“በ1ኛው ዙር ቅር ያሰኘናቸው ደጋፊዎቻችንን በጥሩ ውጤት ለመካስ እየተዘጋጀን ነው” መሳይ ተፈሪ

ወላይታ ድቻ በአንደኛው ዙር የመጨረሻ ጨዋታዎች ያስመዘገበውን ውጤት ተከትሎ በደረጃ ሰንጠረዡ 10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ 1ኛውን ዙር አጠናቋል፡፡ አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ በቡድናቸው የአንደኛ ዙር አቋም እና ስለ ሁለተኛው ዙር ለዳዊት ጸሃዬ የነገሩትን በዚህ መልኩ አቅርበነዋል፡፡

የመጀመሪያ ዙር የቡድኑ ጉዞ

“ሊጉን ሁለት ጨዋታዎችን በሜዳችን በማሸነፍ በጥሩ ሁኔታ ነበር የጀመርነው፡፡ ነገርግን በ4ኛው ሳምንት ከሲዳማ ጋር ካደረግነው ጨዋታ ጀምሮ ተከታታይ እስከ ቅዱስ ጊዮርጊሱ ጨዋታ ድረስ ባደረግናቸው ጨዋታዎች ላይ ክፍተቶች ነበሩብን፡፡ ከዛም በኃላ በነበሩት ጨዋታዎች የተወሰኑ ለውጦችን አድርገን የመሻሻል ነገሮች ነበሩ፡፡ በመቀጠል በድጋሚ በ11ኛው ሳምንት በኤሌክትሪክ ከተሸነፍን በኃላ የነበሩት ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ጥሩ አልነበርንም፡፡ እንደ አጠቃላይ በመጀመሪያው ዙር ያደረግነው እንቅስቃሴ ደካማ የሚባል ነው፡፡”

የድቻ ከሜዳ ውጪ ድክመት ምክንያት

“በመጀመሪያው ዙር ከነበሩብን ድክመቶች አንዱ ከሜዳ ውጪ ያለን ሪከርድ ጥሩ አለመሆኑ ነው፡፡ በአንጻሩ በሜዳችን ያለን ሪከርድ ጥሩ የሚባል ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በነበሩት አመታት ከነበረን ሪከርድ በተለየ ከሜዳ ውጪ ነጥቦችን ለመያዝ ተቸግረናል፡፡ ለዚህም ዋንኛው ምክንያት ቡድናችን በመከላከሉም ሆነ በማጥቃቱ በኩል ሰፊ ክፍተቶች አሉበት ፤ ይህም ነጥብ ከመያዝ አግዶናል ብዬ አስባለሁ፡፡”

በመጀመሪያው ዙር የቡድኑ ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች

“ቡድኑ እንደአጠቃላይ በመከላከሉም ሆነ በማጥቃቱ ላይ ችግሮች አሉበት፡፡ በተለይም ቡድናችን በሚከላከልበት ወቅት በተደጋጋሚ ስህተቶችን እንሰራለን፡፡ ይህም በተደጋጋሚ ዋጋ አስከፍሎናል ፤ በተጨማሪም ቡድናችን እንደ ቡድን አንድ ሆኖ በመጫወት በኩል ክፍተቶች አሉበት፡፡ በተቃራኒው የቡድናችን ጠንካራ ጎን ብዬ የማስበው ከሌሎች ጊዜያት በተለየ በኛ ደረጃ ከሚገኙ ቡድኖች አንጻር ፊት መስመራችን ጥሩ ነው ፤ ግቦችን በማስቆጠር ረገድ ከሌላው ጊዜ በተሻለ ለውጦች አይተናል፡፡ ሌላው ደግሞ ሌሎች ቡድኖች ጋር በሌለ መልኩ በተጫዋቾች መካከል ያለው የአንድነት መንፈስ እና ፍቅር እጅግ የሚያስገርም ነው፡፡”

በሁለተኛው ዙር በቡድኑ ላይ የሚኖሩ ለውጦች

“ከመጀመሪያው ዙር ክፍተቶቻችንን በመማር ቡድናችን ከመጀመሪያው ዙር በተሻለ መልኩ እንዲቀርብ የተለያዩ ነገሮችን እየሰራን እንገኛለን፡፡ የተወሰኑ ተጫዋቾችንም እየተመለከትኩ እገኛለሁ፡፡ ከነዚህም ውስጥ አንድ ሁለት አዳዲስ ተጫዋቾችን ለማስፈረም አቅደናል፡፡”

በሁለተኛው ዙር ከድቻ ምን እንጠብቅ?

“በመጀመሪያው ዙር የነበሩብንን ስህተቶች አርመን ሁለተኛው ዙር በተሻለ መልኩ በመቅረብ በመጀመሪያው ዙር ቅር ያሰኘናቸውን ደጋፊዎቻችንን በጥሩ ውጤት ለመካስ እየሰራን እንገኛለን፡፡”

ያጋሩ

Leave a Reply