በአዲሱ የካፍ ኮንቬንሽን መሠረት ሀገራችን ኢትዮጵያ ከአራት ዓመታት በኋላ የካፍ የዲ ላይሰንስ የአሠልጣኞችን ሥልጠና መስጠት ጀምራለች።
የአፍሪካ እግርኳስ የበላይ አካል የሆነው ካፍ የአባል ሀገራቱን የአሠልጣኞች ስልጠና ደረጃ ከፍ ለማድረግ እንቅስቃሴ ላይ እንደነበር ይታወሳል። የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የቴክኒክ ክፍልም ካፍ በሰጠው መመሪያ መሠረት በሀገራችን ከሚገኙ የካፍ ኢንስትራክተሮች ጋር በመሆን የአሠልጣኞችን ስልጠና የሚሰጥበትን ማኑዋል አዘጋጅቶ ለካፍ መላኩ የሚታወቅ ሲሆን ካፍም በዲ እና ሲ ደረጃ ከኢትዮጵያ የተላከውን ማኑዋል በጥሩ ሁኔታ አድንቆ ግብረ መልስ መላኩ ታውቋል። ካፍ በሰጠው አቅጣጫ እና ሀገራችን ሥልጠናውን መስጠት ትችላለች ባለው መሠረትም የካፍን ሥልጠናዎች ለማግኘት ሲጠብቁ የነበሩ ባለሙያዎች የዲ ላይሰንስ ለማግኘግ ባሳለፍነው ሳምንት በይፋ ሥልጠና መውሰድ መጀመራቸው ተሰምቷል።
የዲ ላይሰንስ ሥልጠናዎችን የማዘጋጀት እና የማስተባበር ኃላፊነት ካላቸው ክልሎች መካከል የአማራ ክልል እግርኳስ ፌዴሬሽን (ከባህር ዳር ዩኒቨርስቲ እና ባህር ዳር ከተማ ክለብ ጋር በመተባበር) ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ኢንስትራክተሮችን በማስመደብ ከሦስት ቀናት በፊት ሥልጠና ማሰጠት ጀምሯል። የዲ ላይሰንስ ሥልጠናውን ለመውሰድ የተቀመጠውን የእድሜ እርከን (18 ዓመት) እና የሃገሪቱን ቋንቋ በሚገባ ለሚችሉ አሠልጣኞች የሚሰጠውን ሥልጠና ኢንስትራክተር ሠላም ዘራይ፣ ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው እና ኤሊት ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ እየሰጡ ይገኛል። በሥልጠናው የመክፈቻ መርሐ-ግብር ላይም የአማራ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ አዱኛ፣ የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ የስፖርት ፋኪሊቲ ዲን ዶ/ር ዳኛቸው እና የባህር ዳር ከተማ ስፖርት ክለብ ሥራ-አስኪያጅ አቶ ልዑል መገኘታቸው ተጠቁሟል።
ሥልጠናው ለረጅም ጊዜ ባለመሰጠቱ ምክንያት በርካታ ፍልጎት ያላቸው ባለሙያዎች ቢኖሩም ካፍ በአንድ ጊዜ ለ30 ተሳታፊዎች ብቻ ሥልጠናው እንዲሰጥ በመወሰኑ በተቀመጠው ቁጥር ልክ ብቻ በአሁኑ ሰዓት ሥልጠናው እየተሰጠ ይገኛል። በባህር ዳር ከተማ እየተሰጠ የሚገኘው ሥልጠና 60 ሰዓታትን እንደሚፈጅ የተረዳን ሲሆን 60% የክፍል ውስጥ 40% ደግሞ የተግባር ሥልጠናዎች እንደሚሰጡበት ተመላክቷል።
የካፍ የዲ ላይሰንስ ሥልጠና አሁን ላይ በባህር ዳር ከተማ እየተሰጠ ቢገኝም በቀጣይ ሌሎች ክልሎች በሚያቀርቡት ጥያቄ መሠረት መሰጠት እንደሚቀጥል ሲጠቆም የሲ ላይሰንስም የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከክልሎች ጋር በመነጋገር በሚያወጣው ፕሮግራም እንደሚሰጥ ተጠቁሟል።