የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 1ኛ ዙር የክለቦች ዳሰሳ – ወላይታ ድቻ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመርያ ዙር መጠናቀቅን ተከትሎ ሶከር ኢትዮጵያ ክለቦችን በተናጠል በመዳሰስ ላይ ትገኛለች፡፡ አንደኛውን ዙር በ10ኛ ደረጃ ያጠናቀቀው ወላይታ ድቻ የውድድር ዘመን አጋማሽ ጉዞ በአብርሃም ገብረማርያም እና ሚልኪያስ አበራ እንዲህ ተዳሷል፡፡

የውድድር ዘመኑ ጉዞ

የወላይታ ድቻ አጀማመር መልካም የሚባል ነበር፡፡ በተከታታይ በሜዳው ባደረጋቸው ጨዋታዎች መከላከያ እና አዳማ ከተማን ማሸነፍ የቻለው ድቻ (በ2ኛው ሳምንት ከፋሲል ጋር በወቅቱ አልተጫወተም) 4ኛው ሳምንት ላይ በሲዳማ ቡና ከተሸነፈ በኋላ ግን ክለቡ ድል ለማስመዝገብ የሚቸገር ቡድን ሆኗል፡፡ በሜዳው ከቡና እና ድሬዳዋ አቻ ሲለያይ ከሜዳው ውጪ በቅዱስ ጊዮርጊስ ተሸንፏለ፡፡ በ8ኛው ሳምንት ወልድያን እስኪያሸንፍ ድረስ ከድል ርቆ ቆይቷል፡፡ በ9ኛው ሳምንት አቻ እንዲሁም በ10ኛው ሳምንት ድል ካስመዘገበ በኋላ ወላይታ ድቻ እና ድል ሳይገናኙ አንደኛው ዙር ተጠናቋል፡፡ ከ6 የመጨረሻ ጨዋታዎችም (በፋሲል የተሸነፈበትን ተስተካካይ ጨዋታ ጨምሮ) 4 ተሸንፎ 2 አቻ ተለያይቷል፡፡

 የዘንድሮው ውጤት ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር

የቡድኑ የአምና እና የዘንድሮው ውጤት ከፍተኛ ልዩነት አለው፡፡ አምና 4ኛ ደረጃ ይዞ የመጀመርያውን ዙር ያጠናቀቀው ድቻ ዘንድሮ 10ኛ ሆኖ አጠናቋል፡፡

ወላይዣ ድቻ ዘንድሮ ያስመዘገበው 17 ነጥብ (በጨዋታ በአማካይ 1.1 ነጥብ) አምና ካስመዘገበው 20 ነጥብ (በጨዋታ በአማካይ 1.5 ነጥብ) ያነሰ ነው፡፡ አምና በጨዋታ በአማካይ 1 ጎል የሚያስቆጥረው ቡድን ዘንድሮ ወደ 0.8 ሲወርድ ከአምናው ጋር ተቀራራቢ ሪኮርድ ያለው በመከላከል ሪኮርዱ ነው፡፡

የቡድኑ የጨዋታ አቀራረብ

ከዚህ ቀደም በ3-5-2 የተጫዋቾች የሜዳ ላይ አደራደር የሚጠቀሙት አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ በውድድር ዘመኑ በርካታ አሰላለፎችን ቢጠቀሙም በአብዛኛው 3-4-3ን ዋንኛ የሜዳ ላይ አደራደር አድርገው ተጠቅመዋል፡፡ ከሶስቱ የመሃል ተከላካዮች ፊት 4 በሜዳው ስፋት የሚደረደሩ አማካዮች ይጠቀማሉ፡፡ ከፊትም ከአማካዮች ጋር በሚመሳሰል ቅርጽ 3 አጥቀዎች ይሰለፋሉ፡፡ ይህ አሰላለፍ ለቡድኑ አዲስ በመሆኑ ተጫዋቾች የሚና ግርታ ውስጥ ሲገቡ ይታያል፡፡ በተለይ የመስመር ተመላላሾቹ ቡድኑ ከማጥቃት ወደ መከላከል እንዲሁም ከመከላከል ወደ ማጥቃት በሚያደርገው ሽግግር ላይ የሚኖራቸው ተሳትፎ እምብዛም ነው፡፡

ጠንካራ ጎን

የአሰልጣኝ መሳይ በጨዋታ አቀራረብ አዳዲስ ነገሮችን ለማሳየት የሚያደርጉት ጥረት የሚያስመሰግናቸው ነው፡፡ 3-4-3 ፣ 3-5-2 እና 4-3-3 አሰላለፍን ተግባራዊ ሲያደርጉ ተስተውሏል፡፡ የፊት መስመር ተሰላፊዎች በተከላካዮች ላይ የሚያሳድሩት ጫና እና ተጫዋቾችን የሚይዙበት መንገድ የተጫዋቾች የታክቲክ አረዳድን ያመላክታል፡፡

አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ዘንድሮም በርካታ አዳዲስ ፊቶችን ለሊጉ አስተዋውቀዋል፡፡ ከፍተኛ ገንዘብ በሚወጣበት ሊግ የሚበጀትላቸውን ጥቂት ገንዘብ በአግባቡ ተጠቅመው ከታችኞቹ ሊጎች ያመጧቸው ተጫዋቾች ደረጃ ከሌሎች እንደማያንስ ማሳየታቸው እንደጠንካራ ጎን የሚወሰድና ለሌሎች ትምህርት የሚሆን ነው፡፡

የአጥቂዎቹ የመከላከል ባህርይ በጠንካራ ጎኑ ሊነሳ የሚገባው ሌላው ነጥብ ነው፡፡ ከፊት የሚገኙት ሶስት ተጫዋቾች (በዛብህ ፣ አላዛር ፣ ጸጋዬ) በተከላካዮች መሀል ያለው ክፍተት (Channels) ላይ በመቆም የተጋጣሚያቸውን እንቅስቃሴ ለማፈን እና ስህተት እንዲፈጥሩ ለማስገደድ የሚያደርጉት ጥረት መልካም የሚባል ነው፡፡ በዚህ እንቅስቃሴ በሚፈጠሩ ስህተቶችም የግብ እድሎችን ሲፈጥሩ ተስተውሏል፡፡ አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ይህንን እንቅስቃሴ እንዲተገብሩ በጨዋታ መሀል ለተጫዋቾቻቸው በምልክት ሲናገሩ መስተዋሉም የታቀደበት እንደሆነ መናገር ይቻላል፡፡

ደካማ ጎን

ከዚህ ቀደም ጥብቅ ፣ በመልሶ ማጥቃት የሚጫወት እና ለተጋጣሚ ክፍተት የማይሰጠው ወላይታ ድቻ ዘንድሮ በተቃራኒው ኳስ ለመቆጣጠር እና ለማጥቃት የሚሞክር ቡድን ሆኗል፡፡ ይህ ሽግግርም ቡድኑ ላይ በርካታ ክፍተቶች እንዲኖሩ አድርጓል፡፡ ቡድኑ ወደ ማጥቃት በሚሸጋገርበት ወቅት በተጋጣሚ የሜዳ ክፍል የሚገኙት ተጫዋቾች ቁጥር ዝቅተኛ ሲሆን የሚስተዋለው ከቀድሞ አጨዋወቱ ለመላቀቅ በመቸገሩ ነው፡፡ ተጋጣሚ ኳስ ከኋላ በሚጀምርበት ወቅት ጫና ለመፍጠር የሚሞክሩት አጥቂዎቹ ብቻ ሲሆኑ አማካዮቹ ወደ ኋላ በጥልቀት በማፈግፈግ የአጥቂዎችን ጥረት መና ሲያስቀሩ ይስተዋላል፡፡ የተጋጣሚ ተከላካዮችም በነጻነት ኳስ መስርተው እንዲጫወቱ ይፈቅዳሉ፡፡

ከሜዳ ውጪ ያለው የቡድኑ ውጤት እጅግ ዝቅተኛ ነው፡፡ ካደረጋቸው 7 የሜዳ ውጪ ጨዋታዎች 5 ጨዋታዎችን በሽንፈት ሲያጠናቅቁ ከንግድ ባንክ እና ሀዋሳ ከተማ ጋር አቻ ቢለያዩም 5 ግቦች አስተናግደዋል፡፡ ለቡድኑ ከሜዳ ውጪ ውጤት ማጣት እንደከዚህ ቀደሙ ጥብቅ አጨዋወት አለመተግበሩ በምክንያትነት ሊጠቀስ ይችላል፡፡

የአሰልጣኝ መሳይ በጉዳት አስገዳጅነት ቢሆንም የመጀመርያ ተሰላፊዎች ምርጫቸው ወጥ አለመሆን ለቡድኑ ደካማ ጉዞ ተጠቃሽ ነው፡፡ በተለይ በተከላካይ መስመር የሚጣመሩ ተጫዋቾች ከጨዋታ ጨዋታ መለዋወጥ እርጋታ እንዳይታይበት አድርጎታል፡፡ አሰልጣኝ መሳይ በውድድር ዘመኑ አጋማሽ በርካታ አቀራረቦችን መሞከራቸው ቢያስመሰግናቸውም የሚመርጡት ፎርሜሽን ከተጫዋቾቹ ባህርይ ጋር የማይጣጣሙባቸው ወቅቶች ነበሩ፡፡ ይህ ደግሞ ከተጫዋቾች መፈራረቅ ጋር ተደማምሮ ቡድኑ ውህደት እንዳይታይበት አድርጎታል፡፡

በሁለተኛው ዙር ምን ይጠበቃል?

የቡድኑ ተጫዋቾች ከአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ  ሲስተም ጋር ይበልጥ ተላምደው በሁለተኛ ዙር ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ አዳዲሶቹ እና ወጣቶቹ ተጫዋቾች ይበልጥ ሊጉን እየተላመዱ በመሆኑ ቡድኑ በሁለተኛው ዙር ተሻሽሎ የመቅረብ እድል አለው፡፡

የ1ኛ ዙር ኮከብ ተጫዋች – በዛብህ መለዮ

ባለፉት የውድድር ዘመናት ወጣ ገባ እንቅስቃሴ ሲያሳይ የነበረው በዛብህ ዘንድሮ በወጥ አቋም ላይ ይገኛል፡፡ ግቦችን በማስቆጠር እና የግብ እድሎቸችን በመፍጠርም የቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴ መሪ ተዋናይ ሆኗል፡፡ በዛብህ በሁለም ጨዋታዎች ላይ ከመሰለፉ ባሻገር 4 ጎሎችን በስሙ ማስመዝገብና 3 ጎል የሆኑ ኳሶች አመቻችቶ ማቀበል ችሏል፡፡

ተስፋ የሚጣልበት – ፉአድ ተማም

አምና በብሄራዊ ሊጉ የማጠቃለያ ውድድር ለካፋ ቡና ባሳየው ድንቅ ብቃት ወላይታ ድቻን መቀላቀል የቻለው ፉአድ በአንደኛው ዙር የመጨረሻ ጨዋታዎች ላይ የመሰለፍ እድል አግኝቶ ጥሩ መንቀሳቀስ ችሏል፡፡ አጥቂው በሁለተኛው የውድድር ዘመን አጋማሽ ከመጀመርያው የተሻለ የመሰለፍ እድል እንደሚያገኝ የሚጠበቅ በመሆኑ ለቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴ ተጨማሪ ሃይል መሆን ይችላል፡፡

1 Comment

  1. woww…..tnx betam temechitognal wolayta dicha teshashilo ende mimeta tesfa adergalewu….hulrme dicha 1

Leave a Reply