ቻምፒየንስ ሊግ፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ የመልስ ጨዋታውን ነገ ሀዋሳ ላይ ያደርጋል

በቶታል 2017 የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ቅድመ ማጣሪያ ቅዱስ ጊዮርጊስ የሲሸልሱን ኮት ደ ኦርን በመልሱ ጨዋታ ሀዋሳ ላይ ይገጥማል፡፡ በመጀመሪያው ጨዋታ ፕራስሊን ላይ በሳላዲን ሰዒድ ሁለት ግቦች 2-0 ያሸነፈው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሲሸልስ መልስ ከዕረቡ ጀምሮ ዝግጅቱን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡

ፈረሰኞቹ በአርብ እለት ጨዋታው በሚካሄድበት የሀዋሳ ኢንተርናሽናል ስታዲየም ልምምዳቸውን በአድርገዋል፡፡ ለሁለት በመከፈልም የተወሰነ ደቂቃ የቆየ ጨዋታውን በአሰልጣኝ ማርት ኑይ መሪነት ሲያደርጉ ተስተውሏል፡፡

የቅዱስ ጊዮርጊስ ምክትል አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ በመልሱ ጨዋታ ምንም ዓይነት መዘናጋት በቡድናቸው እንደማይታይ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡ “የመዘናጋት ነገር አይኖርም፡፡ ዝግጅታችንን ያደረግነው እንደ አዲስ እንጂ 2-0 አሸንፈናል በሚል ስሜት አይደለም፡፡ ከሰኞ ጀምሮ ዝግጅት እያደረግን ነበር፡፡ በህዝባች እና ደጋፊያችን ፊት ጥሩ ነገር ለማሳየት እንሞክራለን፡፡”

አሰልጣኝ ዘሪሁን አክለው እንደተናገሩት በመጀመረያው ጨዋታ ቡድኑ የታዩበትን ክፍተቶች ለመሸፈን እየተሞከረ ነው፡፡ “እምብዛም ክፍተት ባናይም ግን ያገኘናቸውን እድሎች ያለመጠቀም ነገር አለ፡፡ ብዙ እድሎች አግኝተን ሳንጠቀም ቀርተናል፡፡ እነዚህን ነገሮች በደጋፊያችን ፊት ቀይረን ጥሩ ነገር ይዘን እንወጣለን፡፡”

ቅዱስ ጊዮርጊስ በጉዳት ምክንያት የአሉላ ግርማን፣ ምንያህል ተሾመ እና ራምኬል ሎክን ግልጋሎት አያገኝም፡፡ የመስመር ተከላካዩ አሉላ ለተሻለ ህክምና ወደ ህንድ አምርቷል፡፡

የኮት ደኦር ልኡካን ቡድን ሐሙስ አመሻሽ ከቪክቶሪያ ተነስቶ አዲስ አበባ የገባ ሲሆን አርብ ጠዋት ወደ ሀዋሳ ተጉዞ 10፡30 በኃላ ልምምዱን በሀዋሳ ኢንተርናሽናል ስታዲየም ማድረግ ችሏል፡፡ በልምምዱ ሰፊውን ግዜ የፈጀው የመስመር አጨዋወትን መከላከል እና በመስመር የመልሶ ማጥቃትን እንዴት መፍጠር እንደሚቻል ነበር፡፡

የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ደጋፊዎች ዛሬ እና ነገ ወደ ሀዋሳ ለጨዋታው እንደሚመጡ ይጠበቃል፡፡ ስፖርት ማህበሩ ነፃ አውቶብስ ለተጓዥ ደጋፊዎች ማዘጋጀቱንም ለሶከር ኢትዮጵያ አሳውቋል፡፡

ጨዋታው የሚመሩት ዳኞች ከሱዳን ሲሆኑ አራተኛው ዳኛ ከኬንያ ነው፡፡ የጨዋታው ታዛቢ ደግሞ ከደቡብ ሱዳን ናቸው፡፡ የፊፋ ኢንተርናሽናል ዳኛ መሃመድ አሊ ኢስማኤል እንዲሁም ረዳቶቹ ኤልሞይዝ አሊ አህመድ እና ሃይታም አህመድ ጨዋታውን እንዲመሩ በካፍ የተመረጡ ናቸው፡፡

Leave a Reply