የጨዋታ ሪፖርት | ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ጅማ አባ ቡና ነጥብ ተጋርተዋል

የፕሪምየር ሊጉ ሁለተኛ ዙር ሁለተኛ ጨዋታ በደረጃ ሰንጠረዡ ላለመረድ ከሚደረገው ፍልሚያ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑትን ኢትዮ ኤሌክትሪክን እና ጅማ አባ ቡናን አገናኝቶ ግብ ሳይሰተናገድበት ተጠናቋል፡፡

የመጀመሪያው አጋማሽ የቡድኖቹ ፍልሚያ በንፅፅር ጥሩ ፉክክር የተደረገበት ነበር ። ከፍተኛ የጨዋታ ፍላጎት እና ተነሳሽነት የታየባቸው ጅማ አባ ቡናዎች የቡድናቸውን ይዘት በብዛት ይጠቀሙበት ከነበረው የ4-4-2 ቅርፅ ወደ 4-2-3-1 በመለወጥ ጨዋታውን በፈጣን እንቅስቃሴዎች እና በቶሎ ጎል ላይ ለመድረስ በሚያደርጉት ጥረት በተጋጋለ መንገድ ነበር የጀመሩት። በዚህም መሰረት ከፊት በብቸኛ አጥቂነት የተሰለፈው አሜ መሀመድ የጅማዎች ቀዳሚ ለማድረግ ተደጋጋሚ ሙከራ ሲያደርግ ታይቷል። ለዚህም ወጣቱ አጥቂ በ20ኛው 32ኛው እና 38ኛው ደቂቃ ላይ ከረጅም ርቀት ያደረጋቸው ሙከራዎች የሚጠቀሱ ነበሩ ። አባ ቡና ያደረገውን የቅርፅ ለውጥ ተከትሎ የአስር ቁጥር ሚና የተሰጠው እና በነፃነት ለአጥቂው ቀርቦ ሲጫወት የነበረው ዳዊት ተፈራም ጥሩ መንቀሳቀስ ችሏል። በ43ኛው ደቂቃ ላይም ከረጅም ርቀት ያደረገው ሙከራ በሱሌይማን አቡ ተያዘበት እንጂ ቡድኑን ቀዳሚ ለማድረግ ጥሩ ዕድል ፈጥሮ ነበር ። በአጠቃላይ በመጀመሪያው አጋማሽ የአሰልጣኝ ገ/መድህን ሀይሌ ቡድን ያደረገው ለውጥ ሲጠቅመው ተስተውሏል። በተለይም የአማካይ ክፍሉ ያገኘው የቁጥር ብልጫ የተጋጣሚውን የመሀል ክፍል ለመበተን አስችሎታል ። የሁለቱ የተከላካይ አማካዮች በነፃነት የመጫወት እና ቀጥተኛ ጥቃቶችን የማጨናገፍ አጨዋወት የተሳካ የነበረ ሲሆን የመስመር አማካዩ ኪዳኔ አሰፋም እንቅስቃሴ መልካም የሚባል ነበር። ሆኖም ግን ጅማዎች በሶስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ሲደርሱ በተደጋጋሚ ኳስ ይበላሽባቸው የነበረ በመሆኑ የነበራቸው የበላይነት ፍሬያማ እንዳይሆን አድርጎታል።

በተጋጣሚያቸው የመሀል ሜዳ ብልጫ የተወሰደባቸው እና ሁለቱ አጥቂዎቻቸው በብዛት ተነጥለው ለመጫወት የተገደዱባቸው ኤሌክትሪኮች በመጀመሪያው አጋማሽ ደህና ሙከራ ሳያደርጉ ነበር የወጡት። የአማካይ ክፍሉ ቅርፅ በእጅጉ የተዛባ እና በቁመትም ሆነ በጎን ሚዛናዊነት የጎደለው በመሆኑ የመስመር ተከላካዮቹ ማጥቃቱን ለማገዝ እንዲሁም የሜዳውን ስፋት ለመጠቀም ወደፊት የሚያደርግትን እንቅስቃሴ ለማንበብ እና ኳስ ለማሰራጨት እንኳን ሲቸገር ተስተውሏል። በተከላካይ እና በኣማካይ መስመራቸው መሀከልም ሰፊ ክፍተት እየተው መጫወታቸው ኤሌክትሪኮች በቀላሉ ለጥቃት እንዲዳረጉ መንስኤ ሲሆንም ታይቷል ።

ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀምር የአሰልጣኝ ብርሀኑ ባዩ ቡድን በመጀመሪያው አጋማሽ የታየበትን ክፍተት ለማስተካከል የቅርፅ ለውጥ ያስከተለ የተጨዋቾች ቅያሪ እድርጓል። በዚህ መሰረት ብሩክ አየለን እና ዋለልኝ ገብሬን በሙሉአለም ጥላሁን እና በሃይሉ ተሻገር የቀየረው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ 4-4-2 ወደ 4-3-3 የተጨዋቾች አደራደር መጥቷል። ከዚህ ለውጥ በኋላ ቡድኑ የተሻለ መንቀሳቀስ ችሏል። ተወስዶበት የነበረውን የኳስ ቁጥጥር ብልጫም መመለስ የቻለ ሲሆን ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለም የግብ ሙከራዎችን ማድረግ ችሏል ። በተለይም በ55ኛው ደቂቃ ላይ በሀይሉ ተሻገር ከሙሉአለም ጋር በአንድ ሁለት ቅብብል ያገኘውን ኳስ ሞክሮ ወደ ውጪ የወጣበት እና በ85ኛው ደቂቃ ላይ ፍፁም ገ/ማርያም የጅማ አባ ቡናን የተከላካይ መስመር ክፍተት በመጠቀም በግራ መስመር ይዞ የገባውን ኳስ በቀጥታ ሞክሮ ወደውጪ የወጣበት ሙከራዎች በዋነኝነት የሚጠቀሱ ነበሩ።

የኢትዮ ኤሌክትሪኮችን ለውጥ ተከትሎ ጅማዎች እንደመጀመሪያው አጋማሽ ፍጥነትን እና የኳስ ቁጥጥርን ያማከለ ጨዋታ ለማድረግ ቢቸገሩም በመልሶ ማጥቃት እና በፈጣን የማጥቃት ሽግግር ላይ የተመሰረተ አጨዋወታቸው ግን ጥሩ ዕድሎችን እንዲፈጥሩ አስችሏቸዋል ። በተለይም ተቀይሮ የገባው ኄኖክ ኢሳያስ በግራ መስመር በተሰነዘረው መልሶ ማጥቃት ከዳዊት ተፈራ የተቀበለውን ኳስ የሞከረበት እና በጭማሪ ደቂቃ ላይ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የዋለው ኪዳኔ አሰፋ ከግራ መስመር ከረጅም ርቀት የሞከረውን ኳስ በኤሌክትሪኩ ግብ ጠባቂ ሱሊማን ኤቡ ባይመለሱ ኖሮ ለውሀ ሰማያዊዎቹ ሶስት ነጥብ ማስገኘት የሚችሉ አጋጣሚዎች ነበሩ። በጥቅሉ ሲታይ ግን ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው በጥቂቱ ቀዝቀዝ ብሎ የታየ እንዲሁም ተጨዋቾች በተደጋጋሚ እየተጋጩ የሚወድቁበት እና ጎሎችም ያልታዩበት ሆኖ ባማለፉ ጨዋታው ያለግብ ሊጠናቀቅ ችሏል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *