የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 2ኛ ዙር ነገ በሚደረጉ ጨዋታዎች ይጀመራል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ዙር ነገ በሚደረጉ ሁለት የአዲስ አበባ ስታድየም ጨዋታዎች ይጀመራል፡፡ ኢትጵያ ንግድ ባንክ ወልድያን 09:00 ላይ ሲያስተናግድ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጅማ አባ ቡናን 11:30 ላይ ይገጥማል፡፡

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ወልድያ

ሁለቱም ቡድኖች በአሰልጣኞች ላይ ለውጦች አሳይተው ለሁተኛው ዙር ቀርበዋል፡፡ ባንክ ሲሳይ ከበደን ዋና አሰልጣኝ አድርግ ሲሾም ወልድያ ደግሞ ለዋና አሰልጣኙ ንጉሴ ደስታ ረዳቶች ቀጥሯል፡፡

አሰልጣኝ ሲሳይ በንግድ ባንክ ዋና አሰልጣኝነት ከተሾሙ በኋላ የሚያደርጉት የመጀመርያ ጨዋታ ቢሆንም ተሰናባቹ አሰልጣኝ ጸጋዬ ኪዳነማርያም በቅጣት ምክንያት በሁለት የመጨረሻ ጨዋታዎች ላይ ቡድናቸውን መምራት አለመቻላቸውን ተከትሎ ቡድኑን በአሰልጣኝነት እየመሩ መግባታቸው ይታወሳል፡፡

የውድድር ዘመኑን በአሰልጣኙ ብቻ እየተመራ የገፋው ወልድያ በምክትል አሰልጣኝነት ኃይማኖት ግርማን ፤ በግብ ጠባቂ አሰልጣኝነት ደግሞ ይልማ ከበደን መቅጠሩ ቡድኑን ያጠናክረዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ንግድ ባንክ ዳኛቸው በቀለ እና አምሃ በቀለን ለቆ አቢኮዬ ሻኪሩን ሲያስፈርም ወልድያ ደግሞ ያሬድ ብርሃኑን ከደደቢት በውሰት አስፈርሟል፡፡

የክለቦቹ ያለፉት ጨዋታዎች አቋም

ሁለቱ ክለቦች የመጀመርያውን ዙር በተለያየ ጽንፍ ሆነው አጠናቀዋል፡፡ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ14 ነጥቦች ራሱን ወራጅ ቀጠና ውስጥ ሲያገኝ በተከታታይ 3 ጨዋታዎች ላይ ሽንፈት አስተናግዷል፡፡ በነዚህ ጨዋታዎች ብቻ የተቆጠረበት የግብ መጠን (11) ምን ያህል ቡድኑ ከፍተኛ የውጤት ቀውስ ውስጥ እንዳለ የሚያሳይ ነው፡፡

ወልድያ በተረጋጋ ሁኔታ የደረጃ ሰንጠረዡ ወገብ ላይ ሆኖ አጠናቋል፡፡ ያለፉት 5 ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ያልተሸነፈው ወልድያ ከጨዋታ ጨዋታ መሻሻል እያሳየ ይገኛል፡፡

ከጨዋታው ምን እንጠብቅ?

በሊጉ ግብ ማስቆጠር ከሚቸገሩ ቡድኖች መካከል ሁለቱ እርስ በእርስ ይፋለማሉ፡፡ ሁለቱም ከወገብ በላይ እጅግ የተዳከመ የማጥቃት እንቅስቃሴ የሚያደርጉ እንደመሆኑ እና ወልድያ እንዳለው ጠንካራ የተከላካይ መስመር ጨዋታው አሰልቺ ገጽታ እንዳይኖረው ያሰጋል፡፡

እርስ በእርስ ግንኙነቶች

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ለ3 ጊዜያት ተገናኝተው ንግድ ባንክ 1 ፣ ወልድያ 1 ድል ሲያስመዘግቡ አንድ ጊዜ በአቻ ውጤት ጨዋታቸውን ፈፅመዋል፡፡ በዘንድሮው አመት የመጀመርያ ዙር ጨዋታ ደግሞ ወልድያ በአንዱአለም ንጉሴ ብቸኛ ግብ 1-0 አሸንፏል፡፡

ማን ይመራዋል?

ይህንን ጨዋታ ፌዴራል ዳኛ ይርጋለም ወልደጊዮርጊስ በመሀል ዳኝነት ይመሩታል፡፡

ጉዳት እና ቅጣት

ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ግብ ጠባቂው ኢማኑኤል ፌቮ ወደ ጨዋታ ያልተመለሰ ሲሆን በወልድያ በኩል ተጠቃሽ የጉዳት ዜና የለም፡፡ አማካዩ ዳንኤል ደምሴ ከቅጣት መልስ ወደ ወልድያ አሰላለፍ እንደሚመለስ ይጠበቃል፡፡

 

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ጅማ አባ ቡና

ሁለቱም ቡድኖች የተጫዋች ዝውውሮች በማድረግ ለነገው ጨዋታ የሚቀርቡ ይሆናል፡፡ ኤሌክትሪክ ተክሉ ተስፋዬ እና ዳንኤል ራህመቶን ሲያስፈርም 3 ተጫዋቾትነ ያሰናበተው ጅማ አባ ቡና ሲሳይ ባንጫ ፣ አብዱልሃኪም ሱልጣን እና ኄኖክ ካሳሁንን በማስፈረም ክፍተቶችን ለመድፈን ጥረት ማድረግ ችለዋል፡፡

ያለፉት ጨዋታዎች አቋም

ኢትዮ ኤሌክትሪክ በመጨረሻዎቹ የአንደኛ ዙር ጨዋታዎች ከፍተኛ መሻሻል በማሳየት ከወራጅ ቀጠናው መውጣት ሲችል ጅማ አባ ቡና በደካማ የውድድር ዘመኑ ቀጥሎ በወራጅ ቀጠናው ይገኛል፡፡ ምናልባት በ1ኛው ዙር የመጨረሻ ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማን 3-0 ማሸነፉ ቡድኑን ለለውጥ ሊያነሳሳው ይችላል፡፡

ከጨዋታው ምን እንጠብቅ?

በክህሎት እና ልምድ የተሻለ የአማካይ ክፍል ያለው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከጅማ አባ ቡና የአማካይ ክፍል ድክመት ጋር ተደማምሮ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ሊወስድ ይችላል፡፡ በበርካታ ጨዋታዎች አብሮ የመሰለፍ እድል ያገኙት የአባ ቡና ተከላካዮች የፈጠሩት የተረጋጋ የተከላካይ መስመር በጥሩ አቋም ላይ ከሚገኙት የኤሌክትሪክ አጥቂዎች ጋር የሚያደርጉት ፍልሚያም ትኩረት የሚስብ ነው፡፡

እርስ በእርስ ግንኙነቶች

ሁለቱ ክለቦች አንድ ጊዜ ብቻ በሊጉ ተገናኝተዋል፡፡ ይህም በዘንድሮው የውድድር ዘመን 1ኛ ዙር ጅማ ላይ ያለ ግብ አቻ የተለያዩበት ነው፡፡

ጨዋታውን ማን ይመራዋል?

የአምናው የፕሪምየር ሊግ ኮከብ ዳኛ ኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሰ ጨዋታውን በዋና ዳኝነት ይመሩታል፡፡

የጉዳት እና ቅጣት ዜናዎች

የረጅም ጊዜ ጉዳት ያስተናገደው ጀማል ጣሰው አሁንማ ባለማገገሙ በጨዋታው አይሰለፍም፡፡ ለጅማ ለመጫወት የተስማማው ሲሳይ ባንጫ ዝውውሩን ሙሉ ለሙሉ አጠናቆ በነገው ጨዋታ ላይ ጀማልን ይተካል ተብሎም አይታሰብም፡፡

2 Comments

Leave a Reply