” በክለቡ አዲስ ታሪክ ለመፃፍ ተዘጋጅተናል” ሙሉአለም መስፍን

ሲዳማ ቡና አንደኛውን ዙር 5ኛ ደረጃ ይዞ አጠናቋል፡፡ ቡድኑ በአንደኛው ዙር ተፎካካሪ እንዲሆን ቁልፍ ሚና ከተወጡት ተጫዋቾች መካከልም ሙሉዓለም መስፍን በዋነኝነት ይጠቀሳል፡፡ ሙሉአለም በጥሩ አቋም ላይ ስለመገኘቱ ፣ ስለቡድኑ የአንደኛ ዙር ጉዞ እና የ2ኛ ዙር አላማቸው ከዳዊት ጸሃዬ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

የመጀመሪያ ዙር የቡድናችሁን እንቅስቃሴ እንዴት ተመለከትከው?

” የመጀመሪያው ዙር እንቅስቃሴያችንን እኔ በሁለት ከፍዬ ነው መመልከት የምፈልገው፡፡ በሜዳችን እና ከሜዳ ውጪ ያደረግናቸው ጨዋታዎች ሁለት መልክ ያላቸው ናቸው፡፡ በሜዳችን ባደረግናቸው ጨዋታዎች ላይ በጣም ጠንካራ ነበርን ፤ በዚህም በርካታ ነጥቦችን መያዝ ችለናል፡፡ በአንጻሩ ከሜዳ ውጪ ባሉ ጨዋታዎች ላይ ክፍተቶች ነበሩብን ፤ ይህ ደግሞ በኛ ቡድን ላይ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የሊጉ ተሳታፊ ቡድኖች ላይም የሚታይ ችግር ነው፡፡ ለዚህም በርካታ ምክንያቶች አሉ፡፡ የዳኞች ተፅእኖን ጨምሮ በኛ ሀገር እግርኳስ ህግ ላይ ባለሜዳው ቡድን ማሸነፍ አለበት ተብሎ የተፃፈ ነገር ያለ እስኪመስል ድረስ ከሜዳ ውጪ ስትጫወት ለማሸነፍ ትቸገራለህ፡፡ በዚህም በበርካታ አጋጣሚዎች ውጤት እንድናጣ ሆነናል፡፡ በአጠቃላይ ይዘንም ካጠናቀቅነው ደረጃም አንጻር የመጀመሪያ ዙር ጉዞዋችን ጥሩ የሚባል ነው፡፡”

በአንተ እይታ በመጀመሪያው ዙር የነበረው የቡድናችሁ ጠንካራ እና ደካማ ጎን ምን ነበር ብለህ ታስባለህ?

“በልምምድ ሜዳ ላይ አንስቶ የምንሰራቸው ስራዎች ጠንካራ ከመሆናቸው የተነሳ ቡድናችን በየትኛውም ሆኔታ ዘጠና ደቂቃ ተንቀሳቅሶ መጨረስ የሚችል ነው፡፡ ከዛ በዘለለ በቡድን አባላት መካከል ጥሩ መከባበር እና አንድነት አለ ፤ ይህም ሌላኛው ጥንካሬያችን ነው፡፡ እንደ ክፍተት የማስበው ፊት መስመር ላይ ያለብን መጠነኛ የአጨራረስ ችግሮች አሉብን፡፡ ከዛ በተጨማሪ ከሜዳ ውጪ በምናደርጋቸው ጨዋታዎች ላይ የጨዋታ አቀራረብ ችግሮች አሉብን ብዬ አስባለሁ፡፡”

በመጀመሪያ ዙር ላይ ስላሳየኸው ድንቅ እንቅስቃሴ ንገረን፡፡ ከጥሩ ብቃትህ ጀርባ ያለው ሚስጥርስ?

“በመጀመሪያ ዙር በበርካታ ጨዋታዎች ላይ ጥሩ መንቀሳቀስ ችያለሁ፡፡ ነገር ግን ይሄ ብቻ ነው አቅሜ ብዬ ግን አላስብም ፤ ከዚህ በላይ ጥሩ መሆን እንደምችል ይሰማኛል፡፡ ከፈጣሪ ጋር በሁለተኛው ዙር ከዚህ የበለጠ ቡድኔን ለማገልገል አስባለሁ፡፡ በእኔ እምነት ከእኔ ስኬታማ አቋም ማሳየት ጀርባ ትልቁን ድርሻ የሚወስዱት የቡድናችን የተከላካይ ስፍራ ተጫዋቾች ናቸው፡፡ ምክንያቱም የኛ ተከላካዮች ኳስን ይዘው በመጫወት በኩል ጥሩዎች ናቸው ፤ በዚህም እንደ ተከላካይ አማካይነቴ በራሴ ጥረት ከምነጥቃቸው ኳሶች በተጨማሪ ከነሱ ቶሎ ቶሎ ኳሶች ይደርሱኛል ፤ በዚህም በተደጋጋሚ ከነሱ ኳሶችን ማግኘቴ በማደራጀቱ በኩል ጥሩ እንድሆን አድርጎኛል ብዬ አስባለሁ፡፡ በተጨማሪም ከአሰልጣኛችን ጋር በመሆን የመጀመሪያ የአየር ኳሶችን እንዴት ማሸነፍ እንዳለብኝ በተጨማሪ እንሰራለን፡፡ ከዛ በዘለለ አብረውኝ ከጎኔ የሚጫወቱ ተጫዋቾች ጥሩ የኳስ ክህሎት ባለቤት መሆናቸው አግዞኛል ብዬ አስባለሁ፡፡”

በሁለተኛው ዙር ከሲዳማ ቡና ምን እንጠብቅ?

“ሁለተኛው ዙር ከመጀመሪያው በተለየ በጣም ውጥረት የበዛበት ነው የሚሆነው፡፡ ምክንያቱም በክለቦች መካከል ያለው የነጥብ ልዩነት በጣም ጠባብ ከመሆኑ የተነሳ ሁሉም ቀሪ ጨዋታዎች ትኩረት የሚሹ ናቸው፡፡ እኛም እንደ ቡድን በአንደኛው ዙር በሜዳችን ላይ የነበረንን ነገር አስጠብቀን ከሜዳ ውጪ ያሉብንን ችግሮች አርመን ምንም እንኳን የተሟላ የቡድን ስብስብ ባይኖረንም ከታች ካደጉት ልጆች ጋር በመሆን ከአንድ እስከ ሶስት ያለውን ደረጃ ይዘን በመጨረስ በክለቡ አዲስ ታሪክ ለመፃፍ ተዘጋጅተናል፡፡ በተጨማሪም በግሌ ፈጣሪ ከፈቀደና ምን አይነት ጉዳት ካላገደኝ በስተቀር አሁን ካለኝ ነገር በተሻለ የመስራት አቅሙ እንዳለኝ ስለማምን ከመጀመሪያው በተሻለ ለመቅረብ እሰራለሁ፡፡”

በመጨረሻም?

” በመጨረሻም ለቡድን አጋሮቼ መልእክት ማስተላለፍ እፈልጋለሁ፡፡ አሁን ያለንበት ውጤት ምንም የሚያዘናጋ ስላልሆነ እንዳይዘናጉ፡፡ እንዲሁም በተጨማሪም የክለቡ አመራሮች አመቱ ሲጀመር አቅደው እየሰሩ ያሉት ከ1-3 ያለውን ደረጃ ይዞ ለማጠናቀቅ ነውና እኛም ለሚከፍሉን ዋጋ በዚህ ምላሻችንን እንስጥ እላለሁ፡፡”

Leave a Reply