ሀድያ ሆሳዕና ቀደም ብሎ በኦንላይን አስመዝግባቸው የነበሩ ሁለት የውጪ ዜጋ ተጫዋቾችን ዝውውር አጠናቋል፡፡
በአሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት መሪነት የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን በሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ እየገመገመ የሚገኘው ሀድያ ሆሳዕና በትላንትናው ዕለት ቶጓዊው ግብ ጠባቂ ሱሆሆ ሜንሳን በዝውውር ፍፃሜው ቀን በእጁ ያስገባ ሲሆን ቀደም ብሎ በኦንላይን ስማቸውን አስመዝግቧቸው የነበሩ ሁለት የውጪ ዜጋ ተጫዋቾችን ዝውውር በዛሬው ዕለት ማጠናቀቁን ክለቡ ለሶከር ኢትዮጵያ አሳውቋል፡፡
የጋና ዜግነት ያለው ከማል ጃፋሩ ለሀድያ ሆሳዕና የፈረመ ሁለተኛው የውጪ ዜጋ ተጫዋች ሆኗል፡፡ በትውልድ ሀገሩ ቤከም ዩናይትድ በመጫወት የክለብ ህይወቱን የጀመረው ይህ አጥቂ በመቀጠል ወደ ዛምቢያ ሊግ አምርቶ ሙፉሊራ ወንድረርስ፣ ቢውልድ ኮን እና ያለፉትን ሁለት የውድድር ዓመታት ደግሞ ፕሪስን ሊዎፓርድስ በተባለ ቡድን ቆይታን ካደረገ በኋላ ማረፊያውን የኢትዮጵያው ክለብ ሀድያ ሆሳዕና አድርጓል፡፡
የቤኒን ዜግነት ያለው አርናውድ አካክፖ ሦስተኛው የውጪ ዜግነት ያለው አዲሱ የሀድያ ሆሳዕና ፈራሚ ሆኗል፡፡ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የዋና ከተማዋ ኪንሻሳ ክለብ በሆነው ኤ ኤስ ቪታ ክለብ ሲጫወት የቆየው ይህ ተከላካይ የአሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረትን ክለብን መቀላቀል ችሏል፡፡