የኢትዮጵያ ሴቶች ጥሎ ማለፍ 1ኛ ዙር ጨዋታዎች ዛሬ ተካሂደዋል 

የ2009 የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ሴቶች ጥሎ ማለፍ ውድድር በዛሬው እለት በተደረጉ የ1ኛ ዙር ጨዋታዎች ተጀምሯል፡፡ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፣ ደደቢት ፣ ጥረት እና መከላከያም ወደ ተከታዩ ዙር ማለፍ የቻሉበትን ውጤት አስመዝግበዋል፡፡

በ08:00 አበበ ቢቂላ ላይ በኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መካከል የተደረገው ጨዋታ መደበኛው ክፍለ ጊዜ 1-1 ተጠናቆ ንግድ ባንክ በመለያ ምት 4-2 ማሸነፍ ችሏል፡፡

በተደራጀ መከላከል እና በመልሶ ማጥቃቱ ረገድ ኤሌክትሪኮች ተሽለው በቀረቡበት ፣ በኳስ ቁጥጥር ደግሞ የንግድ ባንክ ብልጫ በታየበት ጨዋታ ለኤሌክትሪክ አለምነሽ ገረመው ፤ ለባንክ ትዕግስት ያደታ በመደበኛው ክፍለ ጊዜ የተቆጠሩ ግቦች ባለቤቶች ናቸው፡፡ አሸናፊውን ለመለየት በተሰጠው የመለያ ምት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 4-2 በመርታት ወደ ተከታዩ ዙር ማለፍ ችሏል፡፡ ለባንክ ድል የግብ ጠባቂዋ ዳግማዊት መኮንን አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነበር፡፡

ቀጥሎ 10:00 ላይ መከላከያ ቅዱስ ጊዮርጊስን 2-1 ማሸነፍ ችሏል፡፡ ሳቢ ያልነበረው የመጀመርያው አጋማሽ ያለ ምንም ጎል ሲጠናቀቅ ከእረፍት መልስ መሰሉ አበራ ፈረሰኞቹን ቀዳሚ ማድረግ ችለላ ነበር፡፡ የኋላ ኋላ መከላከያ የምስራች ላቀው አከታትላ ባስቆጠረቻቸው ሁለት ግሩም ጎሎች ታግዞ ጨዋታውን በ2-1 አሸናፊነት መደምደም ችሏል፡፡

09:00 ላይ ጥረት ኮርፖሬት ከ አቃቂ ቃሊቲ ያደረጉት ጨዋታ በጥረት 4-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ ለባህርዳሩ ክለብ ፋጡማ አሊ ፣ ኪፊያ አብዱራህማን ፣ ወርቅነሽ ሜልሜላ እና ተቀይራ የገባችው ስንታየሁ ታፈረ ግቦቹን አስቆጥረዋል፡፡ በተለይም የቀድሞዋ የደደቢት አማካይ ኪፊያ ያስቆጠረችው ግብ ግሩም ነበር፡፡

11:30 ላይ በዚህ ዙር ከተደረጉ ጨዋታዎች ጠንካራው የነበረው የደደቢት እና አአ ከተማ ጨዋታ በደደቢት 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ ብርቱካን ገብረክርስቶስ ከእረፍት በፊት ፣ ሰናይት ቦጋለ ደግሞ ከእረፍት መልስ የሰማያዊዎቹን የድል ግብ ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ናቸው፡፡

የሁለተኛው ዙር ጨዋታዎች ፕሮግራም

የካቲት 17 ቀን 2009

09:00 ድሬዳዋ ከተማ ከ ኢ.ወ.ስ. አካዳሚ (አአ ስታድየም)

11:30 ቦሌ ከ ንፋስ ስልክ ላፍቶ (አአ ስታድየም)

08:00 አዳማ ከተማ ከ ቅድስት ማርያም (አበበ ቢቂላ)

10:00 ልደታ ከ ጌዲኦ ዲላ (አበበ ቢቂላ)

የካቲት 21 ቀን 2009

09:00 ጥረት ከ ኢትዮጵያ ቡና (አአ ስታድየም)

11:30 ደደቢት ከ ሲዳማ ቡና (አአ ስታድየም)

08:00 ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ አርባምንጭ ከተማ (አበበ ቢቂላ)

10:00 መከላከያ ከ ሀዋሳ ከተማ (አበበ ቢቂላ)

Leave a Reply