የጨዋታ ሪፖርት | የሁለተኛው ዙር የመጀመርያ ጨዋታ ያለ ግብ ተጠናቋል 

 የ2009 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ዙር ዛሬ ሲጀምር በቅድሚያ የተገናኙት በ13 ነጥቦች 15ኛ ደረጃ ላይ ይገኝ የነበረው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና በ19 ነጥቦች 9ኛ ደረጃን ይዞ የነበረው ወልድያ ነበሩ። በወልድያ ደጋፊዎች ድጋፍ ደመቅ ብሎ የተጀመረው ጨዋታ ቀስ በቀስ እየተቀዛቀዘ ሄዶ ነበር ያለግብ አቻ የተጠናቀቀው።

 

በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች በዮሀንስ ሃይሉ እና ጫላ ድሪባ አማካይነት ወደግብ ለመድረስ ሙከራ ያደረጉት ወልድያዎች የተሻለ መነቃቃት ታይቶባቸዋል። በተለይ ከሜዳቸው ውጪ በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ላይ በጥንቃቄ የተሞላ አጨዋወትን የሚመርጡት ወልድያዎች በመጀመሪያው ግማሽ በተሻለ ሁኔታ ወደ ፊት ገፍተው ለመጫወት ሲሞክሩ ተስተውሏል። በመከላከል ጊዜ የጫላ ድሪባን እገዛ ያገኝ የነበረው የወልድያዎች የአማካይ ክፍል በማጥቃት ወቅት ወደኋላ ተገፍቶ ይታይ የነበረውን የንግድ ባንክን የተከላካይ ክፍል ተጭኖ ለመጫወት ሙከራ ሲያደርግ ማየት ተችሏል። በተለይም በ21ኛው ደቂቃ ወልድያዎች የሰነዘሩትን ጥቃት ንግድ ባንኮች በአግባቡ ሳያርቁት ቀርተው እና ግብ ጠባቂውም ከጎሉ መጥቶ ሳለ አንዷለም ንጉሴ ኳስ አግኝቶ ከፍ አድርጎ የሞከረው እና ወደውጪ የወጣበት አጋጣሚ ቡድኑ ወደጎል ከቀረበባቸው አጋጣሚዎች መካከል ጠንካራው ነበር።

በአዲሱ አሰልጣኝ ሲሳይ ከበደ እየተመራ ወደሜዳ የገባው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አዲስ ፈራሚውን አቢኮዬ ሻኪሩን ከ ፒተር ንዋድኬ ጋር ከፊት በማጣመር እንዲሁም ለባለተሰጥኦው አማካይ ቢንያም በላይም የተሻለ የጨዋታ ነፃነት በመስጠት ነበር ጨዋታውን የጀመረው። ሆኖም ቡድኑ ብዙ የጎል ዕድሎችን መፍጠር አልቻለም ። ንግድ ባንኮች ካደረጓቸው ጥቂት ሙከራዎች መሀል በ32ኛው ደቂቃ ላይ ፒተር ኑዋዲኬ ከቀኝ መስመር የመታው እና ኤምክሪል ቤሊንጌ አስገራሚ ሁኔታ ያወጣበት የቅጣት ምት በዋናነት የሚጠቀስ ነው። ከዚህ ውጪ 22ተኛው ደቂቃ ላይ ቢንያም በላይ በጥሩ ቅብብል ያገኘውን አጋጣሚ ሞክሮ ወደላይ የወጣበት እንዲህም ፒተር እና ፍቅረየሱስ በግንባራቸው ሞክረው ቤሊንጌ ያዳነባቸው ኳሶች ሌሎች የቡድኑ የመጀመሪያ አጋማሽ ሙከራዎች ነበሩ።

ሁለተኛው የጨዋታ አጋማሽ ከመጀመሪያው በባሰ ሁኔታ ተቀዛቅዞ ታይቷል ። ወልድያዎች የሚፈጥሯቸው የግብ ዕድሎችም ከኋላ በሚላኩ ረጃጅም ኳሶች መነሻነት የሚደረጉ ነበሩ ።  አንጋፋው የቡድኑ አጥቂ አንዷለም ንጉሴ በ53ኛው እና በ75ኛው ደቂቃ ላይ ያረጋቸው ሙከራዎችሞ በዚህ ረገድ የሚጠቀሱ ናቸው ። በተለይም በ75ተኛው ደቂቃ ላይ ያሬድ ብርሀኑ ከመስመር ያሻገረውን ኳስ አንዷለም የሞከረበት መንገድ አስገራሚ ነበር። ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮችም የፈጠሯቸው ዕድሎች ይገኙ የነበሩት በ ፒተር ንዋድኬ አማካይነት ነበር ። በተለይ በ70ኛው ደቂቃ ፒተር ወደ ግብ የመታውን ኳስ ቤሊንጌ ሲመልሰው በቅርብ ርቀት የነበረው ቢንያም በላይ ለማግባት ሞክሮ ቤሊንጌ በድጋሜ ያዳነበት ኳስ ለባንክ ወሳኝ ሙከራ ነበር ። ሆኖም ግን በሁለቱም ቡድኖች በኩል በቂ የግብ ዕድሎች መፈጠር ሳይችሉ  ጨዋታው በእንቅስቃሴ እየተዳከመ ሄዶ ያለግብ ለመጠናቀቅ ተገዷል ።

Leave a Reply