ዋሊድ አታ ሩቅ ያልማል

ዋሊድ አታ ባለፈው ወር የስዊድኑን ቢኬ ሃከን ለቆ ጉዞውን ታላላቆቹ የኢስታንቡል ክለቦች በሚገኙበት የቱርክ ሱፐር ሊግ የሚወዳደረው ጊንኪልቢርጊን ተቀላቅሏል፡፡ የ28 አመቱ የኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ስለ አዲሱ ፈተናው እና የቀድሞ ክለቡ በቅርቡ ያደረገውን ቃለምልልስ እንዲህ አቅርበነዋል፡፡

‹‹ እዚህ ምን ያህል ርቀት መሄድ እንደምችል ማሳየት እፈልጋለሁ ››

ዋሊድ ቢኬ ሃከንን ለቆ የቱርኩን ክለብ በ3 አመት ኮንትራት የተቀላቀለው ባለፈው ኤፕሪል ወር ቢሆንም በመጪው ጁላይ ወር የአውሮፓ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት እስኪከፈት ድረስ ለአዲሱ ክለቡ በነጥብ ውድድሮች መጫወት አይችልም፡፡ ታድያ ዋሊድ ካለ ጨዋታ የሚያሳልፈውን ጊዜ እንዴት እያሳለፈው ነው ? ‹‹ በሀምስታድ ከተማ ከሲሞን ባካዊ ጋር ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን እሰራለሁ፡፡ ሲሞን በስዊድን ትልቁ ሊግ በርካታ ተጫዋቾችን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያሰራል፡፡ ሁልጊዜ እሮጣለሁ ፣ አካላዊ እንቅስቃሴዎችን በስፖርት ማሽኖች ታግዤ እሰራለሁ፡፡ ›› ይላል፡፡

ዋሊድ በ1 ሳምንት ጊዜ ውስጥ የቱርኩን ክለብ ለመቀላቀል ወደ አንካራ ይበራል፡፡ በሁኔታዎች ሁሉ ደስተኛ እና ጠንከራ ስሜት እየተሰማው ነው፡፡ በቅድመ ውድድር ዘመን ወቅት ከጉልበት ጉዳቱ ጋር ሲታገል የነበረው ዋሊድ በ2015 ጥሩ አመት ማሳፍ ባልቻለው ቢኬ ሃከን ምንም የሊግ ጨዋታ አላደረገም፡፡ ነገር ግን በቱርክ ጥሩ ጊዜ እንደሚያሳልፍ ያምናል፡፡

‹‹ ክለቡ (ቢኬ-ሃከን) ጥሩ የውድደር ዘመን ጅማሬ ላይ ባለነበረበት ሰአት መልቀቄ ከባድ ነው፡፡ ነገር ግን የውድድር ዘመኑ ገና ረጅም ነው፡፡ ወደ ጥሩ ሁኔታ እንደሚመለሱ አምናለሁ፡፡ ከስዊድን ውጪ ባሉ ክለቦች መጫወት የሁልጊዜ ምኞቴ ነበር፡፡ የክለቡ አጀማመር ጥሩ አለመሆን ለውሳኔዬ አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡ ስዊድንን መልቀቅና አዲስ ፈተናን መጋፈጥ ስፈልግ ስለነበር ዝውውሩ አስደስቶኛል ›› ይላል፡፡

ጌንኪልቢርጊ በቱርክ ሱፐር ሊግ 8ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን በቡድኑ ውስጥ ከዚህ ቀደም በቢኬ ሃከን የተጫወተው ሜርቫን ሴሊክ ይገኛል፡፡ ዋሊድም በአዲሱ ክለቡ ባየው ነገር ሁሉ ደስተኛ እንደሆነ ይናገራል፡፡

‹‹ ክለቡ በእኔ እምነት እንዳለው አሳይቶኛል፡፡ እኔም እዚህ የተገኘሁት ያለኝን ነገር ሁሉ ለክለቡ ለማበርከት ነው፡፡ በዚህ ክለብ ያለው አደረጃጀት እና ፍልስፍና ከሆላንዱ ታላቅ ክለብ አያክስ አምስተርዳም ጋር ተመሳሳይነት እንዳለው ተነግሮኛል፡፡ ››

ዋሊድ በቱርኩ ክለብ ደስተኛ ቢሆንም ህልሙ በጌንኪልቢርጊ ብቻ እንደማይቆም ያምናል፡፡ ‹‹ በጌንኪልቢርጊ የተመለከትኩት ነገር ጥሩ ቢሆንም ከዚህ የተሻለ ነገር አላስብም ማለት አይደለም፡፡ ጊንኪልቢርጊ የመጨረሻ መድረሻዬ አይደለም፡፡ ከዚህም ከፍ ያሉ ህልሞች አሉኝ፡፡ ወደፊት ምን ደረጃ እንደምደርስ ማየትን እጓጓለው፡፡ ወደፊት ለመጓዝ መጣሬን አላቆምም›› ሲል ህልሙን ይናገራል፡፡

በመጨረሻም 1 ሙሉ የውድድር ዘመን እና 26 የሊግ ጨዋታ ያደረገበት ቢኬ ሃከንን ያመሰግናል፡፡

‹‹ ክለቡ ላደረገልኝ ነገር በሙሉ አመሰግናለሁ፡፡ ወደፊት እንድጓዝ እድሉን ሰጥተውኛል፡፡ በክለቡ ባሳለፍኳቸው ጊዜያት ጥሩ ትዝታ አትርፌ ወደ ቱርክ አመራለሁ፡፡ የምመለስበት አጋጣሚም ካገኘው ለክለቡ በድጋሚ የማልጫወትበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ በእኔ የእግርኳስ ህይወት ውስጥ ትልቅ ቦታ ያላቸው አሰልጣን ፒተር ጌርሃርድሰንንም ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡ እርሱ የስዊድን ምርጡ አሰልጣኝ ነው፡፡ ለእኔ እግርኳስ እድገት ከፍተኛውን ድርሻ አበርክቷል፡፡ ››

ያጋሩ