በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ጅማ አባ ጅፋር እና መከላከያ ወደ ግማሽ ፍፃሜ አልፈዋል

የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የምድብ አንድ ሁለተኛ ጨዋታዎች ዛሬ ሲደረጉ ኢትዮጵያ ቡና እና አዲስ አበባ ከተማ ተጋጣሚዎቻቸው በነበሩት መከላከያ እና ጅማ አባ ጅፋር ተረተው ከምድብ ወድቀዋል።

ጅማ አባጅፋር 1-0 አዲስ አበባ ከተማ (8:00)

እጅግ የወረደ ፉክክር ያስመለከተው የዕለቱ የመጀመሪያ መርሐ-ግብር ከግብ ሙከራዎች የራቀ ነበር። ጨዋታውም የጠራ የግብ ማግባት ሙከራ ለማስመልከት 33 ደቂቃዎች ፈጅተውበታል። በተጠቀሰው ደቂቃም አዲስ አበባ ከተማዎች ከመስመር ባሻገሩት እና እንዳለ ከበደ በግንባሩ በሞከረው ኳስ መሪ ሊሆኑ ነበር።

ቶሎ ቶሎ ኳስ መነጣጠቆች ባዘነበሉበት ጨዋታ ላይም መሐል ሜዳ ላይ የተገደበ እንቅስቃሴ በአብዛኛው ሲታይ ነበር። በአንፃራዊነት ግን የጅማ አባ ጅፋር ተጫዋቾች በተሻለ ወደ ግብ ለመድረስ ሲጥሩ ተስተውሏል። የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረው እጅግ በጥሩ የኳስ ቅብብል ወደ አዲስ አበባ የግብ ክልል ያመሩት ጅማ አባ ጅፋሮች መሪ የሆኑበትን ጎል አግኝተዋል። በዚህ ቡድኑ በጥሩ የአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ሳጥን ይዞት የሄደውን ኳስ መጨረሻ ላይ መሐመድኑር ናስር አግኝቶት ወደ ግብ ቀይሮታል።

ለዐይን ሳቢ ያልነበረው ጨዋታው በሁለተኛው አጋማሽም እንደ መጀመሪያው ግማሽ ሙከራዎች አልነበሩትም። በአንፃራዊነት ግን አዲስ አበባ ከተማዎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ
በ55ኛው ደቂቃ ላይ ሪችሞንድ አዶንጎ ከመሐል የተሻገረውን ኳስ ከተከላካይ ጋር ታግሎ ሲሞክር አቻ ሊሆኑ ነበር። ከአስር ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ቢኒያም ጌታቸው ሌላ ጥቃት ፈፅሞ ነበር።

መሪነታቸውን ለማስጠበቅ የተንቀሳቀሱት ጅማ አባ ጅፋሮች በበኩላቸው ለመከላከል ቅድሚያ ሰጥተው ሲጫወቱ የነበረ ቢሆንም በ66ኛው ደቂቃ ተቀይሮ ወደ ሜዳ በገባው ሱራፌል ዐወል አማካኝነት መሪነታቸውን ወደ ሁለት ሊያሳድጉ ነበር። ሙሉ የጨዋታው ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በተጨመረው ደቂቃ ከጨዋታው ነጥብ ይዞ ለመውጣት የመጨረሻ ዕድል ያገኙት አዲስ አበባዎች በመልሶ ማጥቃት የተገኘን ኳስ ተቀይሮ ወደ ሜዳ በገባው ብሩክ ግርማ አማካኝነት ወደ ግብ ቢልኩትም ሳይሳካላቸው ቀርቷል። ጨዋታውንም በመሐመድኑር ናስር ብቸኛ ጎል ጅማ አባጅፋር አሸንፏል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ኮከብ ተጫዋች ተብሎ የተመረጠው የግቡ ባለቤት መሐመድኑር ናስር ከአቶ አሰፋ ክፍሌ ዋንጫ እና 12 ሺ ብር ሽልማት ተረክቧል።

መከላከያ 1-0 ኢትዮጵያ ቡና (10:00)

የዕለቱ ሁለተኛ መርሐ-ግብር የሆነውን የመከላከያ እና ኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ በርከት ያሉ ደጋፈዎች በስታዲየም ተገኝተው ተከታትለውታል። በጨዋታውም በፈጣን ሽግግር መጫወት የጀመሩት መከላከያዎች በ12ኛው ደቂቃ አኩዌር ቻሞ የቡና ተጫዋቾች የሰሩትን የቅብብል ስህተት ተጠቅሞ የመጀመሪያውን ሙከራ አድርጎ ነበር። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ከወደ ቀኝ ባዘነበለ ቦታ የቅጣት ምት ያገኘው ቡድኑ በቢኒያም በላይ አማካኝነት አጋጣሚውን ወደ ግብ ቢልከውም ፍሬያማ ሳይሆን ቀርቷል።

በተቃራኒው ኳሱን ለመቆጣጠር ያሰቡ የሚመስሉት ኢትዮጵያ ቡናዎች በራሳቸው ሜዳ ዘለግ ያለውን ጊዜ ሲያሳልፉ ነበር። ይህ ቢሆንም ግን እስከ 32ኛው ደቂቃ ድረስ አንድም የሰላ ጥቃት ሳይፈፅሙ ጨዋታውን መከወን ቀጥለዋል። ቡና በተጠቀሰው ደቂቃ የመጀመሪያ ሙከራውን ከማድረጉ በፊት ግን መከላከያ ሁለት ተከታታይ ጥቃት ፈፅሟል። በቅድሚያም ቢኒያም ከርቀት አክርሮ ወደ ግብ መትቶ ሲወጣበት በቀጣይ ደግሞ ልደቱ ጌታቸው ከመዓዘን የተሻገረውን ኳስ በግንባሩ ለማስቆጠር ጥሮ መክኖበታል።

ከላይ እንደተገለፀው ቡና አብዱልመጅድ ሁሴን ከመሐል የተሰነጠቀለትን የመሬት ለመሬት ኳስ ፈጥኖ በማግኘት ወደ ግብ በሞከረው አጋጣሚ የግብ ዘቡን ክሌመንት ቦዬ ፈትነዋል። አጋማሹ ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረው ደግሞ መከላከያ እየመራ ወደ እረፍት የሚያመራበትን ዕድል ፈጥሮ ሳይሳካለት ቀርቷል።

በሁለተኛው ግማሽ ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ ተነቃቅተው ወደ ሜዳ የገቡት ኢትዮጵያ ቡናዎች ግብ ለማስቆጠር ታትረው ቢንቀሳቀሱም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ ተስኗቸዋል። በአንፃሩ መከላከያዎች ደግሞ ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ተጠግተው ጨዋታውን ማከናወን ቀጥለዋል። በ62ኛው ደቂቃ ግን ቡድኑ በግራ መስመር ወደ ኢትዮጵያ ቡና የግብ ክልል በማምራት በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ በነበረው ቢኒያም በላይ አማካኝነት ግብ አስቆጥረው መሪ ሆነዋል።

በአጋማሹ እንደ አጀማመራቸው መዝለቅ ያልቻሉት ቡናዎች አከታትለው የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን ወደ ሜዳ ቢያስገቡም ኳስ እና መረብን የሚያገናኝላቸው ሁነኛ ተጫዋች አጥተዋል። በ77ኛው ደቂቃ ግን ቡድኑ በጥሩ የማጥቃት መናበብ ወደ ግብ ደርሰው አቻ ለመሆን ጥረው መክኖባቸዋል። በቀሪዎቹ ደቂቃዎችም ተጨማሪ የግብ ማግባት ሙከራዎች ሳይደረጉ ጨዋታው በመከላከያ አንድ ለምንም አሸናፊነት ተጠናቋል።

የጨዋታው ኮከብ ተብሎ ደግሞ ቢኒያም በላይ የተመረጠ ሲሆን ከአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ አስራት ኃይሌ (አሠልጣኝ) ዋንጫ እና የገንዘብ (12 ሺ) ሽልማቱን ተቀብሏል።

የዛሬዎቹን ሁለት ጨዋታዎች ውጤት ተከትሎም ድል የተቀዳጁት ጅማ አባ ጅፋር እና መከላከያ ቀሪ አንድ ጨዋታ እያላቸው ወደ ቀጣይ ዙር ማለፋቸውን አረጋግጠዋል። አዲስ አበባ እና ኢትዮጵያ ቡና ግን ከወዲሁ ያለ ምንም ነጥብ ከውድድሩ ውጪ መሆናቸው ታውቋል።

ያጋሩ