የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 1ኛ ዙር የክለቦች ዳሰሳ – ወልድያ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመርያ ዙር መጠናቀቅን ተከትሎ ሶከር ኢትዮጵያ ክለቦችን በተናጠል በመዳሰስ ላይ ትገኛለች፡፡ አንደኛውን ዙር በ9ኛ ደረጃ ያጠናቀቀው ወልድያ የውድድር ዘመን አጋማሽ ጉዞ በዮናታን ሙሉጌታ እና ሚልኪያስ አበራ እንዲህ ተዳሷል፡፡

የመጀመሪያ ዙር የወልድያ ጉዞ

አምና ከከፍተኛ ሊጉ ማደግ የቻለው ወልድያ ዘግይቶ ወደ ገብያ ቢገባም ዘጠኝ ተጨዋቾችን በማስፈረም በአሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ እየተመራ ነበር የዘንድሮውን ውድድር የጀመረው። በሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታም ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን መልካ ቆሌ ስቴድየም  ላይ 1-0 በማሸነፍ ቢጀምርም ሁለተኛ ድል ለማስመዝገብ ግን በስታድየሙ ለመጨረሻ ጊዜ ባደረገው እና ኢትዮጵያ ቡናን በተመሳሳይ ውጤት እስከረታበት የዘጠነኛ ሳምንት ጨዋታ ድረስ መጠበቅ ነበረበት ። በመሀል በተደረጉት ሰባት ጨዋታዎችም ወልድያ አራት ጊዜ አቻ መውጣት ቻለ እንጂ በሌሎቹ ሽንፈትን ነበር ያስተናገደው።

ወልዲያ ከኢትዮጵያ ቡናው ድል በኋላ በቅድስ ጊዮርጊስ አስረኛ ሳምንት ላይ ከመሸነፉ በቀር በቀሪ የሊጉ ጨዋታዎች መሻሻላን አሳይቶ ነበር የመጀመሪያውን ዙር ያጠናቀቀው። ከአዲሱ መሀመድ ሁሴን አሊ አላ ሙዲን ስቴድየም ምርቃት በኋላ በተደረጉ የመጨረሻዎቹ አምስት ጨዋታዎችም ወልድያ ጅማ አባ ቡናን እና ሀዋሳ ከተማን ድል አድርጎ ቀሪዎቹን ሶስት ጨዋታዎች አቻ መውጣት ችሏል ። በእነዚህ ጨዋታዎች ባሳካቸው ነጥቦች ታግዞም ከወራጅ ቀጠና በመውጣት ግማሽ አመቱን በዘጠነኛ ደረጃ ላይ በመቀመጥ አጠናቋል።

የመጀመሪያው ዙር የቡድኑ አቀራረብ

የወልድያ አጨዋወት በዋነኝነት በመከላከል ላይ የተመሰረተ ነው ። በአብዛኞቹ ጨዋታዎችም የቡድኑ ቅርፅ በ 4-4-2 የተጨዋቾች አደራራደር የተቃኘ ነበር ። ለአራቱ ተከላካዮች በጣም ቀርቦ የሚታየው የአማካይ ክፍል በማጥቃት ላይ በሚሰማራበት ወቅት የቡድኑን ቅርፅ ወደ 4-1-3-2 የሚወስደው ሲመስል ከሁለቱ የፊት አጥቂዎች አንደኛው ከኋላ ርቆ ከሚገኘው አማካይ መስመር ጋር ለመገናኘት የሚያደርገው ጥረት ወልድያን የ 4-4-1-1 ቅርፅ የያዘ ያስመስለዋል ። የቡድኑ ዋነኛ የማጥቃት አማራጮችም ከጥልቅ አማካይ እና ከኋላ መስመር ውደ አጥቂዎች የሚላኩ ረጃጅም ኳሶች ነበሩ።

ጠንካራ ጎን

ወልድያ ዋነኛ ጠንካራ ጎኑ ጥብቅ የሆነው የመከላከል አጨዋወቱ ነው። የተቆጠሩበት ስምንት ግቦችም በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ አናት ላይ ከሚገኙ አራት ቡድኖች በሶስቱ  ሊያውም በአንድ ጎል ቢለያይም ዘጠነኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ወልድያ ከቀሩት ቡድኖች ሁሉ ዝቀተኛ ጎል የተቆጠረበት ክለብ ያደርገዋል። ቡድኑ ብዙ ጎል አለማስቆጠሩን ተከትሎ የሚሰበስበው ነጥብ እንዳይመናመን እና በደረጃም እንዳይወርድ የመከላከል ጥንካሬው ትልቅ አስተዋፅኦ ነበረው ። በተለይ ወልድያ ሜዳው ላይ በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ይህ ነጥብ በይበልጥ ጎልቶ ይታያል። ወልድያ በሜዳው ካደረጋቸው ስምንት ጨዋታዎች ምንም ሽንፈት አለማስተንገዱ እና የተቆጠረበትም የግብ መጠን ሁለት ብቻ መሆኑ አስገራሚ ያደርገዋል። የአሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ ቡድን ከሜዳው ውጭ ብዙ ጨዋታዎችን በሽንፈት የጨረሰ  ቢሆንም ጠንካራ የመከላከል ሪከርድ ነው ያስመዘገበው። በሰባቱ የሜዳ ውጪ የተቆጠረበት የግብ መጠን ስድስት ብቻ መሆኑ ቡድኑ ሲሸነፍ የነበረው በግብ እጥረት እንጂ በመከላከል ድክመት ላለመሆኑ ምስክር ነው።

ዘላቂ ብቃት ባላቸው እንደ አዳሙ መሀመድ ባሉ ተጨዋቾች የሚመራው የሰማያዊ እና ነጭ ለባሾቹ የመከላከል አደርጃጀት በቀላሉ የሚታለፍ አይደለም ። በተለይም በሜዳው ቁመት በተከላካይ መስመሩ እና በአማካይ መስመሩ መሀል ያለው ክፍተት ጠባብ መሆን ለተጋጣሚዎ የአጥቂ አማካዮች እንደልብ ለመጫዎት የሚያመች አለመሆኑ ቡድኑን ከቀጥተኛ ጥቃቶች ሲያድነው ማየት ተችሏል ። የህ ተጠቅጥቆ የመከላከል ባህሪ በሜዳው ስፋትም የሚታይ በመሆኑ ወልድያ በመስመር የሚያጠቁ ቡድኖችንም ለመፈተን አስችሎታል። በአጠቃላይ ቡድኑ በሚከላከልበት ሰዐት በተጨዋቾች መሀል የሚኖረው ጠባብ ርቀት እና የጠበቀ ሰው በሰው የመያዝ አጨዋወት ከፈጣን የመከላከል ሽግግር ጋር ተዳምሮ ወልድያ ላይ ግብ ማስቆጠርን ከባድ ስራ እንዲሆን አድርጎታል።

ደካማ ጎን

ወልድያ ግብ የማስቆጠር ችግር ካለባቸው ቡድኖች አንዱ ነው። በመጀመሪያው ዙር በአማካይ አንድ ግብ ለማስቆጠር ሁለት ጨዋታዎች ያስፈልጉት ነበር። ይህ ችግሩ ከማዳ ውጪ በሚደረጉ ጨዋታዎች ላይ ይበልጥ የሚታይ ሲሆን ጅማ ላይ ጅማ አባ ቡናን በሁለት ግብ ልዩነት ካሸነፉበት ጨዋታ ውጪ ወልድያዎች በ ስድስት የሜዳ ውጪ ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ነበር ማስቆጠር የቻሉት። ይህ የቡድኑ ችግር ከጨዋታ አቀራረቡ እና ከአጥቂ መስመር ተሰላፊዎች ብቃት ጋር በቀጥታ ይገናኛል።

ወልድያዎች በተለይ ከሜዳ ውጪ በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ላይ በእጅጉ ወደራሳቸው የግብ ክልል አፈግፍገው መጫወታቸው ቡድኑ የሚያገኛቸው የመልሶ ማጥቃት እድሎች የጊዜ የርቀት እና የቁጥን ችግር እንዲታይባቸው አድርጓል ። ይህም ማለት ቡድኑ ኳስ በሚነጥቅበት ወቅት ወደተጋጣሚው የሜዳ ክልል ለመግባት መሸፈን የሚጠበቅበት ረጅም ርቀት ፍጥነት ከሌለው የማጥቃት ሽግግር ጋር ተዳምሮ የሚሰነዘረው ጥቃት በላይኛው የሜዳ ክፍል ላይ በቂ ቁጥር ባላቸው ተጨዋችምች እንዳይተገባር ማድረጉ ነው። በዚህም ምክንያት ከፊት የሚገኙት የሁለቱ አጥቂዎች እንቅስቃሴ በቀላሉ በተጋጣሚ ቡድን ተጨዋቾች የቁጥር ብልጫ ሲታፈን ይስተዋላል።

ከዚህ ሌላ ሊነሳ የሚገባው ነጥብ ወልድያዎች ካስቆጠሩት ስምንት ግቦች ስድስቱ በፊት አጥቂዎች መቆጠራቸው ነው ። የቡድኑ ጎል የማስቆጠር እጣፈንታም በእድሜ መግፋት እና በቂ የተጨዋች አማራጭ ባለመያዝ በሚታማው የፊት መስመር ላይ ብቻ የተተወ መሆኑ ወልዲያዎች ለሚያስቆጥሩት የግብ መጠን አናሳነት ሌላው ምክንያት ነው። በተለይ አብዛኛውን ሰዐት በመከላከሉ አጨዋወት የሚጠመደው የአማካይ ክፍሉ የተዳከመ ግብ የማስቆጥር ሪከርድ ሊሻሻል የሚገባው ነው።

በሁለተኛው ዙር ምን ይጠበቃል ?

የአሰልጣኝ ንጉሴ ደስታው ወልድያ የደደቢቱን አጥቂ ያሬድ ብርሀኑን በውሰት ውል ለማስፈረም ተስማምቷል፡፡ አምና በመቀለ ከተማ የውሰት ጊዜን ያሳለፈው ያሬድ ለወልድያ የፊት መስመር ጥሩ አማራጭ እንደሚሰጥ ይታሰባል። ወልድያ ከዚህ ዝውውር ሌላ ተጨማሪ ዝውውር የመፈፀም ዕድል ያለው ሲሆን የቡድኑ ጠንካራ የመከላከል ብቃት በዚሁ ከቀጠለ እና ግብ የማስቆጠር ችግሩን ማሻሻል ከቻለ በሁለተኛው ዙር ይለበትን ደረጃ የማሻሻል ዕድል እንዳለው መገመት ይቻላል።

የመጀመሪያው ዙር የቡድኑ ኮከብ ተጨዋች  – አዳሙ መሀመድ

ላለፉት ስድስት አመታት በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በመጫወት ያሳለፈው ጋናዊው የመሀል ተከላካይ ዘንድሮ ወልድያ ለነበረው የኋላ መስመር ጥንካሬ ዋነኛ ተጠቃሽ ነው። አዳሙ የተከላካይ መስመሩንም ሆነ አጠቃላዩን የቡድኑን የመከላከል አደረጃጀት በመምራት ስኬታማ ጊዜን እያሳለፈ ይገኛል። ተጨዋቹ ያለበት የአካል ብቃት ደረጃ በብዙዎቹ ጨዋታዎች ላይ እንዲሰለፍ ያስቻለው ሲሆን ከተከካላካይ መስመር በመነሳትም አንድ ግብ አስቆጥሯል።

ተስፈኛ የሚጣልበት ተጨዋች – ዳንኤል ደምሴ

የውድድር አመቱ ሲጃመር ከባህርዳር ከተማ ወልድያን መቀላቀል የቻለው ዳንኤል ደምሴ ጥሩ ግማሽ አመት አሳልፏል። በሁለት አጋጣሚዎች በቀይ ካርድ ከሜዳ መውጣቱ ውጪ በብዙ የቡድኑ ጨዋታዎች ላይ በመሰለፍ በአማካይ ክፍሉ ላይ የራሱን አስተዋፅኦ ማበርከቱ ለወልድያ የሁለተኛ ዙር ጉዞ ተስፋ ያደርገዋል።

 

Leave a Reply