ማሜሎዲ ሰንዳውንስ የካፍ ሱፐር ካፕ አሸናፊ ሆኗል

ማሜሎዲ ሰንዳውንስ ቲፒ ማዜምቤን 1-0 በማሸነፍ የ2017 ካፍ ሱፐር ካፕ ዋንጫ አንስቷል፡፡ የደቡብ አፍሪካ ቻምፒዮን ሱፐር ካፑን ከኦርላንዶ ፓይሬትስ ቀጥሎ ያሸነፈ ሁለተኛው ደቡብ አፍሪካም ክለብ ሆኗል፡፡ የብራዚላዊው ሪካርዶ ናሲሜንቶ የሁለተኛው አጋማሽ የፍፁም ቅጣት ምት ግብ የሁለቱ ክለቦች ልዩነት ነበር፡፡

የብራዚሎቹ የጨዋታ የበላይነት በታየበት ፍልሚያ ለግብ የቀረበ ሙከራ በማድረግ ቅድሚያውን የያዙት ቲፒ ማዜምቤዎች ነበሩ፡፡ በዘጠነኛው ደቂቃ ማላንጎ ከኦኒያንጎ ጋር ብቻውን ቢገናኝም ሙከራውን የግቡ አግዳሚ መልሶበታል፡፡ የተመለሰውን ኳስ ማላንጎ አሁንም ከቅርብ ርቀት ቢመታም ኦኒያንጎ በድንቅ ቅልጥፍና ወደ ግቡ አግዳሚ ኳሷ እንድትሆድ አድርጓል፡፡ ቀስበቀስ ወደ ጨዋታው ምት መግባት ያቻሉት ሰንዶውንሶች በካሃማ ቢሊያት አማካኝነት ወደ ግብ ሞክረዋል፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ የማዜምቤ የኃላ መስመር የፐርሲ ታኦ እና ቢሊያትን ለመቆጣጠር ሲቸግረው ተስተውሏል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ከረጅም ግዜ እገዳ በኃላ ወደ ቀድሞ ክለቡ የተመለሰው ትሬዘር ማፑቶ ዳግም በማዜምቤ መለያ ወደ ሜዳ ተቀይሮ ገብቷል፡፡ ቢሆንም በሁለተኛው 45 የጨዋታ እንቅስቃሴ የበላይነትን የያዙት ብራዚሎቹ ነበሩ፡፡ ባለሜዳዎቹ የተጋጣሚያቸውን ቁልፍ ተጫዋቾች የሆኑትን ሰለሞን አሳንቴ፣ ናታን ሲንካላ እና ሬንፎርድ ካላባን መቆጣጠር መቻላቸው ለድል አብቅቷቸዋል፡፡ ኮትዲቯረዊው የቲፒ ማዜምቤ ግብ ጠባቂ ሲልቪያን ጎቦሆ የአንቶኒ ላፎርን እና ፐርሲ ታኦ ሙከራዎችን ቢያመክንም ጨዋታው ሊጠናቀቅ 9 ደቂቃዎች ሲቀሩት ሆሎምፖ ኬካና ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ሪካርዶ ናሲሜንቶ በሚገባ ተጠቅሞ ማሜሎዲ ሰንዳውንስን ለድል አብቅቷል፡፡

ሰንዳውንስ ሱፐር ካፑን በማሸነፉ የ100000 ሺህ የአሜሪካ ዶላር በሽልማት መልክ ሲያገኝ ተሸናፊው ቲፒ ማዜምቤ 75ሺህ ዶላር ያገኛል፡፡ ማሜሎዲ ሰንዳውንስ ኦርላንዶ ፓይሬትስን ተከትሎ የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ እና ሱፐር ካፕን ያሳካ ሁለተኛው የደቡብ አፍሪካ ክለብ ነው፡፡ የክለቡ አሰልጣኝ ፔትሶ ሞሴማኔ በስኬት ጉዳና ቡድናቸውን መምራት ቀጥለዋል፡፡ ሰንዳውንስ የደቡብ አፍሪካ ፕሪምየር ሶከር ሊግ የሪከርድ አሸናፊ ነው፡፡ በቻምፒየንስ ሊጉ አምና በዲ.ሪ. ኮንጎው ኤኤስ ቪታ ክለብ እንዲሁም ከኮንፌድሬሽን ዋንጫ በጋናው ሚዲአማ ተሸንፎ ወደ ምድብ ማለፍ ሳይችል ቀርቶ ነበር፡፡ ነገር ግን በቻምፒየንስ ሊጉ ጨዋታ ኤኤስ ቪታ ክለብ ያለተገባ ተጫዋች በማሰለፉ ካፍ ሰንዳውንስ ዳግም ወደ ውድድሩ መልሷል፡፡ ይህንን ሁለተኛ እድል የደቡብ አፍሪካው ክለብ በሚገባ በመጠቀም የአፍሪካ ክለቦች ቻምፒዮን ሆኗል፡፡ ማሜሎዲ ሰንዳውንስ የቻምፒየንስ ሊግ ክብሩን ለማስጠበቀ በመጀመሪያው ዙር ከአንጎላው ክለብ ዴስፖርቲቮ ደ አውጉስቶ  እና ከዩጋንዳው ኬሲሲሰኤ አሸናፊ ጋር ይጫወታል፡፡

Leave a Reply