ፕሪምየር ሊግ | ከሜዳቸው ውጪ የተጫወቱ ክለቦች አስደሳች ሳምንት አሳልፈዋል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 2ኛ ዙር ትላንት ተጀምሮ ዛሬ በተደረጉ 6 ጨዋታዎች ቀጥሎ ሲውል ቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ ሲዳማ ቡና እና ሀዋሳ ከተማ ከሜዳቸው ውጪ ጣፋጭ ድል አስመዝግበዋል፡፡

ወደ ጎንደር ያቀናው ሲዳማ ቡና ፋሲል ከተማን ከድንቅ እንቅስቃሴ ጋር 3-1 በመርታት ደረጃውን ወደ 3ኛ ከፍ አድርጓል፡፡ ሄይቲያዊው ሳውሬል ኦልሪሽ በቅጣት ምት ባስቆጠረው ጎል ሲዳማ ቡናን ቀዳሚ ሲያደርግ ናትናኤል ጋንጂላ ፋሲልን አቻ አድርጎ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡ ፈጣኑ አጥቂ አዲስ ግደይ በ71ኛው ደቂቃ የይርጋለሙን ክለብ በድጋሚ መሪ ሲያደርግ ወሰኑ ማዜ ጨዋታው ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩት የሲዳማን መሪነት ወደ ድልነት ያሸጋገረች ግብ አስቆጥሮ በሲዳማ ቡና አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ በጨዋታው ፋሲል ከተማዎች የፍፁም ቅጣት ምት ይገባን ነበር በሚል አርቢቴር በአምላክ ተሰማ ላይ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡

ወደ አርባምንጭ ያመራው ቅዱስ ጊዮርጊስ ድል አስመዝግቦ መሪነቱን አጠናክሯል፡፡ ፈረሰኞቹ በሃይሉ አሰፋ ባስቆጠረው ጎል ቀዳሚ ሆነው እረፍት ሲወጡ ከእረፍት መልስ አዳነ ግርማ አከታትሎ ያስቆጠራቸው ግቦች የቅዱስ ጊዮርጊስን መሪነት ወደ 3-0 አስፍቶታል፡፡ ታደለ መንገሻ በ89ኛው ደቂቃ የጎል ልዩነቱን ያጠበበች ግብ ቢያስቆጥርም ተቀይሮ የገባው አይቮሪያዊው አዲስ ፈራሚ ብሩኖ ኮኔ የማሳረጊያዋን ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በቅዱስ ጊዮርጊስ 4-1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ስታዲየሙ በከፍተኛ ሁከትና ግርግር ታምሶ በሰዎች ላይ ጉዳት ተከስቷል፡፡

አዲስ አበባ ስታድየም እንደትላንቱ ሁሉ ዛሬም በጎል ድርቅ ተመትቶ ውሏል፡፡  ከሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታዎች አንዱ የነበረው የደደቢት እና ኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ 09:00 ላይ ተካሂዶ ያለ ግብ ተጠናቋል፡፡ ኢትዮጵያ በግብ ሙከራዎች የታጀበ እንቅስቃሴ ቢያደርግም የደደቢትን ጠንካራ የተከላካይ መስመር መስበር ሳይችል ቀርቷል፡፡

11:30 ላይ መከላከያን የጎበኘው ወላይታ ድቻም ጨዋታውን ያለ ግብ በአቻ ውጤት አጠናቋል፡፡ በዋነኝነት የመከላከል ዕቅድን ይዘው የገቡት ድቻዎች በጨዋታው አብዛኛው ክፍል ከኳስ በስተጀርባ ሆነው ሲያሳልፉ መከላከያዎችም የተጋጣሚያቸውን የመከላከል አጥር ለመስበር ያደረጓቸው ሙከራዎች የተሳኩ መሆን ባለመቻላቸው ጨዋታውን በስድስተኛ ተከታታይ የአቻ ውጤት ለመደምደም ተገደዋል።

በዚህም ትላንት በንግድ ባንክ እና ወልድያ እንዲሁም በኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ጅማ አባ ቡና መካከል የተደረጉትነ ንጨዋታዎች ጨምሮ በሳምንቱ በተደረጉ አራቱም ጨዋታዎች የአዲስ አበባ ስታድየም ግብ ሳይስተናገድበት ተጠናቋል፡፡

ወደ አዲስ አበባ ተጉዞ አበበ ቢቂላ ስታድየም ላይ አዲስ አበባ ከተማን የገጠመው ሀዋሳ ከተማ ሌላው ከሜዳው ውጪ ድል ያስመዘገበ ክለብ ነው፡፡ በመጀመርያው አጋማሽ የሀዋሳ ፣ በሁለተኛው ግማሽ ደግሞ የአአ ከተማ ብልጫ የታየበትን ጨዋታ ውጤት የወሰነች ብቸኛ ግብ የተገኘችው በ69ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት የተሻገረውን ኳስ ጊት ጋትኮች በራሱ ግብ ላይ አስቆጥሮ ነው፡፡ የትኬት ቆራጮች ዘግይተው በመምጣታቸው ጨዋታው ከተጀመረ በኋላ ሜዳ የገባውን ተመልካች ሁለት ጊዜ እንዲወጣ ማድረጋቸው የጨዋታው ክስተት ነበር፡፡ ሁኔታው ተመልካቹ እንዲጉላላ እና ጨዋታውን የመመልከት ፍላጎት እንዲያጣ ያደረገ ነበር፡፡

ወደ ድሬዳዋ ያመራው አዳማ ከተማ ድል ለማስመዝገብ ተቃርቦ በመጨረሻ ነጥብ ጥሎ ወጥቷል፡፡ የአምናው ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ታፈሰ ተስፋዬ በ5ኛው ደቂቃ ከመስመር የተሻገረውን ኳስ በግርግር መሃል አስቆጥሮ አዳማ ከተማን ቀዳሚ ቢያደርግም ውጤት ለማስጠበቅ በጥልቀት ማፈግፈጋቸው የኋላ ኋላ ዋጋ አስከፍሏቸዋል፡፡ በረከት ይስሃቅ መደበኛው 90 ደቂቃ ተጠናቆ በተጨማሪ ደቂቃ ያሻማው የማዕዘን ምት በቀጥታ ወደ ግብነት ተቀይሮ ድሬዳዋን አቻ ማድረግ ችሏል፡፡

በአጠቃላይ በ16ኛው ሳምንት የኢተዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከሜዳቸው ውጪ የተጫወቱ ክለቦች አስደሳች ውጤት ማስመዝገብ ችለዋል፡፡ ሀዋሳ ከተማ ፣ ሲዳማ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ድል ሲያስመዘግቡ አዳማ ከተማ ፣ ጅማ አባ ቡና ፣ ወልድያ እና ወላይታ ድቻ ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *