የአሰልጣኞች አስተያየት፡ ደደቢት 0-0 ኢትዮጵያ ቡና

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ16ኛ ሳምንት ተጠባቂ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡናን ያስተናገደው ደደቢት ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል፡፡ ከአቻ ውጤቱን በኃላ የሁለቱም ክለብ አሰልጣኞች ለጋዜጠኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

“የምንፈልገውን አንድ ነጥብ አግኝተናል” አስራት ሀይሌ

ስለጨዋታው

“በእግርኳስ ጨዋታ ሶስት ነገሮች አሉ፡፡ ታሸንፋለህ፣ ትሸነፋለህ እና አቻ ትወጣለህ፡፡ ስለዚህም አቻ ወጥተን የምንፈልገውን አንድ ነጥብ አግኝተናል፡፡”

“ከመሃል ክፍል ላይ የተፈጠሩ ችግሮች ነበሩ፡፡ አስራት መገርሳ ሲያሟሙቅ ጉዳት ደረሰበት፡፡ የሱ መውጣት የነበረውን እንቅስቃሴ በሙሉ አበላሸብን፡፡ ስለዚህ እሱ ቦታ ላይ ያስገናባነው ዳዊትን ነበር፡፡ ዳዊት እንደ የአጥቂ አማካይ ሆኖ ነው የተጫወተው፡፡”

“ሁለተኛ እቅድ ምንም ሳናስበው ሜዳ ላይ ነው የተሰራው ምክንያቱም የሰራነው ስራ በሙሉ ከአስራት ጋር የተያያዘ ነበር አብዛኛው፡፡ የአስራት መቀረት ሳምሶንን ወደኃላ መለሰው፡፡ ኳስን ወደፊት የሚያደርስ አማካይ በዚሁ አጣን ዳዊት የአማካይነት ባህሪ ሳይሆን የአጥቂነት ባህሪ ስላለው በዚህ ምክንያት ወደ ግብ መድረስ አልቻልንም፡፡ የተገኘው ውጤት እንደቡድን ጥሩ ነው፡፡ አስቀያሚ አይደለም፡፡”

“ትልቁ ችግር የምናገኛቸውን እድሎች አለመጠቀም ነው” ገዛኸኝ ከተማ

ስለጨዋታው

“ጨዋታው ጥሩ ነው፡፡ ጥሩ እንቅስቃሴ የታየበት ጨዋታ ነው፡፡ በደረጃ ላይ ያለን ቡድኖች ነን ስለዚህም ጥሩ እንቅስቃሴ ታይቷል፡፡ የሁለተኛው ዙር የመጀመሪያ ጨዋታ ነው፡፡ አንድ ነጥብም ዋጋ አለው፡፡  ሆኖም ግን ማሸነፍን አላማ አድርገን ነበር የገባነው፡፡”

“ቡድናችን ላይ የታየው ትልቁ ችግር የምናገኛቸውን እድሎች አለመጠቀም ነው፡፡ የማጥቃቱ ወረዳ የመጨረሻው ክፍል ላይ ስንገባ ኳሶችን የመጨረስ ችግር አለብን፡፡”

“የመስመር አጨዋወታችን ላይ የተጋጣሚ ቡድን እንቅስቃሴ እና አጨዋወት ላይ ተፅእኖ ነበረው፡፡ ኳስን መስርተን እየተጫወትን ነው፡፡ በኳስ ቁጥጥሩም የእኛ ቡድን የተሻለ ነበር፡፡”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *