ስዩም ከበደ ከአአ ከተማ አሰልጣኝነት ለቀቁ

አሰልጣኝ ስዩም ከበደ ከአዲስ አበባ ከተማ እግርኳስ ክለብ አሰልጣኝነት ስራቸው በገዛ ፍቃዳቸው መልቀቃቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ ለክለቡ ማስገባታቸው ታውቋል፡፡

ከየመኑ አልዋሂዳ ሰንአ ከተመለሱ በኋላ በ2008 የውድድር ዘመን መጀመርያ አዲስ አበባ ከተማን የተቀላቀሉት አሰልጣኝ ስዩም ከበደ በመጀመርያ አመት የክለቡ ቆይታቸው ወደ ፕሪምየር ሊግ እንዲያድግ ያደረጉ ሲሆን ክለቡ በዘንድሮው አመት የፕሪምየር ሊግ ቆይታ የመጨረሻ ደረጃን ይዞ ይገኛል፡፡ አሰልጣኝ ስዩምም በአመቱ መጀመርያ በሚፈልጉት መንገድ የዝግጅት ጊዜ እና ተጫዋቾች አለማግኘታቸው በውጤት ላይ ተፅእኖ እንደፈጠረ እና ነገሮችን ለማስተካከል መጣራቸውን ገልጸው  ክለቡ ወደ ከፍተኛ ደረጃ እንዲሸጋገር መልካም ምኞታቸውን በመግለፅ ክለቡን ለመልቀቅ እንደወሰኑ በደብዳቤ አስታውቀዋል፡፡

በጉዳዩ ዙርያ ከክለቡ የተሰጠ ማብራርያ የሌለ ሲሆን በቀጣይ ክለቡን ስለሚረከበው አሰልጣኝ እና ዝርዝር ጉዳዮች ተከታትለን የምናቀርብ ይሆናል፡፡

Leave a Reply