የመጀመሪያ አምበሉን ምክትል አሠልጣኝ ያደረገው ባህር ዳር ከተማ ሁለት አምበሎችን ሲሾም ሦስተኛ አምበል ደግሞ በተጫዋቾች እንዲመረጥ ዕድሉን ሰጥቷል።
አሠልጣኝ አብርሃም መብራቱን በመሾም በርካታ አዳዲስ ተጫዋቾችን በማስፈረም ጥቅምት 8 ለሚጀምረው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እየተዘጋጁ የሚገኙት ባህር ዳር ከተማዎች ለ15ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ውድድር ከትናንት በስትያ መዲናችን በመግባት በዋሺንግተን ሆቴል ማረፊያቸውን አድርገዋል። በርካታ አዳዲስ ተጫዋቾችን በማስፈረም እንደ አዲስ ቡድኑን እየገነባ የሚገኘው ክለቡም በዛሬው ዕለት አንደኛ እና ሁለተኛ አምበሎቹን ይፋ አድርጓል።
የቡድኑ የመጀመሪያው አምበል የሆነው አማካዩ ፍቅረሚካኤል ዓለሙ ነው። ያለፉትን ዓመታት ፍቅረሚካኤል ሁለተኛ አምበል ቢሆንም ደረጄ መንግሥቱ (የመጀመሪያ አምበል) ቋሚ ተሰላፊ ባለመሆኑ የ2013 የውድድር ዓመትን በሙሉ ቡድኑን በአምበልነት መምራቱ የሚታወስ ነው።
ሁለተኛ አምበል በመሆን በአሠልጣኝ ቡድን አባላት የተሾመው ደገሞ የመስመር ተከላካዩ አህመድ ረሺድ ነው። 2013 ላይ ክለቡን የተቀላቀለው አህመድ ክለቡን በወጥነት ሲያገለግል መቆየቱ አይዘነጋም። አሁን ደግሞ በሁለተኛ አምበልነት ሚና ከክለቡ ጋር እንደሚቀጥል ታውቋል። ሦስትኛ አምበል እስካሁን ያላገኘው ቡድኑ ተጫዋቾች ራሳቸው ተነጋግረው እንዲመርጡ ዕድሉን የአሠልጣኝ ቡድን አባላቱ እንደሰጡ ታውቋል።