በሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ ዛሬ የተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል

የሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ የሁለተኛ ዙር ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ ሲደረጉ ሀዋሳ ከተማ ከ ሲዳማ ቡና 1-1 ሀድያ ሆሳዕና ከ ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ ያለግብ ተለያይተዋል።

ሀዋሳ ከተማ 1-1 ሲዳማ ቡና

በመጀመሪያው የዕለቱ መርሐ ግብር ሀዋሳ ከተማ እና ሲዳማ ቡና ተገናኝተዋል፡፡ ፈጠን ባለ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ በጀመረው ጨዋታ ቀዳሚ 15 ያህል ደቂቃዎች የግብ ሙከራን መመልከት ያልቻልንበት ነበር፡፡ የጨዋታውን የኃይል ሚዛን ለመውሰድ በመስመር አዘንብለው ለመጫወት ሁለቱ ቡድኖች ጥረቶችን ሲያደርጉ ብንመለከትም ወደ ግብ ደርሶ የግብ አጋጣሚን ለመፍጠር ግን 25 ያህል ደቂቃዎችን ሊወስዱ ግድ ብሏቸዋል፡፡ በዚህ ደቂቃ ላይ በአንድ ሁለት ቅብብል ይገዙ ቦጋለ ለአማኑኤል ሰጥቶት የመስመር ተከላካዩም ወደ ግብ አሻምቶ ብሩክ ሙሉጌታ በግንባር ገጭቶ በግቡ የላይኛው ብረት የወጣችበት አጋጣሚ ተጠቃሽ ሙከራ ነበረች፡፡

መሀል ሜዳ ላይ ካሉ ተጫዋቾች በተደጋጋሚ ከሚነሱ ረጃጅም ኳሶች በተለይ ሲዳማ ቡና በሰለሞን ሀብቴ የግራ መስመር በኩል በሚሻሙ ኳሶች ዕድልን ለመፍጠር ሲሞከሩ ቢስተዋልም ከፊት ያሉ አጥቂዎች ቀዝቀዝ ብለው መታየታቸው የጠሩ የግብ ሂደቶትን እንዳንመለከት አድርጎናል። በአንፃሩ ሀዋሳ ከተማዎች ተመሳሳይ የጨዋታ ሂደት በመከተል ወደ ሲዳማ ቡና የግብ ክልል ቢደርሱም የሲዳማን የተከላካይ ክፍል ሰብሮ ለመግባት በተወሰነ መልኩ ሲቸገሩ አይተናል፡፡

30ኛው ደቂቃ ኤፍሬም አሻሞ ነፃ አቋቋም ላይ ለነበረው እና ከመክብ ደገፉ ጋር ትይዩ ለነበረው ብሩክ በየነ ሰጥቶት አጥቂው በቀላሉ ያልተጠቀመባት ተጠቃሽ ነች፡፡ብሩክ ከ10 ደቂቃ በኋላ ከኤፍሬም አሻሞ ያገኘውን ሌላ ኳስ ከሳጥን ውጪ አክርሮ ቢመታም ሙከራው በሲዳማ ቡናው አዲሱ ጋናዊ ተከላካይ ያኩቡ መሀመድ ተጨርፎ መክብብ ደገፉ በቀላሉ ይዞታል፡፡

ከመጀመሪያው አጋማሽ በደንብ የነቃ የሜዳ ላይ ፉክክርን ከተደጋጋሚ የግብ ሙከራ ጋር የተመለከትንበት ሁለተኛው 45 ገና በጊዜ ነበር የግብ ሙከራን ያስመለከተን፡፡ 47ኛው ደቂቃ ላይ በቀኝ በኩል የሲዳማ የግብ ክልል የሀዋሳው መስመር አጥቂ ኤፍሬም አሻሞ በግራ እግር መትቶ መክብብ ደገፉ የያዘበት የዚህኛው አጋማሽ ቀዳሚ ሙከራ ነበር፡፡ በፈጣን የፊት ተጫዋቾቻቸው አማካኝነት ተመርኩዘው ሁለተኛዋን ሙከራ አሁንም ያደረጉት ሀዋሳዎች ናቸው፡፡ የተሳካ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን ሲያስመለከተን የነበረው ኤፍሬም አሻሞ ለዮሀንስ ሶጌቦ ሰጥቶት በቀጥታ የግራ ተከላካዩ መትቶ መክብብ ሲመልሰበት ወንድማገኝ ነፃ የሆነች ኳስ አግኝቶ ወደ ላይ ሰዷታል፡፡ በዚህኛው አጋማሽ በመጀመሪያዎቹ አምስት ደቂቃዎች በሀዋሳ በግብ ሙከራ ቢበለጡም በሂደት ወደ ጨዋታ ቅኝት የተመለሱት ሲዳማ ቡናዎች 53ኛው ደቂቃ ላይ በይገዙ ቦጋለ ያለቀለትን አጋጣሚ አግኝተው መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል።

ደቂቃዎች እየገፉ ሲመጡ ፈዘዝ ብሎ የነበረው የጨዋታ መንፈስ ፍጥነት ታክሎበት ተደጋጋሚ ሙከራን ማሳየቱን ቀጥሏል፡፡62ኛው ደቂቃ ላይ ሀዋሳዎች የሲዳማን ተከላካይ ስህተት ተጠቅመው ኤፍሬም አሻሞ ለብሩክ በየነ ሰጥቶት አጥቂው ከሳጥኑ ጠርዝ አክርሮ መትቶ መክብብ በሚገርም ብቃት ካወጣበት ሦስት ደቂቃዎች በኋላ ጎል አስቆጥሯል፡፡ተቀይሮ የገባው ብሩክ ኤልያስ ብስለቱን ተጠቅሞ ከሳጥኑ ቀኝ ክፍል ለብሩክ በየነ ሰጥቶት አጥቂው አስቆጥሮ ሀዋሳን መሪ አድርጓል፡፡ 71ኛው ደቂቃ የአማካይ ስፍራ ተጫዋቾቻቸውን በደንብ ወደ መጠቀሙ የገቡት ሲዳማ ቡናዎች አቻ የሆኑበትን ጎል አግኝተዋል። ሰለሞን ሀብቴ ከግራ በኩል ወደ ጎል የላካት ኳስ በሀዋሳ ብሩክ ሙሉጌታ ጨርፏት በመጨረሻም ዮሀንስ ሱጌቦ በራሱ ላይ አስቆጥሮ ሲዳማ ቡና 1-1 ሆኗል፡፡ ጨዋታው ተጠናቆ በጭማሪ ደቂቃ የሀዋሳው አጥቂ ተባረክ ኢፋሞ ከሳጥን ውጪ ሞክሮ መክብብ ደገፉ ካወጣበት በኋላ ጨዋታው በአቻ ውጤት ተደምድሟል፡፡

ከጨዋታው ፍፃሜ በኋላ የሲዳማ ቡናው ተከላካይ ያኩቡ መሐመድ የጨዋታው ኮከብ ሆኖ የጎፈሬን ሽልማት ተቀብሏል።

ሀድያ ሆሳዕና 0-0 ድሬዳዋ ከተማ

ቀጣዩ ጨዋታ በሀድያ ሆሳዕና እና ድሬዳዋ ከተማ መካከል ተከናውኗል፡፡የመሀል ሜዳ ፍትጊያ የበዛበት እና ብዙም ስኬታማ ያልነበረው የመጀመሪያው አጋማሽ አብዛኛዎቹን የጨዋታ ደቂቃዎች በአመዛኙ እንቅስቃሴ ላይ ያዘነበሉ ሆነው በሙከራ ረገድ ግን የጠሩ ዕድሎችን መመልከት ያልቻልንበት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ድሬዳዋ ከተማዎች በጋዲሳ መብራቴ እና አብዱራህማን ሙባረክ አማካኝነት ወደ ሀድያ ሆሳዕና የግብ ክልል ለመድረስ ጥረት ሲያደርጉ ሀድያ ሆሳዕናዎች በበኩላቸው መሀል ሜዳ ላይ በኤፍሬም ዘካሪያስ እና ሳምሶን ጥላሁን ግሩም ጥምረት ወደ ድሬዳዋ የግብ ክልል ቶሎ ቶሎ መድረስ ቢችሉም የመጨረሻው የኳሶቻቸው ማረፊያ ግን ስኬታማ አልነበሩም፡፡

36ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት ሳምሶን ጥላሁን አሻምቶ ፀጋዬ ብርሀኑ በግንባር ገጭቶ ለጥቂት ወጥቶበታል። በሙከራ ረገድ ከድሬዳዋ ሻል ብለው የታዩት ሀድያ ሆሳዕናዎች በደስታ ዋሚሾ ሌላ ያለቀለትን ዕድል በድጋሚ አግኝተው በደረጀ ዓለሙ ብቃት ሊከሽፍ ችሏል፡፡ የኤፍሬም ዘካሪያስ ልዩነት ፈጣሪነት በሀድያ ሆሳዕና በኩል ጎልቶ የታየ ሲሆን በተለይ ኤፍሬም ለተስፋዬ አለባቸው ሰጥቶ ግዙፉ አማካይ ከርቀት መትቶ የወጣበት ሌላኛው የነብሮቹ ሙከራ ነበረች፡፡

ከእረፍት መልስ ፍፁም የሀድያ ሆሳዕና የጨዋታም ሆነ የሙከራ ብልጫ በነበረበት አጋማሽ የሀድያ ሆሳዕና የቅብብሎሽ ሂደት ማራኪ ሆኖ የታየበት በተደጋጋሚ ከኤፍሬም ዘካሪያስ መነሻነት ጥቃት ሲሰነዝሩ የተስተዋለበት ነበር፡፡ ፀጋዬ ብርሀኑ በቀኝ በኩል ባደረገው ጥቃት ጅምራቸውን ያደረጉት ሀድያዎች በተለይ 80ኛው ደቂቃ ላይ ሄኖክ አርፊጮ ከርቀት መትቶ ደረጀ ዓለሙ እንደምንም የያዛት ሌላኛው የክለቡ ኢላማዋን የጠበቀች ሙከራ ነበረች፡፡ በተደጋጋሚ በድሬዳዋ የግብ ክልል በአንድ ሁለት ቅብብል ቶሎ ቶሎ በመድረስ ብልጫን የወሰዱት ሀድያዎች በፍሬዘር ካሳ እና ፀጋዬ ብርሀኑ አማካኝነት ተጨማሪ ዕድሎችን ቢያገኙም ጨዋታው 0-0 ተጠናቋል፡፡

ከጨዋታው ፍፃሜ በኋላ የሀድያ ሆሳዕናው አማካይ ተስፋዬ አለባቸው የጨዋታው ኮከብ ሆኖ የጎፈሬን ሽልማት ተቀብሏል።