16ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ዛሬ እና ነገ ይካሄዳሉ

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 2ኛ ዙር 16ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ እና ነገ ሲቀጥሉ መብራት ኃይል በዛሬው ብቸኛ መርሃ ግብር ወላይታ ድቻን 11፡00 ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም ያስተናግዳል፡፡ የዮርዳን ስቶይኮቭ መብራት ኃይል 2ኛው ዙር ከተጀመረ በኋላ በሁለት ጨዋታዎች 4 ነጥቦች ሰብስቦ ከወራጅ ቀጠናው የመውጣት ትግሉን አፋፍሟል፡፡ በአንፃሩ ወላይታ ድቻ ካለፉት 4 ጨዋታዎች 2 ነጥቦች ብቻ ሰብስቦ ከመሪው በርቀት ተቀምጧል፡፡

ሊጉ ነገ በሚደረጉ 6 ጨዋታዎች ይቀጥላል፡፡ አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ በ9፡00 እና በ11፡30 የሚደረጉት ጨዋታዎች ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸው ናቸው፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ዳሽን ቢራን የሚያስተናግድበት ጨዋታ 9፡00 ሲካሄድ ከተከታዩ በ10 ነጥቦች ርቆ የተቀመጠው ቅዱስ ጊዮርጊስ በዝውውር መስኮቱ ተጫዋቾችን ካስፈረመውና የመውረድ ስጋት ውስጥ ከሚገኘው ዳሽን ቢራ ጠንካራ ፉክክር ይገጥመዋል ተብሎ ባይታሰብም ሁለቱም ምርጥ ስብስብ በመያዛቸው ጨዋታው ትኩረት ሳቢ መሆኑ አይቀርም፡፡

በ11፡30 ሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ኢትዮጵያ ቡና ከተከታዩ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ይፋለማሉ፡፡ በሁለቱ ክለቦች መካከል የ6 ነጥቦች ቢኖርም በመጀመርያው ዙር ያሳዩትን ፉክክር ይደግሙታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በቀሪው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መርሃ ግብር ይርጋለም ላይ ሲዳማ ቡና ሀዋሳ ከነማን ፤ ሐረር ላይ ሐረር ሲቲ መከላከያን ፤ አሰላ ላይ ሙገር ሲሚንቶ ኢትዮጵያ መድንን አርባምንጭ ላይ አርባምንጭ ከነማ ደደቢትን በተመሳሳይ በ9፡00 ያስተናግዳሉ፡፡

ፕሪሚየር ሊጉን ቅዱስ ጊዮርጊስ በ42 ነጥቦች ከላይ ሲመራ ኢትዮጵያ መድን በ8 ነጥቦች የመጨረሻውን ደረጃ ይዘዋል፡፡ በከፍተኛ ግብ አግቢነቱ ሰንጠረዥ ላይ ደግሞ ኡመድ ኡኩሪ በ13 ግቦች ይመራል፡፡

{jcomments on}

ያጋሩ