​የጨዋታ ሪፖርት | የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ በፈረሰኞቹ ድል አድራጊነት ተደምድሟል

በ17ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ቀን ውሎ የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ በሊጉ አናት ላይ የሚገኙትን ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ደደቢትን አገናኝቶ ፈረሰኞቹ እጅግ በደመቀ የደጋፊዎቻቸው ድጋፍ በመታገዝ 3-2 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችለዋል፡፡

አሰልጣኝ ማርት ኑይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ባለፈው ሳምንት ወደ አርባምንጭ ከተማ ተጎዞ አርባምንጭ ከተማን 4-1 ካሸነፈው ቡድናቸው ፊት ላይ በጉዳት ያልነበረውን ሰልሀዲን ሰኢድ ወደ ቋሚ 11 ሲመልሱ በእሁዱ ጨዋታ ተቀይሮ የገባው ፕሪንስ ሲቨሬን ወደ ቋሚ አሰላለፍ ለመጀመሪያ ጊዜ መግባት ችሏል፡፡ እንደተለመደው በተመሳሳይ 4-3-3 የተጫዋቾች አደራደርም ጨዋታቸውን ጀምረዋል፡፡
አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ በበኩላቸው በጉዳት እና ቅጣት ከታመሰው ስብስባቸው አስገዳጅነት የጨዋታ አቀራረብ ለውጥ አድርገው በ3-4-1-2 (በአብዛኛው ወደ 5-2-3 የሚዋልል) ቀርበዋል፡፡ አዲሱ ፈራሚ አንዶህ ኩዌኬ ከአይናለም ኃይለ እና አክሊሉ አየነው ጋር በተከላካይነት ሲጣመሩ ሌላኛው አዲሱ ፈራሚ ኦፓኩ ኤሪክ ከሶስቱ ተከላካዮች ፊት ያለውን ቦታ ሸፍኗል፡፡
ከጨዋታው መጀመር በፊት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እንዲሁም የቅዱስ ጊዮርጊሱ የመሀል ተከላካይ ስፍራ ተጫዋች የሆነው ሰልሀዲን በርጌቾ ከዚህ ቀደም በኢትዮጲያ መድን ላሰለጠኑት የአሁኑ የደደቢት አሰልጣኝ ለሆኑት አስራት ሀይሌ የምስጋና ስጦታ አበርክቷል፡፡

በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ቅዱስ ጊዮርጊስ በንፅፅር ከተጋጣሚያቸው በተሻለ መንቀሳቀስ ችለዋል፡፡ በዚሁ አጋማሽ ሁለቱ የደደቢት የመስመር ተመላላሾች ስዩም ተስፋዬ እና ብርሃኑ ቦጋለ በሚገባ የቡድኑን የማጥቃት እንቅስቃሴ ማገዝ ባለመቻላቸው ደደቢቶች ወደፊት ከመከላከል ወደ ማጥቃት በሚደረግ ሽግግር ወቅት ሁለቱ ተመላላሾች መገኘት በሚገባቸው ቦታ ላይ መገኘት ሳይችሉ በመቅረታቸው በርከት ያሉ ኳሶች ሲበላሹ ተስተውሏል ፡ ከዚህም የተነሳ የቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴ በቀጥታ ከግብ ጠባቂው እና ከተከላካዮች በቀጥታ ወደ ፊት በሚጣሉ ኳሶች ላይ ብቻ ተገድቦ ተስተውሏል፡፡

በአንጻሩ ቅዱስ ጊዮርጊሶች እንደተለመደው በሁለቱ የመስመር አጥቂዎች በተለይም በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ጥሩ መንቀሳቀስ በቻለው ፕሪንስ ሲቨሬኖ ዋንጎ በኩል ጥሩ ጥሩ የማጥቃት እንቅስቃሴዎችን ሲዘነዝሩ ተስተውሏል፡፡

በመጀመሪያው አጋማሽ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ የመሀል ሜዳውን ብልጫ በመውሰድ በተደጋጋሚ ወደ ጎል ለመድረስ ጥረዋል፡፡ በዚህም የመጀመሪያውን ግብ ለማስቆጠር 15 ደቂቃዎች ብቻ ነበር የፈጀባቸው፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በሚታወቁበት የመስመር አጨዋወት በግራ መስመር አቅጣጫ ፕሪንስ በግሩም ሆኒታ ወደ ደደቢት የግብ ክልል ከገባ በኃላ በአቅራቢያው ብቻውን ለነበረው ሳልሀዲን ሰኢድ አቀብሎት ሰልሀዲንም በግሩም ሆኔታ ኳሷን ከመረብ አዋህዷት ፈረሰኞቹን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል፡፡

ከግቧ መቆጠር በኃላ ጫናቸውን አጠናክረው የቀጠሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በድጋሚ በ31ኛው ደቂቃ ላይ ምንተስኖት አዳነ ከቀኝ መስመር የተሻገረለትን ኳስ በደደቢት ተከላካዮች የቦታ አያያዝ ስህተት ተጠቅሞ በመታገዝ በግምባሩ በመግጨት መሪነታቸውን ወደ 2-0 ማሳደግ ቻለ፡፡
ደደቢቶች ተዳክመው በተስተዋሉበት በዚሁ የመጀመሪያ አጋማሽ ይህ ነው የሚባል ኢላማውን የጠበቀ የግብ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም፡፡ ጌታነህ ከበደ ከቋሙ ኳሶች በቀጥታ ሞክሮ ወደ ውጪ ከወጡበት ኳሶች ውጪ በክፍት ጨዋታ የግብ እድሎችን የፊት መስመር ተሰላፊዎች ጋር መድረስ አልቻሉም፡፡


የሁለተኛው ግብ መቆጠርን ተከትሎ አሰልጣኝ አስራት የተከላካይ አማካዮን ኤሪክ ኦፓኮን አስወጥተው ሰለምን ሀብቴን በማስገባት በጨዋታው ደካማ እንቅስቃሴ ሲያሳይ የነበረውን አምበሉ ብርሃኑ ቦጋለን ወደ መሀል በማስገባት ሰለሞን የተመላላሽነት ሚናን በመስጠት ወደ ጨዋታው ለመለመለስ ጥረት አድርገዋል፡፡ ተቀይሮ የገባው ሰለሞን ከብርሃኑ በተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴውን ለማገዝ ሲሞክርም ተስተውሏል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሬ ላይ ደደቢቶች ስዩም ተስፋዬን አስወጥተው ኤፍሬም አሻሞን በማስገባት ኪዌኪ አንዶህን በቀኝ መስመር እንዲሁም ሰለምን ሀብቴን በግራ መስመር ተከላካይነት በማሰለፍ የጨዋታ ቅርጻቸውን ወደ 4-4-2 በመቀየር ከመጀመሪያው በተሻለ መንቀሳቀስ ችለዋል፡፡ ነገርግን አሁንም ፈረሰኞቹን ግብ ከማስቆጠር አላገዳቸውም፡፡ በ51ኛው ደቂቃ በሀይሉ አሰፋ ከግራ መስመር ያሻማውን የቆመ ኳስ የደደቢቱ ግብጠባቂ ክሌመንት አሽቴ በሰራው ስህተት ያገኘውን ኳስ ሳልሀዲን በርጌቾ ገጭቶ የሞከራት ኳስ የግቡ ቋሚ ለትማ ስትመለስ በቅርብ ርቀት የነበረው ሰልሀዲን ሰኢድ በጨዋታው ለራሱ ሁለተኛ በሊጉ ደግም ዘጠነኛ ግቡን አስቆጥሮ የፈረሰኞቹን መሪነት ወደ 3-0 ማሳደግ ችሏል፡፡

ከሶስተኛዋ ግብ መቆጠር በኃላ ደደቢቶች ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ቢያደርጉም ተስፋ የመቁረጥ ስሜት በሚመስል መልኩ በተደጋጋሚ ጥፋቶችን ሲፈፅሙ እና በተደጋጋሚ የቢጫ ካርድ ሰልባ ሲሆኑ ተስተውሏል፡፡

አስቻለው ታመነ ጌታነህ ከበደ ላይ በሰራው ጥፋት የተገኘውን የቅጣት ምት የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪው ጌታነህ ከበደ በግምት ከ20 ሜትር አካባቢ በመምታት ማራኪ ግብ አስቆጥሮ ውጤቱን ወደ 3-1 ማጥበብ ቻለ፡፡ በግቧ መቆጠር የተነቃቁ የሚመስሉት ደደቢቶች በአንድ ደቂቃ ልዩነት ተቀይሮ ከገባ በኋላ ጥሩ መንቀሳቀስ የቻለው ሰለሞን ሀብቴ ከግራ መስመር ያሻማውን ኳስ ሽመክት ጉግሳ ሲሞክራት የአበባው ቡጣቆን ፊት ገጭታ ኳሷ ወደ መረብ በመዋሃዷ ውጤቱ ወደ 3-2 ሊጠብ ችሏል፡፡

የቅዱስ ጊዮርጊስ 3-0 መሪነት በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት በተቆጠሩ ግቦች አጣብቂኝ ውስጥ ቢገባም ከ5 ደቂቃ በኋላ የደደቢት አምበል የሆነው ብርሃኑ ቦጋለ በሁለተኛ ቢጫ በቀይ ካርድ ከሜዳ መውጣት ሰማያዊዎቹ በአስገራሚ ሁኔታ ወደ ጨዋታው የተመለሱበት መነቃቃት ላይ ላይ ቀዝቃዛ ውሃ ቸልሶበታል፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊሶች በዚህ ድል በመታገዝ ነጥባቸውን ወደ 35 አሳድገው ተከታዮቻቸው ነገ ጨዋታቸውን እስኪያደርጉ ድረስ ልዩነታቸውን ወደ 7 ነጥብ በማስፋት ከአናት ላይ መቀመጥ ችለዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *