የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 1ኛ ዙር የክለቦች ዳሰሳ – ሲዳማ ቡና

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመርያ ዙር መጠናቀቅን ተከትሎ ሶከር ኢትዮጵያ ክለቦችን በተናጠል በመዳሰስ ላይ ትገኛለች፡፡ አንደኛውን ዙር በ5ኛ ደረጃ ያጠናቀቀው ሲዳማ ቡና የውድድር ዘመን አጋማሽ ጉዞ በዮናታን ሙሉጌታ እና ሚልኪያስ አበራ እንዲህ ተዳሷል፡፡

የመጀመሪያ ዙር የሲዳማ ቡና ጉዞ

ሲዳማ ቡና ጥሩ የሚባል ግማሽ የውድድር አመት ማሳለፍ ችሏል። በመጀመሪያዎቹ አራት ሳምንታት ካደረጋቸው ጨዋታዎች ሶስቱን በማሸነፍ ወደ ሰንጠረዡ የላይኛው ክፍል ላይ ከሚገኙ ክለቦች ተርታ በመሰለፍ የጀመረው ሲዳማ ቡና በቀጣዮቹ ስድስት ጨዋታዎች ግን መጠነኛ መቀዛቀዝ አሳይቷል ። በነዚህ በአመዛኙ ታህሳስ ወር ባደረጋቸው ጨዋታዎች ሜዳው ላይ ሀዋሳ ከተማን በወንድማማቾች ደርቢ ማሸነፍ ከቻለበት ጨዋታ ውጪ ቀሪዎቹን 3 ጨዋታዎች አቻ ወጥቶ በሁለቱ ደሞ ሽንፈትን ቀምሷል። ሲዳማ ቡና የመጀመሪያው ዙር ከመጠናቀቁ በፊት ግን በጥር ወር መልካም እንቅስቃሴ ባማድረግ ወደ አጀማመሩ እንደተመለሰ መታዘብ ይቻላል። ከ11ኛው ሳምንት ጀምሮ ባደረጋቸው የመጨረሻ ጨዋታዎች አንድ ሽንፈት ብቻ ገጥሞት የመጨረሻውን ጨዋታ ከመከላከያ ጋር አቻ ሲለያይ በቀሩት ሶስት ጨዋታዎችን ድል አድርጓል። በዚህም መሰረት  10 ነጥቦችን በማሳካት ቀድሞ በነበረው 15 ነጥብ ላይ ጨምሮ ከመሪው ጋር ያለውን ልዩነት ወደ 4 በመቀነስ 5ተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል ።

የቡድኑ ውጤት ከአምናው ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነፃፀር

የ 2008 እና የ2009 የሲዳማ ቡና የመጀመሪያ ዙር ጉዞ በተመሳሳይ 5ኛ ደረጃ ላይ ነው የተጠናቀቀው። ሆኖም ሲዳማዎች በጨዋታ የሚያሳኩት የነጥብ መጠን በአማካይ ከ 1.46 ወደ 1.73 ከፍ ብሏል። ዘንድሮ ሰባት ጨዋታ ማሸነፍ መቻላቸው በጨዋታ ሶስት ነጥብ የማሳካት እድላቸውን ከ 31% ወደ 47% ጨምሮታል። በሌላ በኩል ሲዳማ ቡና በጨዋታ በአማካይ የሚያስቆጥረው የግብ መጠን ከ1.15 ወደ 0.86 ዝቅ ሲል በተቃራኒው አምና በጨዋታ በአማካይ 1.15 ጎል ይቆጠርበት የነበረው ቡድን ዘንድሮ ይህን ቁጥር ወደ 0.86 ማውረድ ችሏል ።

የመጀመሪያው ዙር የቡድኑ አቀራረብ

የአሰልጣኝ አለማየሁ ኣባይነህ ቡድን የ 4 1 3 2 እና የ 4 1 4 1 አጨዋወት ተጠቃሚ ነው ። የተከላካይ አማካዩ ሙላለም ጥላሁን ከአራቱ ተከላካዮች ፊት መጫወት የተለመደ ሲሆን የቡድኑ ቅርፅ ከፊት በሚጠቀማቸው አጥቂዎች ቁጥር ላይ ተመስርቶ ይለዋወጣል ። አዲስ ግዳይ ከግራ መስመር እየተነሳ በሚጫወትባቸው አጋጣሚዎች ላይ ከቀሩት ሶስት የአጥቂ አማካዮች ጋር ተደምሮ ቡድኑ ከአጥቂ መስመር ተሰላፊው እና ከተከላካይ አማካዩ መሀል አራት ተጨዋቾችን ሲጠቀም የ 4-1-4-1 ቅርፅን ይይዛል ። አዲስ ከፊት ከሚሰለፈው አጥቂ ኤሪክ ሙራንዳ ወይም ላኪ በሪለዱም ሳኒ ጋር ሲጣምር ደግሞ ቅርፁ ወደ 4 1 3 2 ይመጣል ። ሲዳማዎች የአማካይ ክፍል በቴክኒኩ ረገድ የዳበረ መሆኑ ለቡድኑ ዋነኛ የማጥቂያ አማራጭ መፍጠሪያ ያደርገዋል ከዛ ውጪ ሲዳማዎች ከመስመር አማካይዮቻቸው የሚሰነዝሩትም ጥቃት ሌላ አማራጭ ይሰጣቸዋል።

ጠንካራ ጎን

የሲዳማ ቡና የተከላካይ መስመሩ አንዱ ጥንካሬው ነው ። በተለይ  በሜዳው ካደረጋቸው ስምንት ጨዋታዎች የተቆጠረበት የግብ መጠን  ሁለት ብቻ መሆኑ ለመከላከል አደረጃጀቱ ጥንካሬ ዋና መገለጫ  ነው ። የአንተነህ ተስፋዬን ጉዳት ተከትሎ የተፈጠረው ጠንካራው የሰንደይ ሙቱኩ እና የአበበ ጥላሁን የመሀል ተከላካይ ውህደት ለዚህ አንዱ ምክንያት ሲሆን የሙሉአለም መስፍን ተገቢውን ሽፋን ለተከላካይ ምስመሩ መስጠት እና የመስመር አማካዮቹ የመከላከል ተሳትፎም አብሮ የሚነሳ ነጥብ ነው ።

አጠቃላይ የሲዳማዎች የጨዋታ አቀራረብ መከላከልን መሰረት ያደረገ በመሆኑ የተጋጣሚን የአጥቂ ክፍል ከእንቅስቃሴ ውጪ ለማድረግ የሚጠቀሙበት መንገድ እንደተጋጣሚው ሁኔታ የሚቀረፅ እና በጣም ጥሩ የቦታ አጠባበቅ ካላቸው ተከላካዮቹ ብቃት ጋር ተዳምሮ ሲዳማን በሜዳው በቀላሉ ግብ ማይቆጠርበት ክለብ አድርገውታል ።

ሲዳማ ቡና ጠባብ ክፍተት በሚኖርበት እና ክፍተቶች በተጋጣሚ ተከላካዮች በሚያዙበት በላይኛው የሜዳ ክፍል ላይ በንፅፅር የተሻለ የተሳካ የኳስ ቅብብል ሲያደርግ ይታያል ። ይህም በግል ክህሎት ላቅ ያሉ አማካዮችን ከመጠቀሙ ጋር የተያያዘ ጠንካራ ጎኑ ነው ። ከኋላ በኩል ያለው የቡድኑ ጠንካራ ሽፋን ለአማካዮቹ ነፃነት ከፍ ማለት ያለው አስተዋፅኦም ከፍ ያለ ነው ።

 

ደካማ ጎን

ከሜዳው ውጪ ሲዳማ የሚያስመዘግበው ውጤት ሜዳው ላይ ካለው ጋር እጅግ የተራራቀ ነው። በሰባት የሜዳ ውጪ ጨዋታዎችም ቡድኑ ማሸነፍ የቻለው አዲስ አበባ ከተማን ብቻ ሲሆን በሁለት ጨዋታዎች ነጥብ ከመጋራቱ ውጪ በቀሪዎቹ በአራቱ ተሸንፏል ። ድክመታቸው ድል ባለማስመዝገብ ብቻ ሳይሆን ግብ ባለማስቆጠሩም ጭምር ነው። በዚህም በሰባቱ ጨዋታዎች ሶስት ጊዜ ብቻ ነበር ኳስና መረብን ማገናኘት የቻሉት ። የሲዳማ ቡና የመከላከል አጨዋወት በነዚህ አጋጣሚዎች ብዙ ግቦችን ከማስተናገዱ  በተጨማሪ ለቡድኑ ዝቅተኛ ግብ የማስቆጠር እና በቂ እድሎችን ያለመፍጠር ሂደትም እንደ ምክንያትነት ይነሳል።

ሲዳማዎች ወደማጥቃት የሚያደርጉት ሽግግር ደካማነት ተጨዋቾቹ ከራሳቸው ሜዳ ወጥተው የተጋጣሚያቸው ሳጥን ውስጥ በፍጥነት ደርሰው ጥቃት እንዳይፈፅሙ ሲያደርጋቸው ይስተዋላል። ይህ ወደ ተከላካይ መስመሩ የተጠጋው የአማካይ ክፍሉ አቋቋም ቡድኑን ለማጥቃት ሰፊ ርቀት ለመሸፈን ሲያስገድደው እና በብቸኝነት የሚሰለፈውን የፊት አጥቂም በተደጋጋሚ ከግብ ጠባቂዎች ጋር ለማገናኘት እንዲቸገር አድርጎታል።

የቡድኑ የፊት መስመርም የተጨዋቾች ምርጫ እጥረት ይታይበታል። ክለቡ በረከት አዲሱን ማገዱ እና የኤሪክ ሙራንዳን ውል በቶሎ አለማድሱን እንዲሁም ፈጣኑን አዲስ ግዳይን በመስመር አማካይነት እየተጠቀመ መሆኑን ተከትሎ በተወሰኑ ጨዋታዎች ላይ በአጥቂ መስመር ላይ በላኪ በሪለዱም ሳኒ ብቻ እንዲጠቀም አስገድዶታል።  ይህ ነጥብም ሲዳማ ቡና በቂ ግቦችን እንዳያቆጥር እና የሚሰበስባቸውን ነጥቦችም ግቦችን በብዛት ከማስቆጠር ይልቅ የመከላከል አጨዋወቱን በመጠቀም የሚያሳካቸው እንዲሆኑ አድርገውታል ። በዚህም የተነሳ ይመስላል ከአንድ በላይ ግብ የሚያቅጥሩበት ቡድኖች ላይ ምላሽ ለመስጠት ሲቸገር ይታያል።

በሁለተኛው ዙር ምን ይጠበቃል ?

ሲዳማ ቡና በዲስፕሊን ጉዳይ ምክንያት ኮንትራቱን ያቋረጠበትን የበረከት አዲሱን ቦታ ለመተካት ከጋቦን አንድ አጥቂ አምጥቶ ቢያስሞክርም አጥቂው የተፈለገው ደረጃ ላይ ባለመገኘቱ ክለቡ ሳያስፈርመው ቀርቷል ። ከዚህ በተጨማሪ ሀገር ውስጥ ካሉ ክለቦች ላይ ተጨዋቾችን ለማስፈረም እየጣረ እንደሆነ እየተሰማ ይገኛል ። የአሰልጣኝ አባይነህ ጥላሁን ቡድን ያለበት ደረጃ እና የሰበሰበው የነጥብ ብዛት ሲታይ ለሻምፒዮንነት በሚደረገው ፉክክር ውስጥ እንዳለበት መናገር ይቻላል ። በሁለተኛው ዙርም በፊት መስመር ያለበትን ችግር ካስተካከለ እንዲሁም ከሜዳው ውጪ በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ላይ ነጥቦችን ካሳካ በውድድር አመቱ አዲስ ነገር የመስርልት አቅሙ አለው ።

 


መጀመሪያው ዙር የቡድኑ ኮከብ ተጨዋች ሙሉአለም መስፍን

ግዙፉ የቀድሞው የአርባምንጭ ከተማ የተከላካይ አማካይ በሲዳማ ቡና ሁለተኛ አመቱን በምርጥ ብቃት እያሳለፈ ይገኛል ። ተጨዋቹ ከተከላካይ መስመር ፊት በመሆን በሜዳው ስፋት እና ቁመት የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን በመመከት እንዲሁም ከአጥቂ አማካዮች ወደ አጥቂዎች የሚላኩ ኳሶችን በማቋረጥ እና  በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች አሸናፊ በመሆን ለአጠቃላይ የቡድኑ ዋነኛ ጥንካሬ ሲሆን ተመልክተነዋል ።

ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ያሳየ – ፀጋዬ ባልቻ

ዘንድሮ ከተስፋ ቡድኑ ያደገው ፀጋዬ ባልቻ በመጀመሪያው ዙር ባገኛቸው አጋጣሚዎች ጥሩ ተንቀሳቅሷል ። በግራ መስመር ወደ አዲስ ግደይ በኩል የሚያመዝነውን የቡድኑን የጥቃት መስመር በቀኝ ክንፍ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ሚዛኑን እንዲጠብቅም ጥረት አድርጓል። ከቀኝ መስመር በረጅሙ የሚልካቸው ኳሶች የግብ እድል ሲፈጥሩም ተስተውሏል፡፡

Leave a Reply