ሳላዲን ሰኢድ ለአል-አህሊ ፈረመ

ለሳምንታት ከግብፁ ታላቅ ክለብ ዝውውር ጋር ስሙ ሲያያዝ የቆየው ሳላዲን ሰኢድ በመጨረሻም ማረፊያውን ካይሮ ማድረጉን ኪንግፉት ዘግቧል፡፡ የ25 አመቱ ግብ አዳኝ ዘንድሮ በሃገር ውስጥ እና የአፍሪካ ውድድሮች ያሳየውን ብቃት ተከትሎ የአፍሪካ ታላላቅ ክለቦች አይን አርፎበታል፡፡

በሁለቱ የግብፅ ታላላቅ ክለቦች አል-አህሊ እና ዛማሌክ እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ ክለቦች ክትትል ስር የቆየው ሳላዲን በዚህ የውድድር ዘመን መጨረሻ ከዋዲ-ዴግላ ጋር ያለው የ3 አመት ኮንትራት ይጠናቀቃል፡፡ በዚህም ምክንያት አልአህሊን በውድድር ዘመኑ መጨረሻ በቦስማን ህግ በነፃ ዝውውር ይቀላቀላል፡፡

የሳላዲን ሰኢድ ወኪል የሆነው አብዱልራሂም መግኒ ለኪንግ ፉት እንደተናገረው ከሁለቱ የግብፅ ክለቦችና ከግብፅ ውጪ ከሚገኙ ክለቦች ጥያቄዎች ቀርበውለት ነበር፡፡ ሳላዲን በውድድር ዘመኑ መጨረሻ ከአል – አህሊ ጋር የሶስት አመት ኮንትራት ይፈራረማል፡፡ የደሞዝ መጠኑ ይፋ ባይሆንም ከ25-30ሺህ ዶላር ወርሃዊ ክፍያ ሊያገኝ እንደሚችልም ተነግሯል፡፡

ባለፈው ሳምንት የዛማሌኩ አሰልጣኝ አህመድ ሆሳም ‹‹ ሚዶ ›› ሳላዲን ሰኢድ ለዋዲ ዴግላ በአፍሪካ ውድድሮች በመጫወቱ ዝውውሩን ለማጠናቀቅ እንዳመነታ መናገሩ ይታወሳል፡፡

ጉዳት ላይ ያለው ሳላዲን በሁለት ሊግ በተከፈለው የዘንድሮው የግብፅ ፕሪሚየር ሊግ 7 ግቦች ፣ በአፍሪካ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ ደግሞ 1 ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡

{jcomments on}

ያጋሩ