ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ሁለት ጨዋታዎች ዝግጅት የጀመረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ስድስቱን የፈረሰኞቹን ተጫዋቾች ሲያገኝ አንድ ተጫዋች በዲሲፕሊን ቀንሶ ለአዲስ ተጫዋች ጥሪ አስተላልፏል።
በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ኳታር ለምታስተናግደው የዓለም ዋንጫ ለማለፍ የምድብ የማጣሪያ ጨዋታዎችን እያደረገ እንደሆነ ይታወቃል። የቡድኑ አሠልጣኝም ባሳለፍነው ሳምንት ለ25 ተጫዋቾች ጥሪ በማድረግ ዝግጅት ለመጀመር የተንቀሳቀሱ ሲሆን ከቅዱስ ጊዮርጊስ የተመረጡት አማኑኤል ገብረሚካኤል፣ ምኞት ደበበ፣ ሱሌይማን ሀሚድ፣ ጋቶች ፓኖም፣ ቸርነት ጉግሳ እና አቤል ያለው ክለባቸው ሳይፈቅድ ቀርቶ በተባለው ጊዜ ስብስቡን አልተቀላቀሉም ነበር።
ከትናንት በስትያ ቀትር ወደ ባህር ዳር ያመራው ልዑኩም በስፍራው ደርሶ የመጀመሪያ ልምምዱን ከሰዓት ከሰራ በኋላ አመሻሽ ላይ ስድስቱን ተጫዋቾች ማግኘቱ ታውቋል። ምንም እንኳን ተጫዋቾቹ የቅዳሜው ልምምድ ላይ ባይኖሩም ትናንት ጠዋት በተሰራው ሁለተኛ ልምምድ ላይ ከአጋሮቻቸው ጋር በመሆን መሳተፋቸው ታውቋል።
ከቡድኑ ጋር በተያያዘ ሌላ ዜና ባሳለፍነው ረቡዕ ቡድኑን ተቀላቅሎ በማግስቱ የኮቪድ-19 ምርመራ አድርጎ የነበረው የኢትዮጵያ ቡናው ታፈሰ ሠለሞን በዲሲፕሊን ምክንያት ከቡድኑ እንደተቀነሰ ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች። ተጫዋቹ ከቡድኑ ከተቀነሰ በኋላም በምትኩ የፋሲል ከነማው አማካኝ በዛብህ መለዮ መጠራቱም ተጠቁሟል። ይህንን ተከትሎም በግብፁ አል ጎውና ከሚጫወተው ሽመልስ በቀለ ውጪ 24ቱም ተጫዋቾች በአሁኑ ሰዓት ብሉ ናይል (አቫንቲ) ሆቴል የሚገኙ ይሆናል።