” አሁንም የሴቶች ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ነኝ ብዬ ነው የማስበው” መሰረት ማኒ

አሰልጣኝ መሰረት ማኒ በመስከረም ወር የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድንን በሴካፋ ሴቶች ውድድር ከመራች በኋላ ካለአሰልጣኝነት ስራ አሳልፋለች፡፡ ያለፉትን ሦስት ሳምንታት በዩናይትድ ስቴትስ ስልጠናዎችን በመውሰድ ወደ ሀገሯ የተመለሰችው አሰልጣኝ መሰረት ስለወሰደችው ስልጠና እና ተያያዥነት ያላቸውን ጥያቄዎች እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡

የስልጠናውን እድል እንዴት ልታገኚ ቻልሽ?

IVLP (International Visionary Leaders Program) የሚባል በአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመት ስር የሚገኝ ተቋም በሁሉም ሀገሮች በየአመቱ በሀገራቸው ላይ ስራ የሚሰሩ ሴቶችን የተሻለ ነገር እንዲሰሩ ፣ ልምድ እና ተሞክሮዎችን እንዲያገኙ እገዛ የሚያደርግ ሲሆን በስልጠናውም ሦስት ሳምንታት ቆይቻለሁ።

ስልጠናው እንዴት ነበር?

ስልጠናው በብዙ ነገሮች ፤ ሁሉንም ያካተተ በተለይ ሴቶች በተሰማሩበት የስራ ዘርፍ  የማብቃት እና ውጤታማ እንዲሆኑ ማገዝ ላይ ያተኮረ ነበር። ስልጠናው በእኔ ላይ ብዙ ነገሮች ጨምሯል ፤ የበለጠ እንድሰራ ትልቅ እውቀት ሰጥቶኝ ያለፈ ስልጠና ነበር።

የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የዘንድሮ አመት ውድድር እንዴት አየሽው?

በጣም ጥሩ ሁኔታ ነው ያለው ፤ እውነት ለመናገር በዘንድሮ ደግሞ በተሻለ ሁኔታ እየተካሄደ ይገኛል። በተለይ የውድድር ፎርማቱ በሁለት ምድብ ተከፍሎ ሁሉም ቡድኖች እንዲገናኙ መደረጉ ትልቅ ጥንካሬ ነው። ሌላው ገንዘብ መጠኑ ከፍ ዝቅ ይበል እንጂ ሁሉም ተጫዋቾች ተከፋይ መሆናቸው ትልቅ ነገር ነው። የሴቶችን እግር ኳስ አውቀዋለው ፤ ሰርቼበትም አልፌአለው። ከዛ ወጥቶ ዛሬ ተጫዋቾች ተከፋይ መሆናቸው ጥሩ ጎኑ ነው። ሌላው የጨዋታ እንቅስቃሴ ስንመለከት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተለወጠ መጥቷል አዳዲስ ክለቦች ላይ የማየው ነገር በጣም ተስፋ ሰጪ ነው። ጊዜ ሊወስድ ይቸላል እንጂ ነገ ብሔራዊ ቡድን በሚገባ ሊተኩ የሚችሉ ወጣቶች የምናገኝበት ይሆናል። ከዘህ ቀደም በሴቶች እግር ኳስ ላይ የታክቲክ ችግር ነበር ዘንድሮ ግን ይህ ችግር ተቀርፏል ። ብዙ ጎሎች ይቆጠሩ ነበር ታክቲካል ዲሲፒሊን አልነበረም አሁን ግን ተፎካካሪነቱ ጨምሯል ትልልቅ ክለቦች በቀላሉ ማሸነፍ ተቸግረዋል ይህ ለውጥ ነው። በዚህ አጋጣሚ ሳላደንቅ የማላልፈው የፕሪሚየር ሊግ ቡድኖች የሴቶች ቡድን ማቋቋም ተስኗቸው የክፍለ ከተማ ቡድኖች ለሴቶች እግር ትኩረት ሰተው ቡድን በማቋቋማቸው ሊደነቁ ይገባል ።

የዘንድሮ ድሬዳዋ ከተማ በውጤቱ መልካም ጉዞ እያደረገ አይገኝም፡፡  ይህን እንዴት አየሽው? ከአምናው የአንቺ ቡድን ጋርስ እንዴት ታነፃፅሪዋለሽ? 

እንግዲህ እኔ እንደ አሰልጣኝ ያው በአሁን ሰአት ያለው አሰልጣኝ ስለ እራሱ ቡድን ያለበትን ሁኔታ ቢናገር መልካም ነው። አሁን ስላለው ቡድን ልናገር አልፈልግም ፤ ድክመቱንም ጥንካሬውንም እራሱ አሰልጣኙ ቢናገር መልካም ነው። የኔ የአምናው ቡድን ግን ጥሩ ነበር፡፡ በመጨረሻዎቹ ሳምንታት በራሳችን ድክመት ነጥብ ጣልን እንጂ ጥሩ ጉዞ አድርገን ነበር። ከዚህም ብዙ ነገሮችን ተምሬበታለው ብዬ አስባለው።

አሁን በምን ሁኔታ ላይ ትገኛለሽ? ስራ ላይ አትታይም ፤ ከብሔራዊ ቡድን ጋርስ ተለያየሽ? በቀጣይስ ምን ታስቢያለሽ?

ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር አለው ብዬ ነው የማስበው ፤ ከፌዴሬሽኑም ጋር እየተነጋገርን ነው የምንገኘው፡፡ ከብሔራዊ ቡድን ጋር በተያያዘ ብዙ ጊዜ ችግሮች አሉ ፤ ውድድሮች የማግኘት እድሉ ጠባብ ነው። ከውጪ ከመጣሁ ጥቂት ቀናት ሆኖኛል፡፡ አሁን ድሬዳዋ ነው ያለሁት፡፡ ከሳምንት በኋላ አዲስ አበባ በመምጣት ከፌዴሬሽኑ ጋር በመነጋጋር በቀጣይ ምን ሊሆን እንደሚችል አብረን የምናየው ይሆናል፡፡

Leave a Reply