ሀዋሳ ከተማ በተጫዋቾቹ ላይ የቅጣት ውሳኔ አሳለፈ

በዘንድሮው የውድድር ዘመን ያልተጠበቀ ደካማ ውጤት እያስመዘገበ ያለው ሀዋሳ ከተማ ለውጤት መጥፋቱ የተጫዋቾች ዲሲፕሊን ጥሰት እንደ ዋና ምክንያት ሲጠቀስ ቆይቷል፡፡ ክለቡም የዲሲፕሊን ግድፈት ያሳዩ ያላቸው ተጫዋቾች ላይ የቅጣት ውሳኔ አስተላልፏል፡፡ የክለቡ ቦርድ ውሳኔ ያስተላለፈባቸው ግርማ በቀለ ፣ መድሀኔ ታደሰ እና ኤፍሬም ዘካሪያስ ናቸው፡፡

በተከላካይ ስፍራ ላይ የሚጫወተው ግርማ በቀለ ቦርዱ ባስተላለፈው ውሳኔ መሠረት ከክለቡ እንዲሰናበት ተደርጓል፡፡ ግርማ ከክለቡ ጋር ከተነጋገረ በኋላ ነው ወደ ሌላ ክለብ በውሰት እንዲያመራ የሚፈቅድ መልቀቅያ የተሰጠው፡፡ ተከላካዩ የአንድ ወር ደሞዙ እንዳይከፈለው ሲደረግ ክለቡ ያበደረውን ገንዘብም በአሰቸኳይ እንዲመልስም ተወስኗል፡፡

በከለብ ህይወቱ በሀዋሳ ከተማ ማልያ ብቻ የተጫወተው ግርማ በአመቱ መጀመርያ ከክለቡ አምበልነት ተነስቶ ለደስታ ዮሃንስ የተሰጠ ሲሆን ከወዲሁ ስሙ ከኢትዮ ኤሌትሪክ ዝውውር ጋር ተያይዞ መነሳቱን ተከትሎ ከሀዋሳ ውጪ የሌላ ክለብ ማልያን ለመልበስ ተቃርቧል፡፡

ሌላኛው የቅጣት በትር ያረፈበት የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ ኤፍሬም ዘካሪያስ ከወርሃዊ ክፍያ ላይ ግማሹ ተቆርጦ እንዲከፈለው ተወስኗል፡፡ አጥቂው መድሀኔ ታደሰ ደግሞ የአንድ ወር ደሞዝ ተቀጥቷል፡፡

ሀዋሳ ከተማ ከዚህ ቀደም ክለቡ ከመከላከያ ጋር ባደረገው ጨዋታ የቡድኑ ተጫዋቾች ባሳዩት ያልተገባ ባህርይ ቅጣት እና ማስጠንቀቂያ ማሳለፉ የሚታወስ ነው፡፡

1 Comment

  1. የዲሲፕሊን ግድፈት ሰፊ ነው . . ምን ይሁን ግን እንዚህ ልጆች ያደረጉት . . . ለሌላው ስፖርተኛ ማስተማርያ እንዲሆን ይፋ ቢወጣ መልካም ነበር።

Leave a Reply