ዮሃንስ ሳህሌ የኢትዮጵያ ከ17 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆነው ተሾሙ

በአሰልጣኞች ቅጥር ላይ ተጠምዶ የሰነበተው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌን የኢትዮጵ ከ17 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ አድርጎ ቀጥሯል፡፡ ፌዴሬሽኑ የአሰልጣኝ ዮሃንስን ግልጋሎት ለማግኘት በወር 20 ሺህ የኢትዮጵያ ብር ይከፍላል፡፡

አሰልጣኝ ዮሃንስ የዋናው ብሄራዊ ቡድንን ለማሰልጠን ማመልከቻ ካስገቡ 27 አሰልጣኞች አንዱ የነበሩ ሲሆን ከዚህ በፊት በአቶ ሳህሉ አስተዳደር የብሄራዊ ቡድኑ የቴክኒክ ዳይሬክተር ሆነው አገልግለዋል፡፡

የቀድሞው የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋች በስፖርት ቤተሰቡ የሚታወቁት በተለይ በ1990ዎቹ አጋማሽ ለአሰልጣኞች በሚሰጧቸው የአሰልጣኝነት ስልጠና ኮርሶች ነው፡፡ ዮሃንስ በትልቅ ደረጃ የማሰልጠን ልምድ ባይኖራቸውም በዩናይትድ ስቴትስ የወጣቶች አካዳሚዎች ውስጥ በመስራታቸውና የማስተዳደር ክህሎት በመያዛቸው የታዳጊ ቡድኑን ወደፊት ሊያራምዱት ይችላሉ፡፡

አጭር የተጫዋችነት ዘመን የነበራቸው አሰልጣኝ ዮሃንስ የእግርኳስ ተጫዋችነት ዘመናቸውን የጀመሩት በ1975 በራስ ሆቴል ነው፡፡ ከአንድ አመት በኋላ ለእውቅና ወዳበቃቸው ቅዱስ ጊዮርጊስ ተዘዋውረው ሁለት አመታትን በፈረሰኞቹ ቤት አሳልፈዋል፡፡ በ1978 ለጨዋታ ወደ ውጪ አቅንተው በዛው ከጠፉ በኋላ በተጫዋችነት ዳግም አልታዩም፡፡

ፌዴሬሽኑ ከዚህ ቀደም አሰልጣኝ ወንድማገኝ ከበደን የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ አድርጎ መሾሙ ይታወሳል፡፡

ያጋሩ