ቻምፒየንስ ሊግ | አሰልጣኝ ጂያን ሉዊ እና አማካዩ ጃን ቲጋና ስለነገው ጨዋታ ይናገራሉ

የኢትዮጵያው ተወካይ ቅዱስ ጊዮርጊስ የሲሸልሱን ኮት ደኦርን ሀዋሳ ላይ በካፍ ቶታል ቻምፒየንስ ሊግ የቅድመ ማጣሪያ የመልስ ጨዋታ ያስተናግዳል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በሳላዲን ሰዒድ ሁለት ግቦች ታግዞ 2-0 ፕራስሊን ላይ ማሸነፉን ተከትሎ የሲሸልሱ ቻምፒዮን ወደ ቀጣዩ ዙር የማለፉ እድል በጣም የጠበበ ይመስላል፡፡

የኮት ደኦር አሰልጣኝ ራልፍ ጃን ሉዊ ብድናቸው በቂ እና ጠንካራ የሆነ ፉክክር ማግኘት አለመቻሉ በኢንተርናሽናል ጨዋታ ላይ እንዳደከማቸው ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡ “ዝግጅታችንን ከጥር 2 ጀምሮ ነው በተጠናከረ መልኩ ማድረግ የጀምርነው ቢሆንም የሃገር ውስጥ የሊግ ውድድር አለመኖሩን ተከትሎ ጨዋታዎችን ለማግኘት ስንቸገር ነበር፡፡ ልምምዳችን ከጀመርን በአምስተኛው ሳምንት ነው ጠንካራ የሆነ ጨዋታ ያደረግነው እሱንም ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ነበር፡፡ በውጤቱም 2-0 ተሸንፈናል፡፡ በዚህ ሳምንት ተጋጣሚያች የሚጫወተውን የጨዋታ እቅድ ለማጥናት እና ለመላመድ ስራዎች ስንሰራ ነበር፡፡ ካለፈው ሳምንት የተሻለ ውጤት ለማምጣት ነው እቅዳችን፡፡”

ጂያን ሉዊ ለኢትዮጵያዊያን ተጋጣሚዎች አዲስ አይደሉም፡፡ ሲሸልሳዊው አሰልጣኝ ከዚህ ቀደም ሴንት ሚሼል እና የሲሸልስን ብሄራዊ ቡድን እያሰለጠኑ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ችለዋል፡፡ አሰልጣኙም በቅርብ ግዜያት በተደጋጋሚ ከኢትዮጵያዊያን ተጋጣሚዎች ጋር መጫወታቸው እንደሚጠቅማቸው አምነዋል፡፡ “እዚህ የመጣነው ጥሩ ውጤት ለማምጣት ነው፡፡ እናውቃለን በጣም ከባድ መሆኑን ምክንያቱም ቅዱስ ጊዮርጊስ በሜዳው እና ደጋፊው ፊት ነው የሚጫወተው፡፡ እኛ እዚህ የተገኘነው ከባለፈው ሳምንት የተሻለ እንቅስቃሴ ለማሳየት ነው፡፡ በተመሳሳይ ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ ነው፡፡ በዛው ልክ የራስ መታማመናችንን ለማሳደግ ጨዋታው ይጠቅመናል ምክንያቱም በ26 የቻሪቲ ካፕ ጨዋታ (የሲሸልስ የአሸናፊ አሸናፊዎችዋንጫ) ከሴንት ሚሼል ጋር አለብን፡፡ ስለዚህ ለዚህም እንደ መዘጋጃ ይሆነናል እንዲሁም ካለፈው ጨዋታ የምናገግምበት ይሆናል፡፡”

የኮት ደኦር ቡድን ሀዋሳ በነበረው የልምምድ ግዜ መስመር ጥቃቶችን መከላከል፣ ኳስ ከኃላ ተመስርቶ እንዳይመጣ የማድረግ እና ወደ ግብ አክርሮ የመምታት ልምምዶችን ሲሰሩ ነበር፡፡ ጃን ሉዊ ይህ በእሁዱ ጨዋታ ቀዳሚ የጨዋታ እቅዳቸው ሙሉበሙሉ እንዳማይሆን ተናግረዋል፡፡ “እኒን ብቻ ለእቅድነት አላዘጋጀነም፡፡ ብዙ እቅደችን እየተገበርን ነው፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስም በዛው ልክ የተለየ አቀራረብ ሊኖረው ስለሚችል እኛም በዚሁ የተለያዩ ነገሮችን እየሞከርን ነው፡፡ በመጀመሪያው ጨዋታ ይህን ቅዱስ ጊዮርጊስ ሲተገብር ተመልክተናል፡፡ እነሱ አቀራረባቸውን ከለወጡ እኛም እንለወጣለን ምክንያቱም በሰፊ ግብ መሸነፍ አንፈልግም፡፡”

ለአስርት አመታት በላይ በሲሸልስ እግርኳስ የሰሩት ጃን ሉዊ በአፍሪካ ይሁን በአለም እግርኳስ እምብዛም በማትታወቀው የህንድ ውቅያኖስ ደሴት ሃገር ትልቅ ስም እና ስኬት አላቸው፡፡ “የኔ ስኬት የመጣበት ምክንያት ሚስጥር አይደለም በጠንካራ ስራ እና ዲስፕሊን ነው፡፡ የኮት ደኦር ተጫዋቾች ሁሌም ሳሰለጥናቸው ምን ይላሉ መሰለህ አንተ ይህንን የተማርከው ከ20 ዓመታ በፊት ነው እኛን ይህንን ነገር በፍጥነት ልንላመድ አንችልም ይላሉ፡፡ በእርግጥ እኔ ወደምፈልገው ነገር እየመጡ ነው አሁን ቀስበቀስ፡፡”

ጃን ሉዊ ጥሩ የቴክኒክ ብቃት እና ፍጥነት ያላቸው ተጫዋቾች በሲሸልስ አለመኖራቸውን ተከትሎ ብድናቸው በአንድ ሰው ላይ እንዲንጠለጠል አይፈልጉም፡፡ በህብረት መጫወት የመጀመሪያ ምርጫዋቸው እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

ጃን ቲጋና

የኮት ደኦሩ ማዳጋስካራዊ አማካይ ጃን ቲጋና ከሁለት ዓመት በፊት ባህርዳር ላይ ክለቡ በደደቢት በካፍ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ 2-0 ሲረታ የጨዋታው ኮከብ ተብሎ ተመርጦ ነበር፡፡ ጋቦን እና ኤኳቶሪያል ጊኒ በጣምራ ባስተናገዱት የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ላይም ኢትዮጵያ ማዳጋስካርን 4-2 ስትረታ የሃገሩን መለያ ለብሶ መጫወት ችሏል፡፡

ቲጋና በመጀመሪያው ጨዋታ በቅዱስ ጊዮርጊስ በሜዳቸው መሸነፋቸውን ተከትሎ ውጤቱን ለመቀየር እንደተዘጋጀ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግሯል፡፡ “ጥሩ ውጤት ለማምጣት ብድናችን ጠንካራ ዝግጅት ስናደርግ ነበር፡፡ የመጀመሪያ ጨዋታችንን በመሸነፋችን አሁን ላይ በተሻለ እንድንጫወት ስለሚያደርገን ለዚሁ የሚመጥን ዝግጅት አድርገናል፡፡ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እንጥራለን” ብሏል፡፡

ቲጋና ሲቀጥል ከሁለት አመት በፊት ያሳየው ድንቅ እንቅስቃሴ የመድገም ፍላገት እንዳለው ተናግሯል፡፡ “ለእግርኳስ ወዳዶች ሁሉ የተሻለ መጫወት እንደምችል ለማሳየት ፍላጎት አለኝ፡፡ ምክንያቱም የእኔ አላማ ከኮት ደኦር የተሻለ ክለብ የመግባት እና የመጫወት ነው፡፡ ለዚህም በእንደዚህ ዓይነት ጨዋታዎች ላይ እራሴን ማስመስከር አለብኝ፡፡” ሲል ሃሳቡን አጠናቅቋል፡፡

 

Leave a Reply