ማርት ኑይ – ቅዱስ ጊዮርጊስ
ስለ ጨዋታው እና ስለ ዋንጫ ግስጋሴያቸው
” ቡድኔ ከሳምንት ወደ ሳምንት ጥሩ መሻሻሎችን እያሳየ ይገኛል፡፡ በተለይም በሁለቱ መስመሮች በኩል ፕሪንስ እና በሀይሉ ጥሩ ነበሩ፡፡ የሁለተኛው ዙር ሁለተኛ ጨዋታ ላይ ስለምንገኝ አሁን ላይ ሆኖ በርካታ ጨዋታዎች እየቀሩን ስለ ዋንጫ መናገርያ ጊዜው አይደለም፡፡”
ከመጀመሪያው ዙር በተሻለ ቡድኑ ላይ ስለመጡ ለውጦች
” ከመጀመሪያው የተለወጠ ነገር የለም አሁንም ተመሳሳይ ነው፡፡አንዳንድ ጊዜ አላስፈላጊ የሆኑ ስህተቶችን በተለይም ተከላካይ ስፍራ ላይ እንሰራለን፡፡ ግለሰባዊ ስህተቶችን መቀነስ ከቻልን ከዚህም በተሻለ መንቀሳቀስ በቻልን ነበር፡፡ ”
ስለ ቡድኑ ወቅታዊ ሁኔታ
“ቡድኑ በሽግግር ላይ እንደመገኘቱ ይህ አመት በተለይ የሽግግር ወቅት ነው፡፡ ለዚህም እንደ ማሳያ የሚሆነው በርካታ አዳዲስ እና ወጣት ተጫዋቾችን በቡድኑ ውስጥ እየተጠቀምን እንገኛለን ከዚህም የተነሳ የዘንድሮው የውድድር አመት የሽግግር ወቅት ነው፡፡”
አሰልጣኝ አስራት ሀይሌ – ደደቢት
በጨዋታው ላይ በተደጋጋሚ ስላደረጉት የጨዋታ ቅርፅ እና የተጫዋቾች ሚና ለውጥ
“አሰልጣኝ በአንድ ነገር ላይ ብቻ ሊገደብ አይችልም ፤ በጨዋታ ሂደት እንደ ጨዋታው እንቅስቃሴ እና እንደ እይታው ልምምድ ላይ የሰራቸውን ነገሮች መቀያየር ይችላል፡፡ በጨዋታው የተለያዩ የጨዋታ ታክቲኮችን ተጠቅመናል፡፡ በዛሬው ጨዋታ ቡድኔ ጥሩ ተንቀሳቅሷል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በዛሬው ጨዋታ ላይ ሎተሪ ነው የደረሰው ፤ በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ ላይ ሜዳ ውስጥ አልነበሩም ያሸነፉንም በራሳችን በሰራናቸው ሁለት ስህተቶች ነው፡፡ ለእኔ በጨዋታም ሆነ በተቆጠሩብን ግቦች በሚያሳምኑ አልነበሩም፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ አሁን ላይ ከእኛ የተሻለ ቡድን አይደለም የተሸነፍነው በመላ ምት ነው፡፡ ሽንፈቱን በፀጋ ተቀብለናል ነገርግን በጨዋታ እንቅስቃሴ ረገድ ከቡና ጋር ከነበረው ተሽለን ቀርበናል፡፡”
ስለ ስፓርት ሚዲያዎች
“የሚዲያ ባለሙያዎች ላይ ወገንተኝነት ይታያል፡፡ እርግጥ ነው ደደቢት ብዙ ደጋፊዎች የሉትም፡፡ እኔ እዚህ ጋር ብዙ ነገር አወራለሁ ፤ ነገር ግን አንድም ቀን እኔ ያልኳትን ቃል በሚድያ ሲነገር ሰምቼ አላውቅም፡፡ የስፖርት ጋዜጠኛ እስከሆናችሁ ድረስ ሚዛናዊ የሆነ መረጃን ማስተላለፍ አለባችሁ፡፡ ሁሉም ቡድን እኩል ሊታዩ ይገባል፡፡ የዛሬውን ጨዋታ በዳኝነት የመራው ዳኛ ለአራተኛ ተከታታይ ጊዜ ደደቢት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ያደረጉትን ጨዋታ መርቷል፡፡ ከሌላ ቡድን ጋር ለምሳሌ ከቡና ጋር ስንጫወት የተለያዩ ዳኞች ናቸው ጨዋታዎቹን የመሩት፡፡ ከጨዋታው በፊት ዳኛውን ምደባ ሳይ በተፅዕኖ በርካታ ነገሮች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ ገምቼ ነበር፡፡ ከጨዋታው በፊት በዳኛው ምደባ ላይ በርካታ ጭቅጭቅች ነበሩ ነገርግን ምላሽ አላገኘንም፡፡ በእርግጥ ዳኛው ጥሩ ዳኛ እንደሆነ እናውቃለን፡፡ ነገርግን ቢያንስ አንድ ልጅ ከእኛ በቀይ ሊወጣ እንደሚችል ገምተን ነበር ፤ እንደነዚህ አይነት ጉዳዮችን አስተያየት እየሰጣችሁ ማቅረብ ይገባችኃል፡፡”
ከጨዋታው በፊት ስለተበረከተላቸው ሽልማት
“በአሰልጣኝነት ዘመኔ በርካታ ተጫዋቾችን በክለብም ሆነ በብሔራዊ ቡድን ደረጃ አፍርቻለሁ፡፡ ዛሬ የምታዩት ጊዮርጊስ እኔ የተከልኩት ቡድን ነው ማንም ዛሬ ላይ መጥቶ ቢሰራበት የኔ መሠረት ነው፡፡ ከአንዴም ሁለቴ ከጫካ ጀምሮ ወደ ላይ ያሳደኩት ቡድን ነው፡፡ ባደረኩት አስተዋፅኦ እና ያሳደኳቸው ልጆች ውለታቸውን በመመለሳቸው ደስ ብሎኛል፡፡ አባታችን ለዚህ ያበቃሃን አንተ ነህ ብለው የስራህን ስራ በህዝብ ፊት እንደዚህ ክብር ሲሰጥህ ደስ ያሰኛል፡፡”