይ አለመሰለፋቸው ቡድኑ የተሟላ እንዳይሆን አድርጎታል፡፡

ጠንካራ ጎን

የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች የቡድኑ የጀርባ አጥንት መሆናቸውን ዘንድሮም አስመስክረዋል፡፡ የቡድኑ ፅንፈኛ ደጋፊዎች ሳይቀሩ ውጤት በጠፋበትና አወዛጋቢ የዳኝነት ውሳኔዎች በነበሩበት ወቅት ያሳዩት ትዕግስት ቡድኑ ውጤቱን እንዲያሻሽል ረድቶታል፡፡ ከዚህ ቀደም የክለቡን ስም በመጥፎ እንዲጠራ ሲያደርግ የነበረው የደጋፊዎች ስርአት አልበኝነትም ዘንድሮ መቀረፉ በግልጽ ታይቷል፡፡

የዘንድሮው ኢትዮጵያ ቡና ጠንካራ ጎን እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ የአማካይ ስፍራው ነው፡፡ ቡድኑ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት የሚወስዱ እና በቀላሉ የግብ እድል መፍጠር የሚችሉ አማካዮች ባለቤት ነው፡፡ ከተከላካይ አማካዩ ፊት የሚሰለፉት ሁለቱ አማካዮች በሜዳው ቁመትም ሆነ ስፋት የማጥቃት አማራጭ የመፍጠር ብቃታቸው መልካም ነው፡፡ አማካዮቹ ከመስመር አጥቂዎቹ ጋር ያለቸው መግባባትም ቡድኑ በተቃራኒ ሜዳ ላይ የበላይ እንዲሆን አስችሎታል፡፡

የመስመር አጥቂዎቹ ሚዛናዊ እንቅስቃሴ የቡድኑ ሌላኛው ጠንካራ ጎን ነው፡፡ አስቻለው ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ በማድረግ እና ከመስመር ወደ ውስጥ በመግባት አደጋ ሲፈጥር እያሱ ታምሩ ደግሞ ቡድኑ ኳስ ሲያጣ ወደ መሀለኛው የሜዳ ክፍል እና ወደ ኀላ በማፈግፈግ እንዲሁም ኳስ ከኋላ እንዳይመሰረት በመጫን ስኬታማ የመከላከል ተግባር ሲፈጽም ተስተውሏል፡፡

ቡና ዘንድሮ ሜዳ ውጪ ያስመዘገበው ውጤት መልካም ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ወደ ክልል ሲወጣ የሚቸገረው ቡና በውጤትም በአጨዋወትም ተሻሽሎ ቀርቧል፡፡ ካደረጋቸው 5 ጨዋታዎችም የተሸነፈው 1 ብቻ ነው፡፡

ደካማ ጎኖች

የቡና የተከላካይ መስመር የቡድኑ ደካማ ጎን ነው፡፡ ሀሪሰን ሄሱ እንደሚያድናቸው ኳሶች ባይሆን ኖሮ ቡድኑ በርካታ ግቦች ሊያስተናግድ ይችል ነበር፡፡ ለዚህ እንደ ምክንያት የሚቀመጠው ከኤፍሬም ወንድወሰን ውጪ ያሉት ቋሚ ተከላካዮች በጉዳት የሚጠበቀውን ያህል አለመሰለፋቸው በተከላካይ ክፍሉ ላይ መረጋጋት እንዳይኖር አድርጎታል፡፡ ነገር ግን በጉዳት ከአሰላለፍ የሚወጡ ተጫዋችችን የሚተኩ ተጫዋቾች ዝግጁ እንደዲሆኑ አለማድረግ የቡድኑ ደካማ ጎን ነው፡፡

የአጥቂዎቹ የግብ እድሎችን የመጨረስ ብቃት ማነስ ቡድኑን ዋጋ ሲያስከፍለው በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ ያቡን ዊልያም ሁነኛ የሳጥን አጥቂ ባህርይ የሌለው ሲሆን ሳሙኤል ሳኑሚ ከቡድኑ ጋር ለመዋሃድ ወራት ፈጅቶበታል፡፡ አስቻለው በሌለባቸው ጨዋታዎች ላይ በመስመር አጥቂነት መሰለፉም የሚጠበቅበትን ያህል እንዳያበረክት አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ሳዲቅ ሴቾም የቡድኑ ደጋፊዎች የሚተማመኑበት አይነት ተጫዋች መሆን አልቻለም፡፡


በሁለተኛው ዙር ከቡድኑ ምን ይጠበቃል?
ኢትዮጵያ ቡና ከሚሌንየሙ መጀመርያ ወዲህ ቀዝቃዛ አጀማመር በማድረግ ቀስ በቀስ ወደ ምርጥ አቋም መምጣትን ልምድ አድርጎታል፡፡ ዘንድሮ ከአናት ያሉት ክለቦች ሳይርቁት አቋሙን በማስተካከሉ በ2ኛው ዙር ለሊጉ ክብር ተፎካካሪ ከሚሆኑ ክለቦች አንዱ ሊሆን ይችላል፡፡ የቡድኑ ወሳኝ የማጥቃት መሳርያ የሆኑት አህመድ ረሺድ እና አብዱልከሪም ከጉዳት ነጻ ከሆኑም ቡድኑ የሚፈልገውን የማሳካት የሚችልበት አቅም አለው፡፡

በዝውውር መስኮቱ ጋናዊው ሳሙኤል ኩጆን ያስፈረመው ቡና የተከላካይ መስመሩንም አጠናክሯል፡፡


የ1ኛ ዙር ኮከብ ተጫዋች – ሀሪሰን ሄሱ

ቤኒናዊው ግብ ጠባቂ ክለቡ ውጤት ባጣበትም ሆነ በተሻሻለበት ወቅት ወጥ የሆነ ብቃቱን ማሳየት ችሏል፡፡ በተለይም በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የሚያድናቸው ኳሶች ቡድኑ ቢያንስ አንድ ነጥብ ይዞ እንዲወጣ ወሳኝ ነበሩ፡፡

ተስፋ የሚጣልበት ተጫዋች – እሱባለው ጌታቸው

ከ17 አመት በታች ቡድኑ ዘንድሮ ያደገው እሱባለው የጥቂት ደቂቃዎች እድል ብቻ ነው ያገኘው፡፡ ምርጥ እይታ እና ኳስ የማደራጀት ችሎታ ከቴክኒክ ክህሎት ጋር ያጣመረው እሱባለው በሁለተኛው ዙር የመጫወት እድል ካገኘ ክስተት የመሆን አቅም አለው፡፡

Leave a Reply