“የካፍ ምርጫን ማዘጋጀታችን ለእኛ ክብር ነው” ጁነይዲ ባሻ

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን ፕሬዝደንት አቶ ጁነዲ ባሻ 39ኛውን የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌድሬሽን (ካፍ) ጠቅላላ ጉባኤ ለማሰናዳት እንደተዘጋጁ ለናይጄሪያው የራዲዮ ጣቢያ ስፖርትስ ራዲዮ ብሪላ ኤፍኤም ገልፀዋል፡፡

በጠቅላላ ጉባኤው ትኩረትን ከወዲሁ የሳበው የካፍ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ሲሆን በፉክክሩ ለ28 ዓመታት ካፍን የመሩት ካሜሮናዊው ኢሳ ሃያቱ እና ማዳጋስካራዊው አህመድ አህምድ ተፋጠዋል፡፡ ጁነዲ ለስፖርት ብሪላ በሰጡት አስተያየት ኢትዮጵያ ለየትኛው እጩ ድምፅ እንደምትሰጥ ባያሳውቁም ለለውጥ ግን ትኩርት እንደምታደርገ ጠቁመዋል፡፡ “ኢትዮጵያ ሁሌም ለልማት እና ለውጥ ነው የምትጨነቀው፡፡ በካፍ ምርጫ ላይም ይህንን ነው የምንተገብረው፡፡”

ካፍ ውስጣዊ መዋቅሩ መለወጥ አለበት የሚሉ ወገኖች መብዛታቸውን ቢቀጥሉም የአህጉሪቱን እግርኳስ በበላይነት የሚመራው አካል ለለውጥ በሩ ዝግ ሆኗል ማለት ይቻላል፡፡ ሃያቱ የስልጣን ዘመናቸውን ለማስረዘም ባማለም ለፕሬዝዳንትነት የሚፎካከሩ እጩዎች የካፍ ስራ አስፈፃሚ አባላት የሆኑ ብቻ እንዲሆኑ በጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ አሳልፈዋል፡፡ በዘንድሬው ምርጫ ከወዲሁ አንዳንድ ሃገራት ለአህመድ ድምፅ ለመስጠት የተስማሙ አሉ፡፡ ምዕራቡ አፍሪካዊቷ ሃገር ላይቤሪያ፣ ናይጄሪያ እና ዚምባቡዌ ዋነኞቹ ናቸው፡፡ የደቡባዊ አፍሪካ ሃገራት ድምፃቸውን ከወዲሁ ለ57 ዓመቱ አህመድ አንደሚሰጡ በይፋ በኮሳፋ በኩል አስታውቀዋል፡፡

የፊፋ ፕሬዝደንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ የ70 ዓመቱ ሃያቱ ዳግም ፕሬዝደንት ሆነው እንዲቀጥሉ አይፈልጉም፡፡ በኢንፋንቲኖ የተደገፉት አህመድ አሁን ላይ ላለው ለውጥ ፈላጊ ትውልድ ትክክለኛው ድምፅ ናቸው የሚሉ ተባርክተዋል፡፡ ሃያቱ ከዚህ ቀደም ሁለት ግዜ የካፍ ፕሬዝዳንነትን በምርጫ ሲያሸንፉ የረቱት ከደቡባዊ አፍሪካ ሃገራት የመጡ እጩዎችን ነበር፡፡ አህመድ ለሃያቱ ብርቱ ተፎካካሪ ቢሆንም በምርጫ የማሸነፋቸው ነገር ግን አጠያያቂ ነው፡፡

አዲስ አበባ ላይ በሚካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ የሐምሌ 2015 – ሰኔ 2016 ያለው የኦዲት ሪፖርት ይቀርባል፡፡ ጉባኤው የዓመቱን በጀትም ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በታንዛኒያ እግርኳስ ፌድሬሽን አቅራቢነትም የዛንዚባር እግርኳስ ፌድሬሽንን የካፍ ሙሉ አባልነት ጥያቄም ተቀብሎ ውሳኔ እንደሚሰጥ ይጠበቃል፡፡ በተያያዘም የካፍ ፕሬዝዳንት ምርጫ እና የካፍ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላቶች ምርጫ ይደረጋል፡፡ ጁነዲ የስራ አስፈፃሚ አባል ለመሆን በምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ዞን ይወዳደራሉ፡፡ አፍሪካን በፊፋ ካውንስል የሚወክሉ አባላትም ምርጫ ይደረጋል፡፡ የኦዲት ኮሚቴ የሚመሩ አመራሮችን ለቀጣዩ 5 አመታት በጠቅላላ ጉባኤው የሚመረጡ ይሆናል፡፡

መጋቢት 5 የካፍ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባ የሚኖር ሲሆን በእለቱ የስራ አስፈፃሚ አባላቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር በቢሸፍቱ ያስገነባውን የይድነቃቸው ተሰማ አካዳሚ የምረቃ ስነ-ስርዓት እንደሚታደሙ የወጣው ፕሮግራም ያሳያል፡፡ መጋቢት 6 የካፍን 60ኛ አመት የመስረታ ክብረ በዓል በማስመልከት የአፍሪካ እግርኳስን የተመለከተ ፎረም እንደሚካሄድ ታውቋል፡፡ መጋቢት 7 ጠቅላላ ጉባኤው የሚካሄድ ይሆናል፡፡

ኢትዮጵያ ጉባኤው በማስተናገዷ ደስተኛ መሆኗን ጂነዲ ገልፀዋል፡፡ “የካፍ ምርጫን ማዘጋጀታችን ለእኛ ክብር ነው፡፡ ሁሉንም ነገር አዘጋጅተን ጨርሰናል፡፡ አፍሪካን እና ምርጫውን ለማስተናገድ ዝግጁ ነን፡፡” ጁነዲ ሲቀጥሉ “ኢትዮጵያ እንደካፍ መስራች አባልነቷ ይህንን እድል በማግኘታችን ኩራት ይሰማናል” ብለዋል፡፡

በጠቅላላ ጉባኤው እና በፎረሙ ላይ የፊፋ ፕሬዝደንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖን ጨምሮ በአፍሪካ እግርኳስ ስም ያላቸው የቀድሞ ተጫዋቾች ይገኛሉ ተብሏል፡፡

 

Leave a Reply