የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 1ኛ ዙር የክለቦች ዳሰሳ – ድሬዳዋ ከተማ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመርያ ዙር መጠናቀቅን አስመልክቶ ሶከር ኢትዮጵያ የክለቦቹን ግማሽ የውድድር ዘመን ዳሰሳ በተከታታይ 6 ቀናት ስታቀርብ ቆይታ በዚት ፅሁፍ አሳርጋለች፡፡ አብርሃም ገብረማርያም እና ሚልኪያስ አበራ በዚህ ፅሁፍ አንደኛውን ዙር በ12ኛ ደረጃ ያጠናቀቀው ድሬዳዋ ከተማን እንዲህ ባለ መልኩ ዳሰውታል፡፡

የውድድር ዘመኑ ጉዞ

ድሬዳዋ ከተማ አምና በ2ኛው ዙር የተመዘገበውን ደካማ ውጤት ተከትሎ ብቸኛዋ የሊጉ ሴት አሰልጣኝ መሰረት ማኒን አሰናብቶ በአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው በመተካት ነበር የ2009 የውድድር ዘመንን የጀመረው፡፡ የድሬዳዋ ከተማን የውድድር ዘመን መልክ “ወጥነት የጎደለው” በሚል አጭር ቃል መግለጽ ይቻላል፡፡ ተከታታይ ድሎች ለማስመዝገብ የሚቸገርና በየጨዋታው ሊያስመዘግብ የሚችለው ውጤት የማይገመት ቡድን ሆኖ ታይቷል፡፡

በመክፈቻው አሜዳው ውጪ በአዳማ ከተማ 1-0 ተሸንፎ የሊግ ጉዞውን የጀመረው ድሬዳዋ በሁለተኛው ሳምንት ኤሌከትሪክን 2-1 በመርታት ወደ ድል ተመልሷል፡፡ በመቀጠል በሲዳማ ቡና ተሸንፎ በሜዳው አዲስ አበባን በማሸነፍ አካክሷል፡፡

የህዳር ወር የቡድኑ ጉዞ ተከትሎ ቡድኑ ከሜዳው ውጪ የሚቸገር ነገር ግን በሜዳው ጨዋታዎች እያሸነፈ የሚወጣ መስሎ ነበር፡፡ ነገር ግን በ5ኛው ሳምንት ወደ ሶዶ ተጉዞ ከወላይታ ድቻ ያለ ግብ ከተለያየ በኀላ ከባድ የውድድር ዘመን ለማሳለፍ ተገዷል፡፡ በ6ኛው እና 8ኛው ሳምንት በሜዳው የተሸነፈውን ጨዋታ ጨምሮ ቡድኑ ለተከታታይ 9 ጨዋታዎች ከድል ርቆ ቆይቷል፡፡

በ14ኛው ሳምንት ፋሲል ከተማን አስተናግዶ 1-0 ካሸነፈ በኋላ ቡድኑ ላይ የማንሰራራት ተስፋ ታይቶ የነበረ ቢሆንም በ1ኛው ዙር የመጨረሻ ጨዋታ በጅማ አባ ቡና 3-0 ተረትቶ በ12ኛ ደረጃ ላይ በመቀመጥ 1ኛውን ዙር አጠናቋል፡፡

 

 ቡድኑ ከአምናው ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነጻጸር

የዘንድሮው ድሬዳዋ ከተማ በበርካታ መመዘኛዎች ከአምናው በእጅጉ የወረደ የውድድር ዘመን በማሳለፍ ላይ ይገኛል፡፡ የመሰረት ማኒው ቡድን በመጀመርያው ዙር 20 ነጥብ ማስመዝገብ ሲችል የዘላለም ሽፈራው ቡድን ማስመዝገብ የቻለው 15 ነጥብ ነው፡፡ በዚህ የውድድር ዘመን 2 ተጨማሪ ጨዋታ እንዳለ ማስተዋልም ልብ ይሏል፡፡

ድሬዳዋ በየጨዋታው የማሸነፍ እድሉ ከ46% ወደ 20% የወረደ ሲሆን በየጨዋታው የሚያስመዘግበው ነጥብም ከ1.5 ነጥብ/ጨዋታ ወደ 1 ነጥብ/ጨዋታ ወርዷል፡፡

ብርቱካናማዎቹ በግብ ማስቆጠር ረገድም ከአምናው የተዳከመ ቡድን ይዘው ቀርበዋል፡፡ አምና በጨዋታ በአማካይ 1 ጎል የሚያስቆጥረው ቡድን ዘንድሮ ከእጥፍ በላይ አሽቆልቁሎ በአማካይ የሚያስቆጥረው የግብ መጠን 0.4 ብቻ ነው፡፡ ድሬዳዋ ከአምናው የተሻሻለበት ብቸኛ መስፈርት የመከላከል ሪኮርዱ ነው፡፡ አምና በአማካይ በጨዋታ 1.2 ጎል ይቆጠርበት የነበረው ቡድን ዘንድሮ የሚቆጠርበትን መጠን ወደ 0.9/ጨዋታ ማውረድ ችሏል፡፡

የቡድኑ የዘንድሮው አቀራረብ

አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው 4-4-2 የተጫዋቾች የሜዳ ላይ አደራደርን በአመዛኝ ጨዋታዎች ላይ ተጠቅመዋል፡፡ ቡድኑ እንደየጨዋታዎቹ እና አሰልጣኞቹ እንደሚያሰልፏቸው ተጫዋቾች ባህርይ የ4-4-2 አካል የሆኑት 4-4-1-1 እና 4-1-3-2 ቅርጽ የሚታይበት ጊዜያት አሉ፡፡ ቡድኑ ከፊት ሐብታሙ ወልዴን በዋነኝነት ሲጠቀም ከሐብታሙ አጠገብ የሚሰለፈው ተጫዋች ባህርይ የአጨዋወት ቅርፁን ሲለዋውጠውም ይስተዋላል፡፡

የአማካይ መስመሩ ጠፍጣፋ ቅርጽ ሲኖረው ተለምዷዊው የሁለት የመሀል አማካዮች እና የሁለት የመስመር ተጫዋቾችን የሚጠቀም ነው፡፡ በአብዛኛው ጨዋታዎችም ይህ የአማካይ ክፍል ወደተከላካይ መስመሩ ቀርቦ እና ከሁለቱ የፊት አጥቂዎች ርቆ ይታያል ።  በዚህም ምክንያት የድሬደዋ የማጥቃት አጨዋወት በብዛት በመልሶ ማጥቃት ላይ የተመሰረተ እና ከመስመሮች የሚነሳ ነው ።

ጠንካራ ጎን

ተከላካይ መስመሩ የቡድኑ ጠንካራ ጎን ነው፡፡ ከሳምሶን ፊት የሚሰለፉት ኄኖክ አዱኛ ፣ በረከት ሳሙኤል፣ ተስፋዬ ዲባባ እና ዘነበ ከበደ በአንደኛው ዙር የነበራቸው አቋም ቡድኑ ቢያንስ አንድ ነጥብ ይዞ እንዲወጣ እና በአንድ ግብ ልዩነት አሸንፎ እንዲወጣ ያስቻለ ነበር፡፡ ድሬዳዋ በተለይ ከሜዳው ውጪ ሲጫወት አመዛኞቹ ተጫዋቾች ከኳስ ጀርባ ሆነው በመከላከል ክፍተት ላለመፍጠር ሲጠነቀቁ ይስተዋላል፡፡ ከኄኖክ አዱኛ በቀር ብዙም የማጥቃት እንቅስቃሴ አካች ያልሆነው የተከላካይ መስመሩ ለግብ ጠባቂው በተጠጋ አቋቋም በመከላከል ቡድኑ ደካማ የውድድር ዘመን እያሳለፈ በሚገኝበት ወቅት እንኳን በ7 ጨዋታዎች ግብ ሳይቆጠርበት እንዲወጣ አድርገዋል፡፡

ለቡድኑ የመከላከል ስኬት አሰልጣኝ ዘላለም ከሚታወቁበት የመከላከል አጨዋወት ባሻገር በኋለኛው ክፍል የሚገኙት ተጫዋቾች የተናጠል አቋም በተለይም የበረከት ሳሙኤል እና ሳምሶን አሰፋ ድንቅ ብቃት ትልቁን ድርሻ የሚወስድ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በተለይ መሀል ሜዳ ላይ ኳስን ተቆጣጥረው ከሚጫወቱ ቡድኖች ጋር የድሬደዋ የአማካይ ክፍል ለተከላካይ ክፍሉ እጅግ በመቅረብ እና በሁለቱ መስመሮች መሀል ለተጋጣሚዎቹ ክፍተት ባለመስጠት መጫወቱ ለመክላከል ጥንካሬው አስተዋፅኦ አድርጓል ።

 ደካማ ጎን

የቡድኑ ዋንኛ ድክመት በእያንዳንዱ የሜዳ ክፍል (Department) ላይ ያለው ያለመገናኘት ነው፡፡ የተከላካይ መስመሩ ከአማካይ ክፍሉ ፤ አማካዩ ከጥቂ ክፍሉ ፤ የመስመር ተጫዋቾች ከአማካይ እና አጥቂዎች ጋር ያላቸው ግንኙነት የተቆራረጠ እና ሁሉም ክፍል የየራሱን ስራ ብቻ የሚሰራ አስመስሎታል፡፡ ለዚህ ድክመት ዋንኛ ተጠቃሽ ምክነንያት የሚሆነው የአማካይ ክፍሉ ላይ የሚሰለፉት ተጫዋቾች የማገናኘት (Link up) እና እንቅስቃሴ የመምራት ብቃት አናሳ መሆን ነው፡፡

የድሬዳዋ አጠቃላይ የማጥቃት እንቅስቃሴ በፕሪምየር ሊጉ ደካማው ነው፡፡ አሰልጣኙ የሚመርጡት የጨዋታ አቀራረብ ለዚህ እንደምክንያትነት የሚጠቀስ ሲሆን የሁነኛ ፈጣሪ አማካይ እጥረት መኖርም ለችግሩ ሌለላው ምክንያት ነው ፡፡ የአማካይ ክፍሉ ወደኋላ የተሳበ እንቅስቃሴ ወደመከላከል መስመሩ የመቅረቡን ያህል ባልተመጣጠነ መልኩ ከአጥቂዎቹ ስለሚርቅ ይህን ክፍተት የሚያጠብ ፈጣን የሆነ ፈጣሪ ተጨዋች አለመያዙ ሲጎዳው ተስተውሏል ። በዚህ ምክንያት ቡድኑ ወደማጥቃት የሚያደርገው ሽግግር አጥቂዎች ጋር ሳይደርስ እና ዕድሎች ሳይፈጠሩ በቀላሉ ሲስተጓጎል ይስተዋላል ። ስለሆነም ድሬደዋዎች የሚፈጥሩት የጎል ዕድል እጅግ አናሳ ሲሆን የሚፈጠሩትንም ጥቂት እድሎች በመጨረስ በኩል የአጥቂው ክፍል ደካማ ጊዜን አሳል ፏል ። በ15 ጨዋታ 6 ጎል ብቻ ማስቆጠሩ የማጥቃት እንቅስቃሴውን ደካማነት በቀላሉ ይነግረናል፡፡

በሁለተኛው ዙር ምን ይጠበቃል?

ድሬዳዋ በሁለተኛው ዙር ከፍተኛ ማሻሻያ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ክለቡ ካስፈረማቸው 4 ተጫዋቾች መካከል ሁለቱ አጥቂዎች ቢሆኑም የቡድኑ ችግር አጠቃላይ የማጥቃት እንቅስቃሴው በመሆኑ ይህን ለማሻሻል የአጥቂ አማካይ ተጫዋች ግዢ መፈጸም ወይም በቡድኑ ለሚገኙ የፈጠራ ችሎታ ላላቸው ተጫዋቾች እድል መስጠት ይገባዋል፡፡ አሰልጣኝ ዘላለም የአቀራረብ ለውጥ ይዘው በመቅረብ ለሊጉ የሚመጥን የማጥቃት እንቅስቃሴ ማሳየትም ይጠበቅባቸዋል፡፡

የአንደኛው ዙር የቡድኑ ኮከብ – ሳምሶን አሰፋ

አንጋፋው ግብ ጠባቂ ምርጥ የውድድር ዘመን እያሳለፈ ይገኛል፡፡ በ7 ጨዋታ ግብ ያልተቆጠረበት ሳምሶን በግል ጥረቱ ቡድኑን ተሸክሞ ሲወጣ በተደጋጋሚ ተመልክተነዋል፡፡ በአንጻራዊነት ጠንካራ የሆነውን የተከላካይ መስመር ከኋላ በመምራትም ቡድኑ የተደራጀ የመከላከል አጨዋወት እንዲኖረው ማድረግ ችሏል፡፡

ለሁለተኛው ዙር ተሰፋ የሚጣልበት ተጫዋች – ሚካኤል ለማ

አምና በደቡብ ፖሊስ ድንቅ አመት አሳልፎ በኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ቡድን የተካተተው ሚካኤል በድሬዳዋ ከጉዳት ጋር በተያያዘ የሚጠበቅበትን  ያህል ማበርከት ባይችልም የእምቅ አቅም ባለቤት ነው፡፡ አሰልጣኝ ዘላለም የሁለተኛ ዙር ቡድናቸውን በሚካኤል ዙርያ ቢያዋቅሩ የግብ እድሎችን የመፍጠር እና በአጥቂና አማካዮች መሀል ያለውን ሰፊ ክፍተት የመድፈን አቅም አለው፡፡

Leave a Reply