የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 1ኛ ዙር የክለቦች ዳሰሳ – መከላከያ 

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመርያ ዙር የክለቦችን ጉዞ በተናጠል በመዳሰስ ከጀመረች 5ኛ ቀን ላይ ትገኛለች፡፡ በዚህ ጽሁፍ አንደኛውን ዙር በ8ኛ ደረጃ ላይ ያጠናቀቀው መከላከያ የውድድር ዘመን አጋማሽ ጉዞ በዮናታን ሙሉጌታ እና ሚልኪያስ አበራ እንዲህ ተዳሷል፡፡

የመጀመሪያ ዙር የመከላከያ ጉዞ

መከላከያ ከዘንድሮው የውድድር አመት መክፈቻ ሶስት ጨዋታዎች ውስጥ በሁለቱ ተሸንፎ እና በአንዱ አቻ ተለያይቶ ጥሩ ባልሆነ መንገድ ነበር 2009ን የጀመረው ። ከአራተኛው ሳምንት ጀምሮ በተደረጉ ጨዋታዎች ግን ጦሩ አስገራሚ ጉዞ ማድረግ ቻለ። ከህዳር ወር መጨረሻ እስከ ታህሳስ ወር ማብቂያ ድረስ ባደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች አራቱን በድል በመወጣት እና በሁለቱ ነጥብ በመጋራት ነበር የግማሽ አመቱን ምርጥ ጊዜ ያሳለፈው። ይህ አካሄዱን በጥር ወርም ቀጥሎበት መሪዎቹን በነጥብ ይቀርባል ተብሎ ቢጠበቅም የቡድኑ የጥር ወር ጉዞ ግን እንደተጠበቀው ሳይሆን ቀረ። መከላከያ በወሩ መግቢያ ላይ በአርባምንጭ 1-2 ከተረታ በኋላ ያደረጋቸውን የመጨረሻ አምስት ጨዋታዎች በሙሉ በአቻ ውጤት ነበር የጨረሰው።

የቡድኑ ውጤት ከአምናው ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነፃፀር

ዘንድሮ ከግማሽ በላይ የሆኑትን ጨዋታዎች በአቻ ውጤት የጨረሰው መከላከያ ሁለቱን ተከታታይ የውድድር አመታት በተመሳሳይ ስምንተኛ ደረጃ ነው የሊጉን አጋማሽ  ያጠናቀቀው። ሆኖም ግን የቡድኑ የአሸናፊነት ዕድል ከአምናው ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነፃፀር ከ 30% ወደ 26% ዝቅ ብሎ እናገኘዋለን። መከላከያ በያዝነው የውድድር አመት ግብ በማስቆጠሩ የተሻለ ነገር አሳይቶ 0.84 ከነበረው የጨዋታ በአማካይ የግብ መጠን ወደ አንድ ጎል ከፍ ማለት ቢችልም የሚያስተናግደው የግብ መጠንም በአማካይ 0.76 ወደ 1.06 ጨምሯል ።

የመጀመሪያው ዙር የቡድኑ አቀራረብ

በአሰልጣኝ ሻለቃ በለጠ ገ/ኪዳን ስር የሚሰለጥነው የመከላከያ ቡድን የ 4-4-2 የተጨዋቾች አደራደርን ይጠቀማል። በእርግጥ የተከላካይ አማካዩ በሀይሉ ግርማ ከአራቱ አማካዮች መሀል ተነጥሎ መታየቱ የቡድኑን አጨዋወት ወደ 4-1-3-2 ይወስደዋል። ከሶስቱ አማካዮችም ሁለቱ ሳሙኤሎች በግራ እና በቀኝ በኩል እያጠበቡ ወደመሀል በመግባት ሲጫወቱ የቡድኑ አምበል ሚካኤል ደስታ ከሳጥን እስከሳጥን ያለውን ቦታ የመሸፈን ሀላፊነት አለው። መከላከያ በሚያጠቃበት ወቅት ሁለቱን የመስመር አማካዮች በዋነኝነት ይጠቀማል። የመስመር ተከላካዮቹ ከኋላ በረጅም የሚልኳቸውና እስከተጋጣሚያቸው ይመከላከል ወረዳ ድረስ ገብተው የሚያሻግሯቸውን ኳሶችም ከፊት ለሚሰለፉት ሁለት አጥቂዎች ሌሎቹ ዕድል መፍጠሪያ መንገዶች ናቸው።

ጠንካራ ጎን

ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያዊያን ተጨዋቾች የተገነባው የመከላከያ ስብስብ ጥሩ የአካል ብቃት ላይ መገኘት በመጀመሪያው ዙር በዋና ተሰላፊዎች ላይ ተደጋጋሚ ለውጥ እንዳይኖር እና ተጨዋቾች በየሳምንቱ አብረው በመሰለፍ በመሀከላቸው ጥሩ የመናበብ እና የመግባባት እድል እንዲፈጠር አድርጓል። በሽግግሮች ላይ በተጨዋቾች መሀል የሚታየው በቶሎ ቦታን የመተካካት አጨዋወት እንዲሁም ጨዋታዎች እስኪጠናቀቁ ድረስ በመታግል  ውጤትን ለመቀየር በሙሉ ሀይል የመጫወት ሂደትም ቡድኑ ካለው የአካል ብቃት ደረጃ የመነጨ መሆኑን መናገር ይቻላል። መከላከያ  ከሰበሰባቸው 20 ነጥቦች መሀል ዘጠኙን ያሳካው ከመመራት ተነስቶ ባስቆጠራቸው ግቦች መሆኑም ይህን ሀሳብ ይበልጥ ያጠናክረዋል። ይህ ጥንካሬያቸው በጎዶሎ ተጨዋች ጨዋታዎችን ለመጨረስ በተገደዱባቸው አጋጣሚዎች ጭምር የታየ ነበር።

ሌላው የቡድኑ ጠንካራ ጎን የመስመር ተከላካዮቹ ማጥቃት ላይ ያላቸው ተሳትፎ ነው። የመስመር አማካዮቹ ወደመሀል የጠበበ አጨዋወት በሜዳው ስፋት በሁለቱም አቅጣጫዎች የሚተወውን ክፍት ቦታ በመጠቀም ቴዎድሮስ በቀለ ከግራ እንዲሁም ሽመልስ ተገኝ ከቀኝ መስመር ተከላካይነት ቦታ ላይ በመነሳት ማጥቃቱን ሲያግዙ ይታያል። ይህ በጥቂት ቡድኖች ውስጥ ብቻ የሚታይ ጠንካራን ጎንን መከላከያ መያዙ ሊበረታታ የሚገባው ነው። በተለይ ቴዎድሮስ መከላከያ በታህሳስ ወር ላደረገው መልካም ጉዞ የግብ እድሎችን ከመፍጠር ጀምሮ ጎል ይሆኑ ኳሶችን እስከማቀበል እንዲሁም ጎል እስከማስቆጠር የደረሰባቸው ጨዋታዎች ለቡድኑ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርገዋል።

በተናጠል ብቃት ለቡድኑ ውጤት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረገው ግብ ጠባቂው አቤል ማሞ ድንቅ አቋም ላይ መሆን ለመከላከያ ጥንካሬ ሲሆነው ታይቷል። አቤል በተለይ በመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ በአስገራሚ ሁኔታ ያድናቸው የነበሩ ሙከራዎች ለቡድኑ ነጥቦችን ይዞ መውጣት አይነተኛ አስተዋፅኦ ነበራቸው። የተከላካይ አማካዩ በሀይሉ ግርማ ሚናም በጥንካሬው ሊነሳ የሚገባው ነው። በተለይ ከሚካኤል ደስታ ጋር ያለው ጥምረት የተጋጣሚ የአጥቂ አማካዮች በመስመሮች መሀከል ክፍተቶችን እንዳያገኙ የሚያደርግበት እና የመስመር ተከላካዮቹ በማጥቃት ወቅት የሚተውትን ቦታ የመስመር አማካዮችም ሆኑ የመሀል ተከላካዮች ለመሸፈን የሚያረጉትን ጥረት ሚዛናዊ እንዲሆን ባማድረግ በኩል ቁልፍ ሚና ሲጫወት ተስተውሏል።

ደካማ ጎን

የመከላከያ ትልቁ ደካማ ጎኑ ብዙ የጎል እድሎችን አለመፍጠር እና የተገኙ የግብ ዕድሎችን ያለመጨረስ ችግር ነው። የአማካይ መስመሩ የጠበበ አጨዋወትን ተከትሎ ቡድኑ የሜዳውን ስፋት እንዲጠቀም ዋና ሚና ያላቸው የመስመር ተከላካዮች ጥሩ ባልሆኑባቸው ጨዋታዎች ላይ መከላከያ ከአማካይ መስመሩ በቂ የግብ እድሎችን መፍጠር ሲሳነው ይታያል። በተለይ የመስመር አጥቂዎችን ከሚጠቀሙ እና በመስመሮች በኩል የሚነሱ የተጋጣሚን ጥቃት ለመመከት ከሚችሉ ቡድኖች ጋር ሲጫወት ይህ ችግር ጎልቶ ይታያል። የቡድኑን የመስመር ተከላካዮች እንቅስቃሴ መገደብ የመከላከያን ጥቃት ለመቀንስ ወሳኝ መሆኑን ተረድተው እና መፍትሄ ይዘው ወደሜዳ ለሚገቡ ቡድኖች ምላሽ የሚሰጥ ታክቲካዊ መላ አለማበጀት እና ሁሉንም ቡድኖች ተመሳሳይነት ባለው አጨዋወት መግጠም ይህን የቡድኑን ደካማ ጎን ያጎላዋል።

በብዛት በምንይሉ ወንድሙ እና ማራኪ ወርቁ የሚመራው የአረንጓዴ እና ቀይ ለባሾቹ የአጥቂ መስመር በእንቅስቃሴ የተጋጣሚን የተከላካይ መስመር የመረበሽ አቅሙ መልካም ቢሆንም አጨራረስ ላይ ግን ደከም ብሎ ታይቷል። የምንይሉ ወንድሙ ከረጅም ጊዜ ጉዳት በኋላ ወደሜዳ መመለስ እና አሁንም ሙሉ ለሙሉ አለማገገም እንዲሁ የሌላኛው አጥቂ ባዬ ገዛሀኝ እስከመጀመሪያው ዙር መጨረሻ ድረስ ከጉዳቱ አለመመለስ የጦሩን የፊት ክፍል እንዳሳሳው መመለከት ይቻላል።

በሁለተኛው ዙር ምን ይጠበቃል ?

እስካሁን ባለው ሁኔታ መከላከያ የተጨዋቾች ዝውውር ላይ እየተሳተፈ አይደለም። የባዬ ገዛኸኝ ልምምድ መጀመር እና በሁለተኛው ዙር ወደሜዳ ለመመለስ መቃረብ ለአሰልጣኝ ሻለቃ በለጠ ቡድን መልካም ዜና ይመስላል። ባዬ ወደቀደመ አቋሙ በፍጥነት የሚመለስ ከሆነ እና መከላከያ ግቦችን ባማቆጠሩ በኩል ያለበትን ችግር ከቀረፈ በሊጉ ሰንጠረዥ ወደላይ ከፍ የማለት እድል ይኖረዋል። ጦሩ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ተሳትፎው የሚገፋበት ከሆነም ሁለቱን ውድድሮች አጣጥሞ በመቀጠል የትኩረት መበታተን ሳይገጥመው ጨዋታዎችን ማድረግም ይኖርበታል።

የቡድኑ መጀመሪያው ዙር የቡድኑ ኮከብ ተጨዋች – ሳሙኤል ታዬ

የቀኝ መስመር አማካዩ ሳሙኤል ታዬ መከላከያ እንደ ቡድን ጥሩ ባልነበረባቸው ጨዋታዎች ላይ ሳይቀር መልካም እንቅስቃሴ አድርጓል። የቡድኑ ዋና የጥቃት መነሻ መስመር ሆኖ በማገልገል ብቻም ሳይሆን በመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ ግቦችን አስቆጥሮ ቡድኑ ነጥብ ይዞ እንዲወጣ ያደረገባቸው አጋጣሚዎችም የተጨዋቹን ወሳኝነት የሚያስረዱ ናቸው። እስካሁን ባለው ሂደትም የቀድሞው የኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ኢትዮጵያ ቡና አማካይ ዘንድሮ ካስቆጠራቸው አራት ግቦች ሶስቱ በመጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎች የተገኙ ነበሩ።

Leave a Reply