ሀዋሳ ከተማ የሱዳን ከ20 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድንን አሸንፏል

ሀዋሳ ከተማ አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ የሱዳን ከ20 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድንን በአቋም መለኪያ ጨዋታ አስተናግዶ 2-1 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል፡፡ የሱዳን ወጣት ቡድን ዛምቢያ በሳምንት መጨረሻ በማስተናገደ በሚጀመረው የቶታል የአፍሪካ ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ ላይ ተካፋይ በመሆኑ ጨዋታውን ለዝግጅት ተጠቅሞበታል፡፡

ጨዋታው የእንግዶቹ በአካል ብቃቱ ረገድ ጠንክረው በመቅረባቸው በመሃል ሜዳ ኳስን ለማግኘት በሚደረግ እና ወደፊት ለመሄድ በሚደረጉ ጥረቶች ታጅቦ ነበር የተጀመረው፡፡ በ8ኛው ደቂቃ አማካዩ አምር ካማልዲን ወደ ግብ ከቅርብ ርቀት የሞከረውን ኳስ የብድን አጋሩ ካሊድ አብደልሞኔም መልሶበታል፡፡ ከአንድ ደቂቃ በኃላ ፍሬው ሰለሞን የግብ ጠባቂው መሃመድ አልኑር በሰራው ስህተት ኳስን ቢያገኝም የመታው ኳስ የሱዳን ተከላካዮች መልሰውታል፡፡

 በ12ኛው ደቂቃ ከማዕዘን የተሻረገውን ኳስ በአግባቡ ማውጣት የተሳናቸው ሱዳኖች ኳስ ሁለት ግዜ የግቡን አግዳሚ መልሶ ከመጣ በኃላ ኮትዲቯራዊው አዲሱ የሀዋሳ ከተማ ፈራሚ መሃመድ ሲላ ከቅርብ ርቀት በግንባሩ በመግጨት ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል፡፡ መሪነቱ የዘለቀው ግን ለደቂቃ ብቻ ነው፡፡ የግራ መስመር አማካዩ ሙሳብ ኮርድማን ከመስመር ያሻገረውን ኳስ ሲላ በራሱ መረብ ላይ አስቆጥሮ ቡድኖቹ አቻ ሆነዋል፡፡ ሲላ ለሀዋሳ በመጀመሪያው ጨዋታ በተቃራኒ እና በራሱ ግብ ላይ አስቆጥሯል፡፡ የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ደቂቃ ሲቀረው ከመሃል ተከላካይ ሰንጣቂ ኳስ አብደልሞኔምን ከሀዋሳው ግብ ጠባቂ ሜንሳህ ሶሆሆ ጋር ቢያገናኝም ሶሆሆን ያለፈው የሱዳኑ አጥቂ የሞከረው ሙከራ መሳይ ጳውሎስ በግሩም ሁኔታ ከመስመር አውጥቶበታል፡፡ 

በሁለተኛው አጋማሽ ቡድኖቹ ኳስን መሰረት አድረገው ሲያጠቁ ተስተውሏል፡፡ በሁለተኛው 45 ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ከድሬዳዋ ከተማ በዝውውር መስኮቱ ሀዋሳ ከተማን የተቀላቀለው ምስጋናው ውልደዮሃንስ የአሸናፊነን ግቧን ከመረብ አዋህዷል፡፡ የሱዳን ከ20 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን በኢድ ሞጋዳም እና ኢብራሂም መሃመድ አማካኝነት አቻ ለመሆን ቢሞክሩም ቶጎዊው ሶሆሆ በቀላሉ ኳስቹን ማምከን ችሏል፡፡
ሀዋሳ ከተማ በሁለተኛው ዙር የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አዲስ አበባ ከተማን በመግጠም ይጀምራል፡፡ ሴኔጋል፣ ካሜሮን እና ደቡብ አፍሪካ ጋር በምድብ አንድ የተደለደለው የሱዳን ከ20 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን ደግሞ ከሴኔጋል ጋር በመጪው ሰኞ ንዶላ ላይ በመጫወት የአፍሪካ ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ ውድድሩን ይጀምራል፡፡

Leave a Reply