የሳምንቱ ታላቅ ጨዋታ | ደደቢት ከ ኢትዮጵያ ቡና 

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 16ኛ ሳምንት 2ኛ ዙር ትላንት በተደረጉ ጨዋታዎች ተጀምሯል፡፡ በዛሬው እለት ደግሞ በሊጉ ከፍተኛ ትኩረት ከሚሰጣቸው ጨዋታዎች መካከል አንዱ የሆነው የደደቢት እና ኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ ይካሄዳል፡፡ ሶከር ኢትዮጵያ በቅድመ ጨዋታ ዳሰሳዋ ከጨዋታው ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን እንዲህ አሰናድታቸዋለች፡፡


ቦታ – አዲስ አበባ ስታድየም

ቀን – እሁድ የካቲት 19 ቀን 2009

ሰአት – 09፡00

ስርጭት – ቀጥታ የጽሁፍ ስርጭት በሶከር ኢትዮጵያ


የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ እንዲጠበቅ የሚያደርጉ በርካታ ክስተቶች በተገናኙ ቁጥር መከሰቱ ጨዋታውን ለመመልከት ጉጉት እንዲያደድርብን ያስገድዳል፡፡ ሁሌም በተገናኙ ቁጥር ይሸናነፋሉ ፣ አሸናፊው ክለብም ድል የሚያደርገው ከመቼውም ጊዜ የላቀ ድንቅ አቋም አሳይቶ ነው፡፡ ተጫዋቾች የብቃታቸውን ጫፍ በጨዋታዎቹ ላይ ሲያሳዩም በተደጋጋሚ ተመልክተናል፡፡ በዛው መጠን ውዝግቦች እና ቀይ ካርዶች የማያጡት ጨዋታም ነው፡፡

ደደቢት እና ኢትዮጵያ ቡና የዘንድሮው የውድድር ዘመን መክፈቻ ሳምንት ላይ ነበር የተገናኙት፡፡ በጌታነህ ከበደ ሐት-ትሪክ ታግዘው 3-0 በማሸነፍ በእለቱ ተደስተው መውጣት የቻሉትም ሰማያዊዎቹ ነበሩ፡፡ አሁን ደግሞ ከ3 ወራት በኋላ የሚያደርጉት ጨዋታ የክለቦቹ የውድድር ዘመን ጉዟቸውን የመወሰን አቅም ያለው ነው፡፡ በ27 ነጥብ 2ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ደደቢት ከመሪው ቅደዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያለውን የደረጃ ሰንጠረዥ አናት ፉክክር ለማስጠበቅ ፤ በ24 ነጥቦች 6ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ኢትዮጵያ ቡናም ወደ መሪዎቹ ለመቀላቀል እና ከደደቢት ጋር ነጥቡን ለማስተካከል የሚረዳ ወሳኝ ጨዋታ ነው፡፡


የጨዋታ አቀራረብ

ሁለቱም ቡድኖች ከመስመር አጥቂዎቻቸው የግብ እድሎችን ሲፈጥሩ በተደጋጋሚ ተስተውሏል፡፡ በዚህ ጨዋታም የመስመር ላይ የበላይነት ቁልፍ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በሽመክት ጉግሳ እና ኤፍሬም አሻሞ የሚመራው የደደቢት የማጥቃት እንቅስቃሴ በአማካዮች በሚገባ ከታገዘ ውጤታማ ሆኖ ሊወጣ ይችላል፡፡ በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ቡና አማካዮች እና የመስመር ተከላካዮች ለመስመር አጥቂዎቹ (አስቻለው እና እያሱ) የሚሰጡት እገዛ ከደደቢት ተሽለው እንዲወጡ ሊያደርጋቸው ይችላል፡፡ ቡና በሜዳው ቁመትም ሆነ ስፋት የተመጣጠነ የማጥቃት ስርአት ያለው ሲሆን ደደቢት በሜዳው ስፋት የማጥቃት እንዲሁም በሜዳው ቁመት የመከላከል ዝንባሌ ያሳያል፡፡

ሁለቱም ቡድኖች ባለፉት ተከታታይ ጨዋታዎች ጥቂት ግብ ያስተናገደ ጠንካራ የተከላካይ ክፍል መመስረት ችለዋል፡፡ ደደቢት ከፍተኛ ልምድ ባላቸው አይናለም ኃይለ እና አክሊሉ አየነው የተከላካይ ክፍሉን ከማዋቀሩ ባሻገር ዋና ተግባራቸው ለተከላካይ ክፍሉ ሽፋን መስጠት በሆነው አስራት እና ኩሊባሊ እንዲታገዙ ያደርጋል፡፡ ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ ከፊት መስመር ተጫዋቾች በሚጀምር የመከላከል ስራ እና ኳስን በመቆጣጠር ተጋጣሚያቸው ወደ አደጋ ክልላቸው እንዳይጠጋ ለማድረግ ይሞክራሉ፡፡

በአጠቃላይ ሁለቱ ቡድኖች ለጨዋታ በሚቀርቡበት መንገድ ላይ ልዩነት መኖሩ ጥሩ ጨዋታ እንድናይ ይረዳናል፡፡


የቅርብ ጊዜ አቋም

ደደቢት | አቻ-አሸ-አቻ-ተሸ-አሸ

ደደቢት የአንደኛውን ዙር ያገባደደው ወላይታ ድቻን ከመልካም እንቅስቃሴ ጋር 3-0 በመርታትና 2ኛ ደረጃን በመያዝ ነው፡፡ ነገር ግን ያለፉት 5 ተከታታይ ጨዋታዎችን ውጤት ስንመለከት ቡድኑ የአቋም መዋዠቅ እንደሚታይበት ማስተዋል ይቻላል፡፡

ኢትዮጵያ ቡና | አሸ-አቻ-አሸ-አሸ-አቻ

ኢትዮጵያ ቡና 1ኛውን ዙር ያጠናቀቀው በመልካም አቋም ላይ ሆኖ ነው፡፡ ካለፉት 5 ጨዋታዎች የሰበሰባቸው 11 ነጥቦችም ከአስከፊ አጀማመሩ አገግሞ ከመሪዎቹ ጋር ያለውን ልዩነት እንዲያጠብ አድርጎታል፡፡


የቅርብ ጊዜ ግንኙነቶች

ሁለቱ ክለቦች ባለፉት ሶስት ግንኙነታቸው በ2008 የመጀመርያ ዙር ደደቢት 2-1 ሲያሸንፍ በ2ኛው ዙር ኢትዮጵያ ቡና 3-0 አሸንፏል፡፡ በ2009 የመጀመርያ ዙር ደግሞ ደደቢት 3-0 አሸንፏል፡፡


ጉዳት እና ቅጣት

ደደቢት የቀኝ መስመር ተከላካዩ ስዩም ተስፋዬን ግልጋሎት በዚህ ጨዋታ ላይ አያገኝም፡፡ ከዚህ ውጪ በደደቢትም ሆነ በቡና በኩል የሚገኙ ተጫዋቾች ለጨዋታው ብቁ ናቸው፡፡


ምን ተባለ?

አስራት ኃይሌ – የደደቢት አሰልጣኝ

ጥሩ ተጫውተን አሸንፈን ለመውጣት እንታገላለን። ሁሉም ቡድን አሸንፋለው ብሎ እንጂ እሸነፋለው ብሎ አይመጣም፡፡ ኢትዮጵያ ቡናዎችም ያለፈው ስህተታቸውን አርመው ጠንክረው እንደሚመጡ እናውቃለን፡፡ እኛም በመጀመርያው ዙር አሸንፈናል ብለን የምንኩራራበት ነገር አይኖርም፡፡ የተሻለ እንቅስቃሴ አድርገን ውጤቱን አስጠብቀን እንወጣለን፡፡

እድሉ ደረጀ – የኢትዮጵያ ቡና ምክትል አሰልጣኝ

ለእሁዱ ጨዋታ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ቡድን ዝግጅት አድርገናል። ሁሉም ጨዋታ ለእኛ ከባድ ነው ፤ በመሆኑም በሚገባ ተዘጋጅተናል። የባለፈው የ3-0 ሽንፈት የሚያመጣው ተነሳሽነትም ሆነ የሚያሳድርብን ተፅእኖ የለም፡፡ ምክንያቱም የዛን ጊዜ ቡናና አሁን ያለው ቡና ፍፁም የተለያየ ነው። ቡድናችን ከፍተኛ የሆነ መሻሻል አሳይቷል፡፡ በእኛ በኩል ጨዋታውን አሸንፎ ለመውጣት መነሳሳት አለ።


ጨዋታውን ማን ይመራዋል?

የእለቱን ጨዋታ የ2007 የውድድር ዘመን ኮከብ ዳኛ ኢንተርናሽናል አርቢቴር ኃይለየሱስ ባዘዘው ይመራዋል፡፡


ግምታዊ አሰላለፍ

ኢትዮጵያ ቡና (4-3-3)

ሀሪስን ሄሱ

አብዱልከሪም መሃመድ – ኤፍሬም ወንድወሰን– ወንድፍራው ጌታሁን – አህመድ ረሺድ

አማኑኤል ዮሃንስ – ጋቶች ፓኖም (አምበል) – ኤልያስ ማሞ

እያሱ ታምሩ – ሳሚ ሳኑሚ – አስቻለው ግርማ

ደደቢት (4-3-3)

ክሌመንት አዞንቶ

ደስታ ደሙ – አይናለም ኃይለ – አክሊሉ አየነው – ብርሃኑ ቦጋለ (አምበል)

ካድር ኩሊባሊ – አስራት መገርሳ – ሳምሶን ጥላሁን

ሽመክት ጉግሳ – ጌታነህ ከበደ – ኤፍሬም አሻሞ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *