የኢትየጵያ ፕሪምየር ሊግ 1ኛ ዙር የክለቦች ዳሰሳ – ሀዋሳ ከተማ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመርያ ዙር መጠናቀቅን ተከትሎ ሶከር ኢትዮጵያ ክለቦችን በተናጠል በመዳሰስ ከጀመረች 4ኛ ቀን ላይ ትገኛለች፡፡ በዚህ ጽሁፍ አንደኛውን ዙር በ13ኛ ደረጃ ላይ ያጠናቀቀው ሀዋሳ ከተማ የውድድር ዘመን አጋማሽ ጉዞ በአብርሃም ገብረማርያም እና ሚልኪያስ አበራ እንዲህ ተዳሷል፡፡

የውድድር ዘመኑ ጉዞ

የሀዋሳ ከተማ የውድድር ዘመን ጉዞ በፈተና የተሞላ እና ከተጠበቀው በታች ሆኗል፡፡ በአዲስ መጪው አዲስ አበባ ከተማ በሜዳው 2-0 ተሸንፎ የውድድር ዘመኑን የጀመረው ሀዋሳ ከተማ ከቀናት በኋላ ግብ ጠባቂው ክብረአብ ዳዊትን በሞት ማጣታቸው መሪር ሀዘን ውስጥ ከቷቸዋል፡፡ በ3ኛው ሳምንት አርባምንጭን በማሸነፍ ወደ ድል ቢመለሱም የክብረአብ ህልፈት በቡድኑ ላይ የስነልቦና ጫና መፍጠሩ የሚካድ አይደለም፡፡ ከ3ኛው ሳምንት ድል በኋላ ሌላ ድል ለማስመዝገብ በ11ኛው ሳምንት ጅማ አባ ቡናን እስካሸነፉበት ጨዋታ ድረስ ለመዝለቅም ተገደዋል፡፡ አመዛኙን የአንደኛ ዙር የውድድር ዘመን በወራጅ ቀጠና ያሳለፈው ሀዋሳ በተስተካካይ ጨዋታ ንግድ ባንክን ማሸነፉን ተከትሎ ከወራጅ ቀጠናው በመውጣት የመጀመርያውን ዙር ማጠናቀቅ ችሏል፡፡

የበድኑ ውጤት ከአምናው ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነጻጸር

ሀዋሳ ከተማ አምና በተመሳሳይ ወቅት 10ኛ ደረጃ ላይ ይገኝ ነበር፡፡ ያስመዘገበው 16 ነጥብ (በጨዋታ በአማካይ 1.2 ነጥብ ) ዘንድሮ ካስመዘገበው 14 ነጥብ (በጨዋታ በአማካይ 0.9 ነጥብ) የተሻለ ነው፡፡ ሀዋሳን በሁለቱ ተመሳሳይ ወቅቶች ያስቆጠራቸው ግቦች ተቀራራቢ ናቸው፡፡ (በአማካይ 1.06 በጨዋታ) በመከላከል ሪኮርድም ተቀራራቢ የሆነ አማካይ የጎል መጠን አስተናግዷል፡፡

በአጠቃላይ ሀዋሳ ከተማ ካለፈው አመት ብዙም ለውጥ ያላሳየ ቡድን ነው ማለት ይቻላል፡፡

የጨዋታ አቀራረብ

አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በተደጋጋሚ የሚጠቀሙበት 4-3-3 የተጫዋቾች ሜዳ ላይ አደራደርን በበርካታ ጨዋታዎች ላይ ተጠቅመዋል፡፡ በአንዳንድ ጨዋታዎች ደግሞ 3-5-2 እና 4-2-3-1ን ተጠቅመዋል፡፡

ሀዋሳ በ4-3-3 አሰላለፍ የአማካይ መስመሩ ላይ ከኃይማኖት ወርቁ ፊት ፍሬው ሰለሞን እና ታፈሰ ሰለሞን(ኤፍሬም ዘካርያስን) ይጠቀማሉ፡፡ የድንቅ ክህሎት ባለቤት የሆኑት አማካዮቹ በሜዳው ቁመት ተጋጣሚያቸው ላይ በቀላሉ የበላይነት የሚወስዱ ናቸው፡፡

በአጥቂ መስመር ላይ አንድ የፊት አጥቂ ከሁለት የመስመር አጥቂዎች ጋር ይሰለፋሉ፡፡ ጋዲሳ መብራቴ በቀኝ መስመር ወደ መሀል አጥብቦ በመግባት አደጋ የሚፈጥር ሲሆን የአንደኛው የመስመር አጥቂ (ፍርዳወቅ/መድህኔ) የአጥቂነት ባህርይ ከሌላኛው የፊት አጥቂ ጋር ተቀራርቦ በመጫወታው የቡድኑ ቅርፅ 4-4-2 የሚመስልበት አጋጣሚዎች በጨዋታ መሀል ይታያሉ፡፡

ጠንካራ ጎን

የቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴ ጠንካራ ጎኑ ነው፡፡ ፍሬው ሰለሞን ፣ ጋዲሳ መብራቴ እና ታፈሰ ሰለሞንን የመሳሰሉ ተጫዋቾች እንቅስቃሴ ቡድኑ ተደጋጋሚ የግብ እድሎችን እንዲፈጥር አድርጓል፡፡ የአማካይ ተጫዋቾቹ እና የመስመር አጥቂዎቹ የማጥቃት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እየተወጡ ሲሆን በሁለቱም በኩል የሚገኙት የመስመር ተከላካዮችም የማጥቃት እንቅስቃሴያቸው ድንቅ ነው፡፡

ሀዋሳ ከተማ በአንደኛው ዙር በኳስ ቁጥጥር የተበለጠበት አጋጣሚን ማግኘት ያስቸግራል፡፡ ለዚህም የአማካይ መስመሩ ጥንካሬ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል፡፡

አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ለወጣቶች የሰጡት የመጫወት እድል በጠንካራ ጎኑ የሚጠቀስ ነው፡፡ ከታዳጊ ቡድኑ ያደጉት መሳይ ጳውሎስ ፣ እስራኤል እሸቱ ፣ ነጋሽ ታደሰ እና ወንድማገኝ ማዕረግ ተደጋጋሚ የመጫወት እድል ማግኘት ችለዋል፡፡

ደካማ ጎን

የመከላከል እንቅስቃሴ የቡድኑ ደካማ ጎን ነው፡፡ 22 ግቦችን ያስተናገደው ሀዋሳ ከንግድ ባንክ ቀጥሎ ከፍተኛ ግብ ያስተናገደ ክለብ ሆኗል፡፡ የተከላካይ መስመሩ በጉዳት እና ቅጣት መሳሳት እንዲሁም ተክተው የሚገቡ ተጫዋቾች የሊግ ልምድ አናሳነት ቡድኑ በርካታ ግብ እንዲያስተናግድ በዋና ምክንያትነት ቢቀመጥም የቡድኑ አጠቃላይ የመከላከል አደረጃጀት ደካማ ነው፡፡

ቡድኑ በሜዳው ስፋት ያተኮረና ቀጥተኛ እንቅስቃሴ ከሚያደርጉ ቡድኖች ጋር ሲጫወት ይቸገራል፡፡ አማካዮቹም ሆነ የመስመር አጥቂዎቹ ወደ መሀል አጥብበው የሚጫወቱ በመሆናቸው የተከላካይ መስመሩ (በተለይም ፉልባኮቹ በሚያጠቁበት ጊዜ) ተጋላጭ ሲሆን ይስተዋላል፡፡ ከወገብ በላይ የሚገኙ ተጫዋቾች በመከላከል ላይ ያላቸው ተሳትፎም እጅግ አናሳ ነው፡፡

የግብ ማስቆጠር ድክመት ሌላው ተጠቃሽ ደካማ ጎን ነው፡፡ ሀዋሳ በጣም በርካታ የግብ እድሎች እንደመፍጠሩ ወደ ግብነት መቀየር ቢችሉ ኖሮ ሀዋሳ በወራጅ ቀጠናው ባልተገኘ ነበር፡፡ ቶጓዊው አጥቂ ጃኮ አራፋት ከቡድኑ እንቅስቃሴ ጋር ቢዋሃድም የጨራሽ አጥቂነት ባህርይ የለውም፡፡ በተለይም ቡድኑ ወደ አደጋ ክልል ሲገባ የሚገኝበት ቦታ ከሚጠበቅበት እጅግ ርቆ በመሆኑ ቡድኑ ከፊት ዱልዱም ቅርፅ (ስል ያልሆነ / ካለ አጥቂ የሚጫወት) ቡድን ያስመስለዋል፡፡

የዲሲፕሊን ጉዳይ ክለቡን ኋላ ካስቀሩት ምክንያቶች መካከል ሊጠቀስ ይገባዋል፡፡ በአንደኛው ዙር በርካታ ቀይ ካርዶች የተመዘዙበት ቡድን ሀዋሳ ከተማ ሲሆን በቅጣቶች ምክንያት የተሟላ ስብስብ ይዞ ወደ ሜዳ እንዳይገባ አድርጎታል፡፡ የአንዳንድ ተጫዋቾች ባህርይም የጨዋታን መንፈስ የሚረብሹ ናቸው፡፡ በተለይ የዳኝነት ውሳኔዎችን በጸጋ ባለመቀበል የሚፈጥሩት ግርግር ቡድኑ በጨዋታ ላይ ትኩረቱን እንዲያጣ ሲያደርገው በተደጋጋሚ ተስተውሏል፡፡

በሁለተኛው ዙር ምን ይጠበቃል?

ሀዋሳ በተከላካይ መስመር አይቮሪያዊው መሀመድ ሲይላን ሲያስፈርም በመስመር አጥቂ ስፍራ ላይ ደግሞ ምስጋናው ወልደዮሐንስን ማስፈረም ችሏል፡፡ የሁለቱ ተጫዋቾች መፈረም ቡድኑ ያለበትን ክፍተት ይደፍናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ሀዋሳ የክለቡን የውስጥ ችግሮች በውይይቶች ለመፍታት ያደረገው ጥረት በሁለተኛው ዙር ውጤታማ እንዲሆን ሊያደርገው ይችላል፡፡ በመጨረሻዎቹ የአንደኛ ዙር ጨዋታዎች ቡድኑ የውጤት መሻሻል እንዲያሳይ ሲረዳውም ተመልክተናል፡፡

የአንደኛው ዙር ኮከብ ተጫዋች – ፍሬው ሰለሞን

ሀዋሳን ዘንድሮ የተቀላቀለው ፍሬው በግሉ ምርጥ ጊዜ ማሳለፍ ችሏል፡፡ የአጥቂ አማካዩ የቡድኑን የማጥቃት እንቅስቃሴ ከመምራት በተጨማሪ 5 ጎሎችን በማስቆጠር ስሙን በጎል አስቆጣሪዎች ተርታ ማሰለፍ ችሏል፡፡ ባለክህሎቱ ፍሬው ከድሬዳዋ ከተማ ጋር በተደረገው ጨዋታ የፈጸመው ያልተገባ ድርጊት ቢያስወቅሰውም በይፋ ይቅርታ መጠየቁ የሚበረታታ ተግባር ነው፡፡

ተስፋ የሚጣልበት ተጫዋች – መሳይ ጳውሎስ

መሳይ የተጫዋቾችን ጉዳት ተጠቅሞ በፍጥነት የቡድኑ ቋሚ ተሰላፊ መሆን ችሏል፡፡ በሁለተኛው ዙር በቦታው ጠንካራ ፉክክር የሚጠብቀው በመሆኑ ቦታውን ማስከበር ከቻለ የወደፊቱ የቡድኑ ኮከብ መሆን ይችላል፡፡

2 Comments

  1. ውድ የሶከር ኢትዮጵያ አዘጋጆች በሀገሪቱ ስፖርት ዙሪያ በድረገፅ የምታቀርቡት መረጃ ወደር እንደማይገኝለት ሁሌም የምንገልፀው ነው፡፡ በቅርቡም የፕሪምየር ሊጉን 1ኛ ዙር መጠናቀቅ ተከትሎ እያቀረባችሁት ባለው የቡድኖች ዳሰሳ ዝግጅት እጅጉን እየተደመምን የተሟላ መረጃ እያገኘን ነው፡፡ ዛሬም ስለ ሀዋሳ ከነማ ዳሰሳችሁን ተመልክተናል በጣም ጥሩ ዳሰሳ እና ግምገማ እንዲሁም አሀዛዊ መረጃ መሆኑን እየገለፅኩኝ ምናልባት በታይፕ ስህተት ሆኖ ሳይሆን አይቀርም ሀዋሳ ከነማ ካደረጋቸው 15 ጨዋታዎች ጎል ሳይቆጠርበት የወጣው በአንዱ ብቻ(ከድሬዳዋ ከነማ ጋር) እንዲሁም ጎል ሳያስቆጥር የወጣው በአራት (ከአአ ከነማ፣ደደቢት፣ አዳማና ኤሌክትሪክ ጋር) ጨዋታዎች ብቻ መሰለኝ ትክክል ከሆነ ቢታረም አሪፍ ነው ….. በተጨማሪም በዲሲፕሊን ጉድለት እንደገለፃችሁት ብዙ ነገር እያጣ እንደሆነ በዚህ አመት ያስተዋልነው ጉዳይ ነው ከዳኞች ጋር ያለውም እሰጥ አገባ እንዲሁ በግሌ እቃወማለው መሻሻል ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ ነገር ግን ሀዋሳ ከነማ “በዲሲፕሊን ጉዳይ ብዙ ካርድ የተመዘዘበት ቡድን ነው” የሚለውን ድምዳሜ አይቼ ምንም እንኳን የቀይ ካርዱን ብስማማም 5 ቀይ ካርድ(አራቱ በሁለት ቢጫ ካርድ መሆኑን ልብ ይሏል) የተመዘዘበት ሌላ ቡድን የለም እስከአሁን እየዳሰሳችሁ ባላችሁት ቡድኖች ውስጥም ከሀዋሳ ከነማ በላይ ብዙ ምናልባትም ከእጥፍ በላይ የቢጫ ካርድ የተመዘዘባቸው ቡድኖች እንዳሉ ተመልክቻለው፡፡ ድምዳሜው በቀይ ካርድ ከሆነ በፅሁፉ ውስጥ “ቀይ ካርድ ብዙ የተመዘዘበት” በሚለው ቢስተካከል መልካም ይሆናል አብዛኛው ሚድያ ሶከር ኢትዮጵያን እንደ ዋቢ ስለሚጠቀም እንዳያወዛግብ በሚል ነው፡፡ በተረፈ ቀጥሉበት በርቱልን ፡፡

    1. @Hawassa Sport Discussion

      ለአስተያየትህ ከፍ ያለ ምስጋና እናቀርባለን፡፡
      አንተም እንደጠቀስከው ካርድ የሚለው በታይፕ ስህተት በመሆኑ ቀይ ካርድ በሚለው ይስተካከልልን፡፡ ነገር ግን ቡድኑ በ3 ጨዋታዎች ነው ያልተቆጠረበት (ከአርባምንጭ ፣ ባንክ እና ድሬዳዋ)፡፡ ግብ ሳያስቆጥር የወጣባቸውም 5 ናቸው (የድሬዳዋን አልጠቀስከውም)

Leave a Reply