“2ኛው ዙር እያሸነፍን እና ነጥብ እየሰበሰብን የምንሄድበት ዙር ይሆናል” አስራት ኃይሌ

ደደቢት በዘንድሮው የውድር ዘመን አሰልጣኝ በማሰናበት ቀዳሚው ክለብ ነበር፡፡ ከ4ኛው ሳምንት ጀምሮ ቡድኑን የተረከቡት ውጤታማው አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ ደደቢት 2ኛ ደረጃን ይዞ የመጀመርያውን ዙር እንዲያጠናቅቅ ረድተውታል፡፡ አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ በቡድኑ የአንደኛ ዙር ጉዞ እና 2ኛ ዙር ዙርያ ከሚልኪያስ አበራ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡

የዘንድሮ የደደቢት ግማሽ የውድድር ዘመን ጉዞ ምን ይመስላል?

እንደሚታወቀው የነበረው አሰልጣኝ መነሳት ተከትሎ ስሰራው ከነበረው ቴክኒካል ዳሬክተርነት ተነስቼ ነው ቡድኑን በዋና አሰልጣኝነት የተከብኩት፡፡ ቀድሞ ከነበረው አሰልጣኝ ያገኘሁት መረጃ ባይኖርም ከክለቡ አመራሮች ጋር በመነጋግር ቡድኑ ያለበትን ደካማ ጎኖች እያረምኩ እና ጥንካሬውን እያጎለበትኩ በተጨማሪ ቡድኑ የሚጫወትበትን የታክቲክ ስርአት በመቀየር ስራችንን ጀምረን አሁን በጥሩ ሁኔታ እንገኛለን፡፡

ለዋንጫ እንደሚጫወት ቡድን ከሜዳ ውጭ የማሸነፍና ጎሎችን በብዛት ያለማስቆጠሩ ችግር ከምን የመጣ ነው?

በየጨዋታው  ሁልጊዜ አንድ አንድ ሰው እናጣለን፡፡ በጉዳት እና ቅጣት ሁሌም የተሟላ ቡድን አይኖረንም። ሁሌም የተጋጣሚ ቡድን ደጋፊ እና ሜዳው ያለመመቸት ጫና ይኖርብናል፡፡ በርግጥ ቡድናችን ውስጥ የአጥቂ ችግር አለ ፤ ጌታነህ ብቻ ነው በማጥቃት ላይ በሚደረግ እንቅስቃሴ የሚጎላው፡፡ በክልሎች በተቻለ መጠን ለማሸነፍ ነው ትግል የምናደርገው፡፡ ተጨዋቾቹም ወደ ክልል ሲሄዱ መጠነኛ የራስ መተማመን ችግር አለባቸው፡፡

የቡድንዎ ተጨዋቾች የአካል ብቃት በሚፈልጉት ደረጃ እየሆነልዎ ነው ?

ከሞላ ጎደል እየለመዱት ነው ጫን ብዬ ክብደት ያለው ሥራ አልሰጣቸውም ፤ በሒደት ለጥንካሬ ፣ ለትንፋሽ እና ለፊትነስ የሚሆኑ ስራዎችን እየሰራን ነው፡፡ ከበፊቱ ግን ተሽለዋል፡፡

የዳዊት ጎል የማስቆጠር አቅሙ በጣም ቀንሷል፡፡ ይህ የሆነው ቡድኑ ከሚከተለው ታክቲካዊ አቀራረብ ነው ? ወይስ የተጨዋቹ ደረጃ እየወረደ መምጣቱ ነው?

የዳዊት የኳስ ክህሎቱ እንዳየሁት ከሆነ ጥሩ ነው። ነገር ግን ቀድሞ በሁለት አጥቂ ነበር የምንጫወተው በጌታነህ እና በዳዊት ። እንደኔ ሁለቱም ተመሳሳይ የአጨዋወት ባህሪ ያላቸው በመሆኑ ጌታነህ በፊት አጥቂነት ዳዊትን ደግሞ ከመስመር በሚነሳ አጥቂነት እንዲሰለፍ አድርጌዋለው ፤ ይህ የቦታ ለውጥ ትንሽ ግራ ሳይገባው አልቀረም። በፊት ወደለመደው ቦታ በተደጋጋሚ ይሄዳል። አዲስ ቦታ ሲሰጥህ የራስ መተማመንህ መውረድ የለበትም። አሁን ጥሩ ነው ፤ የአካል ብቃቱም እየተሻሻለ ነው፡፡

በሁለተኛው ዙር ምን  እንጠብቅ ?

እያሸነፍን እና ነጥብ እየሰበሰብን የምንሄድበት ዙር ይሆናል ብዬ አስባለው። ቡድኑ ባለበት ክፍተት ላይ ጥሩ ተጨዋቾችን አስመጥተናል፡፡ ይህ የበለጠ ጥቅም ይሆነናል፡፡ ከታች ያደጉት ታዳጊዎች ጥሩ ተስፋ አላቸው፡፡ ከሊጉ ጋር እየተላመዱ ጎል  እያስቆጠሩም ነው። ከዋንጫ ተፎካካሪዎች ውስጥ ነን አሸናፊ የማንሆንበት ምክንያት አይኖርም። ሁልጊዜ አንድ ቡድን ብቻ ቻንፒዮን መሆን የለበትም። እኛም ሻንፒዮን ለመሆን ጠንክረን እንሰራለን።

Leave a Reply