ጅማ አባ ቡና ሲሳይ ባንጫን ሲያስፈርም 3 ተጫዋቾችን አሰናብቷል

ጅማ አባ ቡና በውድድር ዘመኑ አጋማሽ የዝውውር መስኮት ንቁ ተሳትፎ እያደረገ ይገኛል፡፡ በትላንትናው እለትም የአዳማ ከተማው ግብ ጠባቂ ሲሳይ ባንጫን የግሉ አድርጓል፡፡ ሲሳይ እስከ ውድድር ዘመኑ ማብቂያ የምዕራብ ኢትዮጵያውን  ክለብ ያገለግላል፡፡

አባ ቡና ጀማል ጣሰውን በረጅም ጊዜ ጉዳት ማጣቱን ተከትሎ በግብ ጠባቂ ስፍራ ለይ ሲቸገር ቆይቷል፡፡ የሲሳይ መምጣትም ክፍተቱን ለመድፈን ይረዳዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ከ2003-2006 በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ምርጫ ውስጥ ሲካተቱ የቆዩት ሲሳይ እና ጀማል ጣሰው በተቀራራቢ አቋም ለቦታው ፉክክር ሲያደርጉ የምናስታውሰው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ሲሆን አሁን በአንድ ክለብ ተገናኝተዋል፡፡

ጅማ ከሲሳይ በተጨማሪ ኄኖክ ካሳሁን እና አብዱልሀኪም ሱልጣንን ማስፈሰሙ አይዘነጋም፡፡ በተጨማሪም የግራ መስመር ተከላካይ ለማስፈረም እንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡

ከአባ ቡና ጋር በተያዘ ዜና በዘንድሮ የውድድር ዘመን ለክለቡ ምንም ግልጋሎት ያላበረከቱ 3 ተጫዋቿች ተሰናብተዋል፡፡

በክረምቱ በከፍተኛ ክፍያ ወደ አባ ቡና ያመራው ቢንያም አሰፋ ከቡድኑ ከተሰናበቱት ተጫዋቾች አንዱ ነው፡፡ በጉዳት ምክንያት ለአባ ቡና ምንም ጨዋታ ያላደረገው ቢንያም ከክለቡ ጋር በደረሰው ስምምነት መሰረት ተለያይቷል፡፡

በክረምቱ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሊግ የማጠቃለያ ውድድር ባሳየው እንቅስቃሴ ወደ አባ ቡና ያመራው ኪሩቤል ተካ ሌላው ተሰናባች ተጫዋች ነው፡፡ ኪሩቤል በጥቂት ጨዋታዎች ላይ ተጠባባቂ ወንበር ላይ ከመቀመጡ በቀር ለቡድኑ ምንም ግልጋሎት ሳያበረክት ክለቡን ለቋል፡፡

ከሙገር ሲሚንቶ በክረምቱ አባ ቡናን የተቀላቀለው ማርዋን ራያ 3ኛው ተሰናባች ነው፡፡ አማካዩ እንደ ቢንያም ሁሉ ለክለቡ አንድም ጨዋታ ሳያደርግ ከክለቡ ተሰናብቷል፡፡

Leave a Reply