ኢትዮጵያዊው ኢንተርናሽናል ዋሊድ አታ ወደ ሳውዲ አረቢያው ናጅራን ስፖርት ክለብ አምርቷል፡፡
የመሃል ተከላካዩ ወደ ተወለደባት የመካከለኛው ምስራቅ ሃገር ያመራው ከስዊድኑ ኦስተርሰንድስ ጋር የነበረው ውል ከተጠናቀቀ በኃላ ነው፡፡ ዋሊድ በሳውዲ አረቢያ መዲና ሪያድ ከኢትዮጵያዊ እናት እና ኤርትራዊ አባት ነው የተወለደው፡፡
ዋሊድ በህዳር ወር ከኦስተርሰንድስ ጋር የተሳካ ቆይታ ቢያደርግም ውሉ ሳይታደስ ከስዊድኑ ክለብ ጋር ተለያይቷል፡፡ በ2015/16 የውድድር ዘመን ከሳውዲ ፕሮፌሽናል ሊግ የወረደው ናጅራን ዳግም ወደ ታላቁ የሃገሪሩ ሊግ ለመመለስ በማለም ተጫዋቾችን ሲያስፈርም ቆይቷል፡፡ ክለቡ ዋሊድን ያስፈረመው የተከላካይ መስመሩ በማጠናከር ወደ ሳውዲ ፕሮፌሽናል ሊግ ለማደግ የሚያደርገው ጥረት እውን ለማድረግ እንደሆነ ተነግሯል፡፡ ዋሊድ በዝውውሩ መሳካት ደስተኛ መሆኑን ለሶከር ኢትዮጵያ አዲሱ ክለቡን ከተቀላቀለ በኃላ ገልጿል፡፡
ናጅራን በሳውዲ አንደኛ ዲቪዚዮን በደረጃ ሰንጠረዡ ከመሪው አል ፋያ ክለብ በስምንት ነጥቦች ርቆ በ30 ነጥብ አምስተኛ ነው፡፡ ሶስት ክለቦች ወደ ዋናው ሊግ የሚያድጉ በመሆኑ ክለቡ አሁንም ዳግም ወደ ሊጉ የመመለስ ተስፋ አለው፡፡ ናጅራን ምስረታው በ1981 ያደረገ ሲሆን በ2000 አጋማሽ ወደ ሊጉ ማደግ ችሎ ለ10 ዓመታት በሊጉ ቆይታ ማድረግ ችሏል፡፡