የጨዋታ ሪፖርት | ቅዱስ ጊዮርጊስ በቀላሉ ወደ 1ኛ ዙር ያለፈበትን ድል ኮት ዲኦር ላይ አስመዝግቧል

​በ2017ቱ የቶታል አፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ቅድመ ማጣሪያ የመልስ ጨዋታውን በሀዋሳ ዓለምአቀፍ ስታዲየም ያደረገው ቅዱስ ጊዮርጊስ ሶስት ለባዶ በሆነ ውጤት በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር ተቀላቅሏል፡፡

ትናንት የተጀመረው ጨዋታ በሀዋሳ በጣለው ከባድ ዝናብ ምክኒያት ሜዳው ውሀ ቋጥሮ ማጫወት ባለመቻሉ በ55ኛው ደቂቃ በዳኛው ውሳኔ ተቋርጧል። የጨዋታው ኮሚሽነር ጉዳዩን ለአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌዴሬሽን ካሳወቁ በኀላም ቀሪ 35 ደቂቃዎች ዛሬ ረፋድ 4 ሰአት ላይ እንዲደረጉ ሆኗል።

በከባድ ዝናብ በተጀመረው ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ በጨዋታ ቁጥጥር እና የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን በመፍጠር ከተጋጣሚው የተሻለ ሆኖ ታይቷል። በ9ኛው ደቂቃ በረጅም የተሻማውን ኳስ አዳነ ግርማ ገጭቶ ሲያወርድ ሳላህዲን ሰይድ አግኝቶ በማስቆጠር ቅዱስ ጊዮርጊስን ቀዳሚ አደርጓል። ከግቡ መቆጠር በኃላ ጫና ፈጥረው መጫወት የቀጠሉት ፈረሰኞቹ በአቡበከር ሳኒ እና በአብዱልከሪም ኒኪማ ግልፅ ግብ የሚሆኑ እድሎችን የፈጠሩ ቢሆንም መጠቀም አልቻሉም።
በጨዋታው 32ኛ ደቂቃ በኃይሉ አሰፋ ከማዕዘን ምት ያሻገረውን ኳስ ተከላካዩ አስቻለው ታመነ በግንባሩ በማስቆጠር የቅዱስ ጊዮርጊስን ግብ ወደ ሁለት አሳድጓል።


በጨዋታው ጥሩ እንቅስቃሴ ያደረገው አቡበከር ሳኒ ኳስ ወደ አደጋ ክልሉ ሲገባ በመጠለፉ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት አዳነ ግርማ አሰቆጥሮ ልዩነቱን ወደ 3 አስፍቷል። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ 2 ደቂቃ ሲቀር አብዱልከሪም ኒኪማ ያሻገረውን ኳስ አዳን ግርማ ሲመታው ግብ ጠባቂው መልሶት ዳግም ሲመለስ ሳላሀዲን ሰይድ  በግንባሩ ሞክሮ የሳተው አጋጣሚ የሚያስቆጭ ነበር፡፡

ከዕረፍት መልስ የስታዲየሙ የመጫወቻ ሜዳ ውሀ ይዞ አላጫውት በማለቱ ጨዋታው በ55ኛው ደቂቃ ተቋርጧል። በ49ኛው ደቂቃ አበባው ቡጣቆ ያሻገረውን ኳስ ተከላካዩ ሳላሀዲን በርጊቾ አግኝቶ የኮት ድ ኦር ተከላካዮች እና ግብ ጠባቂው በወደቁበት ሁኔታ መትቶ በሜዳው መበላሸት ምክኒያት ኳስ አቅጣጫ ስታ የግቡን ቋሚ ታካ የወጣችበት አጋጣሚ ሜዳው ምንያህል ለጨዋታ አስቸጋሪ እንደነበር ያሳየ ነበር።

ዛሬ ረፋድ 4 ሰዓት ላይ የጨዋታው ቀሪ ደቂቃዎች ሲደረጉ ቅዱስ ጊዮርጊስ የተሻለ እንቅስቃሴን ቢያደርግም ተጨማሪ ግብ ሳይስቆጥር ቀርቷል። በመከላከሉ የተሻሉ ሆነው የቀረቡት ኮት ዲ ኦሮች በሳላህዲን ሰዒድና እና በሀይሉ አሰፋ እንዲሁም ፍሬዘር ካሳ አማካይነት የተፈጠሩ ግልፅ የግብ አጋጣሚዎችን ማምከን ችለዋል። በኮት ዲኦር በኩል  ኮሊን ኢስተር ከማዕዘን ምት ወደ ግብ ሞክሮ ሮበርት ያወጣበት ኳስ እንዲሁም ጂያን ቲጋና በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ወደ ግብ የሞከራቸው ኳሶች የሚጠቀሱ ነበሩ።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታውን በድምር ውጤት 5-0 በሆነ ውጤት ማሸነፋን ተከትሎ በቀጣዩ ዙር ከኮንጎ ብራዛቪሉ ኤሲ ሊዮፓርድስ ጋር የሚገናኝ ይሆናል፡፡ በኮት ድ ኦር ላይ 3 ግቦችን ማስቆጠር የቻለው ሳላህዲን ሰዒድ ከሞሪሺየሳዊው ኤፍሬም ጉይካን እና ሊብያዊው ሞአያድ አላፊ ጋር የቻምፒየንስ ሊጉን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪዎች ሰንጠረዥ በመምራት ላይ ይገኛል።

Leave a Reply