” የ2ኛው ዙር ዋንኛ እቅዳችን ካለንበት የውጤት ቀውስ መውጣት ነው” በዛብህ መለዮ

ወላይታ ድቻ በአንደኛው ዙር ከቀድሞ ጊዜያት የተዳከመ እንቅስቃሴ ቢያደርግም በዛብህ መለዮ በግሉ ድንቅ የውድድር ዘመን በማሳለፍ ላይ ይገኛል፡፡ የአጥቂ አማካዩ 4 ግቦችን ያስቆጠረ ሲሆን 3 ጎል የሆኑ ኳሶችንም አመቻችቶ አቀብሏል፡፡

በዛብህ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረገው ቆይታ ጠንክሮ መስራቱ በድንቅ አቋም ለመገኘት እንደረዳው ተናግሯል፡፡

“በግሌ ሁልጊዜም ቢሆን የተሻለ ነገርን ለመስራት ጥረት አደርጋለሁ ፤  ለዚህም አሰልጣኙ ከሚሠጠኝ ነገር በተጨማሪ በግሌ ተጨማሪ ነገሮች አሰራ ስለነበር በ15ቱም የሊጉ ጨዋታዎች ላይ በቋሚነት በመሠለፍ ስኬታማ የሆኑ ጊዜያትን አሳልፌያለሁ ብዬ አምናለሁ፡፡ እንደ ቡድን ውጤታችን ጥሩ ባይሆንም በግሌ በተለይ በዚህ አመት ውጤታማ ነኝ ብዬ አስባለሁ፡፡ የኔ ጥሩ መሆን በተዘዋዋሪ ቡድኔን እንደሚያግዝም አስባለሁ፡፡”

ይላል፡፡ በዛብህ አክሎም አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ የአጨዋወት ባህርዩን ተረድቶ የሰጠው ነጻ ሚና ብቃተቱን እንዳጎላው ያምናል፡፡

” አሰልጣኝ መሣይ ተፈሪ በሚከተለው ታክቲክ የኔን አንድ ቦታ ላይ ቆሞ መጫወት አለመቻልን በመረዳት ለኔ በተለይ በመከላከሉም ሆነ በማጥቃት ውስጥ በነፃነት እንድሣተፍ ሙሉ ነፃነቱን ስለሰጠኝ ይሄ የበለጠ ውጤታማ እንድሆን አግዞኛል ብዬ አስባለሁ፡፡”

ባለ ክህሎቱ አማካይ በምርጥ አቋሙ በመዝለቅ ቡድኑን ወደ ውጤታማነት መመለስ እና የዋህያዎቹን ማልያ ማጥለቅ ህልሙ መሆኑን ይናገራል፡፡

” በቅድሚያ ዋነኛው እቅዴ ከቡድን አጋሮቼ ጋር በጋሬ በመሆን ቡድናችንን ካለበት የውጤት ቀውስ ማውጣት ነው፡፡ በመቀጠል አሁን እያሳየሁት ካለው ነገር በተሻለ አቅሜን አሳይቼ ለብሔራዊ ቡድን ለመመረጥ የተቻለኝን ጥረት አደርጋለሁ፡፡”

በ10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ 1ኛውን ዙር ያጠናቀቀው ወላይታ ድቻ ዘንድሮ መልካም የውድድር አመት እያሳለፈ አይገኝም፡፡ ነገር ግን በዛብህ በየጨዋታው የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ከአምናው መሻሻሉን ይናገራል፡፡

“ከአምናው ስብስብ የተወሰኑ ተጫዋቾች ናቸው ቡድኑን የለቀቁት ፤ በተለይም በቋሚነት ይጫወቱ ከነበሩት ልጆች በድሉ መርዕድ ነው ከቡድኑ የተለየው፡፡ በዘንድሮው ስብስብ ውስጥ የተሻለ አቅም ያላቸው ተጫዋቾች ተጨምረዋል፡፡ የእግርኳስ ነገር ሆነና ውጤት መያዝ አልቻልንም እንጂ በጨዋታ እንቅስቃሴ ረገድ የዘንድሮው ቡድን ከአምናው የተሻለ ነው፡፡” የሚለው በዛብህ ለቡድኑ ድክመት ምክንያት የሚለውን እንዲህ ይገልጸል፡፡

“እንደሚታወቀው ከዚህ ቀደም የነበረው የወላይታ ድቻ አንዱና ዋነኛው ጥንካሬው የነበረው በመከላከል አደረጃጀት ላይ ጥሩ ነገር ነበረን ፤ ነገርግን በዘንድሮው አመት ላይ ያ ጥንካሬያችን አብሮን የለም፡፡ በአንጻሩ ከዚህ ቀደም ከነበሩት አመታት በተለየ ግቦችን እያስቆጠርን እንገኛለን ፤ ነገርግን በቀላሉ ግቦችን እያስተናገድን መሆኑ ለውጤት ማጣታችን ምክንያት ነው፡፡

“የአንደኛው ዙር የቡድናችን እንቅስቃሴ ፣ ደረጃችንም እንደሚገልፀው እንደጠበቅነው አይደለም፡፡ ነገር ግን በችግሮቻችን ላይ የቡድኑ አባላት ተወያይተንባቸዋል በዚህም በሁለተኛው ዙር አርመን ለመቅረብ እንሞክራለን፡፡” ሲልም በሁለተኛው ዙር የተሻለ ወላይታ ድቻን ይዘው እንደሚቀርቡ ገልጿል፡፡ በዛብህ መጨረሻም በጥሩ ብቃት ላይ እንዲገኝ ለረዱትበሙሉ ምስጋናውን አቅርቧል፡፡

” አሁን ላለሁበት ደረጃ እንድበቃ ለረዳኝ ፈጣሪዬ ፣ ለቤተሰቦቼ እንዲሁም እዚህ እንድደርስ ላገዘኝ አሰልጣኝ መሣይ ተፈሪ እና የቡድን አጋሮቼ ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡”

Leave a Reply